የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭነት፡- እውነት ወይስ ተረት? (5)

የጥንቷ ኢትዮጵያ ግዛቷ ከየት እስከ የት ነበር?

‹ኢትዮጵያ የዓለማችን የሥልጣኔ ምንጭ ናት› ብለን ስናወራ ንግግራችን አሁን ካለችው ኢትዮጵያችን ጋር ብቻ የተያያዘ ክልልን የሚያመለክት አይደለም፤ ከዚያም በላይ ‹ኢትዮጵያ› የሚባለው ግዛት ሦስት አህጉራትን ጭምር ያካልል እንደነበር ነው ማስረጃዎቹ የሚመሰክሩት፡፡ እንዲሁም በጥንት ጊዜ ‹ኢትዮጵያውያን› የሚባሉት ጥቁር ሕዝቦችን ኹሉ ነበሩ፡፡ በጥቅል ሲቀመጥ የጥንት ኢትዮጵያ ከህንድ እስከ አትላንቲክ ውቅያኖስ ያለውን ክልል ያጠቃልል ነበር፡፡

በዚህ ላይ የሚነሣው ጥያቄ ‹የጥንትዊት ኢትዮጵያ ግዛት በጣም ሰፊ ክልልን የሚመለከት ከሆነ፤ ከህንድ እስከ ሊቢያ የተዘረጋ ከነበረ፤ አሁን ያለችው ደግሞ በጣም ትንሹን ክፍል ትወክላለች ማለት ነው፤ ይህ ከሆነም በምን መብትና መነሻ ነው ጥንታዊቷን የምትወክለው? ሱዳንስ፣ ሱማሌስ፣ ኤርትራስ፣ ሌሎቹስ የአፍሪካ ሀገራት የጥንቷን ኢትዮጵያን የመወከል መብት አይኖራቸውም ወይ? ከአፍሪካ ባለፈም በመካከለኛው ምሥራቅ እስያ ያሉ ሀገሮች ኢትዮጵያውያኑ እኛ ነን ቢሉ አይችሉም ውይ? የኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የግዛት ስፋት ግን የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ምንጭነት የሚያጠፋና ከአሀኑ ነበራዊ የዓለም ሁኔታ ጋር ሊያምታታን አይገባም፡፡ ይህን ነጥብ የሚከተለው ገለጻ ግልፅ ያደርግልን ይመስለኛል፡፡

የአሜሪካ የአዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ‹ኢትዮጵያ› የሚለውን ስም ‹ሱዳን› በሚል ቀይሮ ላሳተመው መጽሐፍ ማስተካካያ እንዲደረግበት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በጠየቀየችበት መጽሐፍ ላይ ከጥንታዊ ታሪክ አንጻር የኢትዮጵያን መልክዐምድራዊ ማብራሪያ በአጭሩና በታመቀ መልኩ እንዲህ በሚል ተገልጽዋል፡፡

‹… የሕዝቡን ማንነትና የአካባቢውን የመልክዐ ምድር ቅርጽ ስንመለከት ከቅርጹ አንጻር ከግበጽ ደቡብ ጀምሮ እስከ ሕንድ ድረስ ያለውን አካባቢ የሚሸፍን ሆኖ ይገኝ እንደነበረ ሲነገር፤ በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብም ኢትዮጵያዊ የሚለውን የጋራ ቅጽል ስም ይዞ ይገኝ እንደ ነበር የታወቀ ነው፤ ቀስ በቀስ ግን በግራና በቀኝ የሚገኙ አካባቢዎች በአንድ በኩል በተለያየ ጊዜ ከተለያየ የታሪክ አጋጣሚ የተለየ ስምና የፖለቲካ ድንበር እየያዙ ሲገኙና በዚህም ምክንያት የነዋሪዎቻቸው (ሰዎች) ስያሜ፣ ባህልና አምልኮት እየተለወጠ ሲመጣ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነው የዚህ አካባቢ ማእከላዊ ክፍል ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እንደያዘ ለዘመናት መቆየቱ (መቀጠሉ) ብቻ ሳይኾን ቀደም ብሎ በጋራ ስለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ይነገሩ የነበሩትን የታሪክ ትውስታዎች ይዞ ይገኛል፤ ከዚህም በቀር የዓባይ ምንጭ መነሻ የሆነችው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ማእከላዊ ጠንካራ መንግሥትን ለመመሥረት ቅድሚያ ያለው ሆኖ እንደመገኘቱ መጠን በአንጻሩ እጁን ለጠላት ሳይሰጥ፣ ነጻነቱን፣ ክብሩንና ታሪኩን፣ ወዘተ ጠብቆ የቅዱሳት መጻሕፍት፣ የጥንት ታሪክና የሥነ ጥንት ኢትዮጵያ ህልውና መቀጠል ምሳሌ ሆኖ ተገኝቷል፡፡[1]

አለቃ አስረስ የኔሰውም ‹ትቤ አክሡም መኑ አንተ?› በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 102 ላይም ‹ የካም ዘር እንኳንስ በክፈለ ሀገሩ በአፍሪካ ይቀርና ከተሰጠው ክፍል አልፎ በሴም ሀገር በእስያ መንግሥት የመሠረተ የካም ዘር መሆኑን› በመጠቆም በምሳሌ ሲያስረዱ ‹ከሴም ዘሮች ታላቁ ባለቃልኪዳን አብረሃም ነው፤ በአብረሃን ዘመን የኢየሩሳሌም ዙሪያ አውራጃዎች በማን እጅ እንደነበሩ ሚስቱን የሚቀብርበት ቦታ አጥቶ ከካም ዘሮች መቃብር መሬት ገዝቶ ሚስቱን እንደቀበረ መጻሕፍቱ ይነግሩናል፡፡› ብለው በዘፍጥረት 23፤ 4 ያላውን ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ፦ እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር።› ያለውን ቃል እንደማሳያ ይጠቅሳሉ፡፡ በገጽ 103 ላይም ‹ባቢሎንን ያቀናና የመሠረተ የካ የልጅ ልጅ የኩሳ (ኩሽ) ልጅ ናምሩድ መሆኑን ገና አላወቁትም፤› በማለት በእሥያ ይገኝ የነበረው አብዛኛው ሕዝብ የካም ዘር፡- የኢትዮጵያ ግዛት አካል፡- እንደነበር ያብራራሉ፡፡

እኝሁ ሊቅ በገጽ 127 ላይ ‹‹የሀገራችንን ታሪክ ይቅርና አባቶቻችን አልፈው የባቢሎንና የፋርስን ነገሥታት፣ የሮምንና የቁንስጥንጥንያን ነገሥታት የግብጽማ ገንዘባቸው ነው፤ የነዚህን ሁሉ ታሪክ ከየቋንቋው ለቅመው በግዕዝ ጽፈው አስቀምጠውልናል፡፡› ካሉ በኋላ‹ የመጻሕፍቱንም ቁጥር ሳናበዛ እንኳ በቀላሉ ፩ኛ ዮሐንስ መደብር፣ ፪ኛ ዩስፉስ፣ ፫ኛ ዜና እስክንድር፣ ፬ኛ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ፣ ፭ኛ አውሻክር፣ ፮ኛ አቡፈረጅ፣ ፯ኛ መቃቢስ፣ ፰ኛ መጽሐፈ በረላም፣ ደግሞ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡› በማለት የታሪኮቹን ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ስለ ኩሽ ዘር የጥንት ገናናነትና የትውልድ ሁኔታ  ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

‹ከማየ አይኅ በኋላ ሳባንና አቢስን የወረሱ በሳባ፣ በአቢስ የነገሡ የሳባ፣ የአቢስ ባላባቶችና መደበኞች ነገደ ካም ናቸው፡፡ ካም ኩሽን፣ ኩሽ ሳባንና አቢስን ይወልዳል፤ ከነዚህም ሌላ ፳፮ ነገድ ወልዷል፡፡ ከ፳፰ቱ ነገደ ሽባእና ድዳን የሚባሉት እነዚህ ፪ቱ ነገድ እንደ ምናሴና እንደ ኤፍሬም የልጅ ልጆች ናቸው፤ (ዘፍ.፲÷፯)፡፡ አቢስ የበኩሩ የሳባ ሳብዓይ የናምሩድ ተከታይ ፯ኛ ልጅ ነው፤ ከሳባ እስከ ናምሩድ ፮ቱ ሽባእና ድዳን ሳይቀሩ ፰ቱ ነገድ በኦሪትና በዜና መዋዕል ተጥፈዋል፤ የቀሩት ኻያው ግን በታሪክ እንጂ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ አይገኙም፡፡ አንዳንድ ታሪክ በአቢስ ፈንታ ከለው፣ በከለው ፈንታ አቢስ ይላል፤ ከለው የአቢስ ፪ኛ ስም ነው፤ ኢትዮጲስ የኩሽ ፪ኛ ስም እንደ ኾነ፡፡› ያሉትም አንድ ጥቁምታ ነው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ወሐዲስ፤ ገጽ 16)

ከሀገራችን የታሪክ ምንጮች መካከል መሪ ራስ አማ በላይ በዋሻ ውስጥ የተደበቁ የጥንት የብራና መጽሐፎችን አገኝቻለሁ በማለት የተለዩ የታሪክ ማስረጃዎችን ይዘው ብቅ ያሉ ሰው ናቸው፡፡ እሳቸው ‹የጥንቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ› በሚለው መጽሐፋቸው እንዳስቀመጡት ከኾነ ‹እስያ› የሚለው የአህጉር መጠሪያም የተወሰደው እፄ (እፅያ) ሰንደቅ አልማ ከተባለው የኢትዮጵያ መሪ ሲኾን ትርጓሜውም ‹ታላቅ ሀገር› ማለት ነው (የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ ገጽ 41)፡፡

 በዚህ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ነገዶች እንዴት በተለያየ አካባቢ ተበታትነው እንደሚገኙና መለያቸው ምን እንደኾነ አብራርተው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ ስለ ባቢሎን፣ ስለ ሞርታኒያ፣ ስለ ታንዛኒያና የመሳሰሉት አገሮች በኢትዮጵያ ነገዶች እንዴት እንደተመሠረቱና እንደቀኑ ማስረጃ ይሠጣል፡፡ ከላይ ካስቀመጥናቸው ከድሩሲላ እና ከጃክሰን መጽሐፎች ጋርም አብሮ ይሄዳል፡፡ ይህንን ፐሮፌሰር መስፍንም ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 27 ላይ ‹ገና ተጠንቶ አላለቀም እንጂ ኢትዮጵያውያን ከሞሮኮ እስከ ህንድ ማኅተማቸው ይገኛል›፡፡ ብለዋል፤ በገጽ 70-71 ላይም ጥንታዊት ኢትዮጵያ ‹ዓለምን ከሮም ጋር ተካፍላ መግዛቷ እንደሚባለው ተረት ነው እንበል፤ በሕንድ፣ በሞሮኮና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያ መጣን የሚሉት ሰዎች ታሪክ ተመርምሮና  ተጣርቶ ታውቋል ወይ? በእነዚህ በሁለቱም አገሮች ጥንት ከኢትዮጵያ መምጣታቸውን የገለጹልኝ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡› ብለው የገጠመኝ ልምዳቸውን በምሳሌነት ጠቅሰው አሳይተዋል፡፡

የመሪ አማን በላይ መጽሐፍ ‹ኢትዮጵያ› የሚለው ስም ኢትኤል ከሚለው የመልከጼደቅ ልጅ መሰየሙን ያብራራል፡፡ ትርጉሙንም ሲያስቀምጥ ‹ኢትኤል ማለት የአምላክ ሥጦታ፤ ኢትኦጵ ማለት ደግሞ የወርቅ ሥጦታ ማለት ነው› በማለት ይገልጻል፡፡ ኢትኤል ግዛት መሥርቶ መኖር የጀመረበት የግዮን ሥፍራም ‹ዮጵ› በሚባለው ወርቅ የከበረ ስለነበረ የእሱን ስም ‹ኢትዮጵ› የሚስቱ ስም የ‹ሲና›ን ደግሞ ‹ኢንቆዮጳግዮን› ብሎ ቀይሯል፡፡ ከዚያም ‹ኢትኤል ግዮን ወንዙን ለወንዝ አጠራቅሞና ሰብስቦ እስከሚገናኝበት ያለውን ምድር ኹሉ በስሙ ኢትዮጵያ እንዲባል አድርጓል፡፡› (የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፤ ገጽ 26)፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉት ዘሮቹም በየሔዱበት ሥፍራ መሠረታቸውን ሳይለቁ ኢትዮጵያውያን እየተባሉ ተጠርተዋል፡፡ በዚህ የተነሣም ይመስላል ሦስት አህጉራት በአንድነት ኢትዮጵያ የሚል ስም ይጠቀሙ የነበረው፡፡

እንዲሁም በዚህ ዙሪያ ከሰፈሩ ማስረጃዎች መካከል ሰር ዋሊሰ ባጅ የተባለው የጥንት ግብፅ ጥናት ተመራማሪ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› በሚለው መጽሐፉ መግቢያ፡-

‹ሆሜርና ህሮዶቶስ የሱዳንን፣ የግብፅን፣ የአረብ፣ የጳላስጣይንና የእስያን እና የህንድን ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ብለው ይጠሯቸዋል፡፡› ብሏል፡፡ ይህንን የበለጠ ሲያብራራ ‹የጥንት የታሪክ ጸሐፊዎችና የጂኦግራፊ ሊቃውንት ከግብፅ እስከ ህንድ ባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩትን ሕዝቦች በሙሉ ኢትዮጵያውያን በማለት ይጠሯቸው ነበር፤ ስለኾነም በዚህ ክልል የሚኖሩት ባለጥቁር ቆዳ (ጥቁር) ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ እነዚህን ኢትዮጵያውያንንም ምሥራቃውያንና ምዕራባዊያን በማለት በሁለት ይከፍሏቸው ነበር፤ ምሥራቃውያን የሚሏቸው እስያውያኑን ሲኾን ምዕራባውያን የሚሏቸው ደግሞ አፍሪካውያኑን ነበር፡፡› ብሎ አስቀምጧል፡፡

 ባጅም ይህንን ያቀረበው ጋሽ ፀጋዬ እንደጠቀሰው በጥንቶቹ የግሪክ ታሪክ ሊቃውንት ሄሮዶቶስንና ኢፎሩስን፣ የሮማ ታሪክ ጸሐፊ ስትራቦን፣ የባዛንታይን ምሁር እስጢፋኖስን፣ … የመሳሰሉትን የጥንት የታሪክ ምንጮች መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ስለ አፍሪካ ስያሜም ተጨማሪ ነጥብ ማንሳት የተሻለ ሥዕል ይሰጠናል፡፡ አፍሪካ የሚለው አህጉር ‹አፋር› ከሚለው ቃል ተወስዶ ሳይታወቅ በፊት በአብዛኛው መጠሪያው ‹ኢትዮጵያ› ነበር፡፡ በጥንት የአፍሪካ ባህል፣ ሥነ ልሳንና ሥነ ሰብ ጥናት የታወቀው ከላይ የጠቀስነው ምሁር ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ስለ አፍሪካ ስያሜ በጦቢያ መጽሔት ተጠይቆ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

‹አፍሪካ የተሰኘው የአህጉሪቱ ስም እንኳን የመነጨው ከካማውያን ፊደልና ስም ነው፡፡ አፍ ማለት ‹ምድር› ወይም በምድር ላይ ያለ ‹በቀልት› ማለት ነው፡፡ አፍ-ራካ ወይም አፍ-ሪካ ማለት ‹የእግዚአብሔርና የፀሐይ ንጉሥ ምድር› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አፋር ወይም አፈር የተባለው የአፋር ስም፣ ኦል-ኦፍ ወይም ዎል-ኦፍ ወይም ዘራፍ የምንለው የፉከራ ቃላችን፣ የዘር ግንዳችን መነሻ አፍሪካ መኾኑን በመንፈስ ኩራት ለመግለፅ ነው፡፡›  (ጦቢያ መጽሔት ቅጽ 5 ቁ.11፣ 1990)

 ፀጋዬ በሌላ ጽሑፉ ‹በጥንቶቹ ግብፃዊያን ‹አፋር› ወይም ‹አፈር› የሚለው ቃል ‹ጥቁር-አፈር› ማለትን ነው የሚያመለክተው፡፡› ብሎ አስቀምጧል፡፡ (Africa Origin of Major World Religion: The Origin of the ‘Tirinity’ and Art -Ethiopian Origin to Egypto-Greek and Hebrew, page 99)

ምንም እንኳን አቀራረባቸውና የመረጃ ምንጫቸው ቢለይም ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የተለየ መረጃ አግኝተው ያቀረቡት መሪ ራስ አማን በላይም አፍሪካ የሚለው የአህጉሪቱ መጠሪያ ከአፋር እንደተወሰደ ይስማማሉ፡፡ እሳቸው፡-

‹ኦፊር የአፍሪካውያን አባት ለዛሬዎቹ አፋሮች አባት ነው፡፡ በኦፊር ስም ከዛሬው አውሳ የሚገኝ ወርቅ ኦፊር ይባል ነበር፤ ዋና ከተማው ተርሴስ ነው፤ እርሱም በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የታወቀ ወርቅ ስለነበረ የኦፌር ወርቅ ክቡር ነበር፤ በኦፌር ሀገሩን አፍሪቃ ሰዎችን አፍሪካያውያነ ይሉዋቸዋል፡፡› በማለት አስቀምጠውታል፡፡ (አብርሂት  2000 ዓ.ም. ገጽ 52)

በዚህ አገላለፅና ማስረጃ መሠረት አፍሪካ የሚለው ሰም ‹አፋር› ከሚለው መጠሪያ የተወሰደ ከኾነና አፋርም በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኝ መኾኑም እሙን ከኾነ፤ እንዲሁም የጥንት አፍሪካ ስም በኢትዮጵያ የሚጠራ ከነበረ፣ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ምንጭነት የሚመሰክሩ የተለያያዩ የትውፊት፣ የጽሑፍ፣ የአርኮሎጂና የሥነልሳን ማስረጃዎች ከመሠከሩ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ምንጭነት የሚቃወመው ማን ነው? የራሱን አላዋቂ ወይስ ሌላ? የራስ የኾነን ነገር እንዳለማወቅ/እንደማቅለል ትልቅ ችግር የለም፡፡

[1] የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ቅ/ሲኖዶስ፤ የዛሬ ኢትዮጵያ የቅዱሳት መጻሕፍት፣ የታሪክና የሥነ ጥናት ኢትዮጵያ ናት፤ 1992 ዓ.ም.ገጽ 5-6

Please follow and like us:
error

Leave a Reply