ያልዘሩት አይበቅልም (ስለ ኢትዮጵያ አስገራሚ ጽሑፍ ነው) 

(ከኮቴቤው የሻው ተሰማ)
ገና ሕጻን እያለሁ ነበር ለአያቴ ያለኝ ፍቅር በትንሷ ልቤ ውስጥ እየሰደደ ያኮረተው፡፡ ምን ላድርግ ያስጨፍረኛል-ያጫውተኛል- ፍንድቅድቅ እስክል፡፡
አሻ ቅምጥሻ… ቅምጥሻ
ሚስትህ ማናት፣
ጦጢት ናት- ጦጢት ናት!
እንዲያው ከመሆን ትሁን- ትሁን!
ቀጩ ቀጫጩ ያራዳ ገብስ፣
አይሸከሸክ አይነፈስ፡፡
ይችን ለምጃላችሁ፣ አያቴ ከዋለበት ሲገባ እየተንደረደርሁ ሄጀ እላዩ ላይ ጥምጥም ነው፡፡ አሁንም ሁኔታው እፊቴ አለ፤ ያንን ባዘቶ የመሰለ ጢሙን እያፍተለተልኩ፣ ለስላሳ በራውን እያባበስኩ ‹አባባ ትልቁ ዥፈንልኝ›፡፡› እያልኩ እለማመጠዋለሁ፤ ይቀጥላል፡፡
በስተኋላሽ ሆኜ እኔ ልንከትልሽ፣
በስተኋላሽ በኩል እኔ ልንከትልሽ (ቃግ)
በስተኋላሽ በኩል እኔ ልንከትልሽ፣
በስተኋላሽ በኩል እዚያው አንቺ ፍሰሽ፡፡
ብሎ እየዘፈነ ትከሻየን ይዞ እስክስታ ያለማምደኛል፡፡ አንዳንድ ቀንም እንቆቅልሽ የሚሉትን ጨዋታ ያጫውተኛል፡፡
‹እንቆቅልህ›
‹ምናውቅልህ›
‹ትንሻ መሰሶ ጫፏ ተዘልሶ፡፡›
እኔ መልሶቼን አቀርባለሁ ‹ የስንዴ ዛላ›
‹አይደለም›
‹የቡና መቁሊያ›
‹አይደለም›
‹የላሜ ቦራ ቀንድ›
‹አይደለም› ይላል ከዘራውን እያባበሰ፡፡
‹ያባባ ትልቁ ከዘራ›
‹አሁን አወቅህ- ጎበዝ የኔ አንበሳ!› ብሎ ሳም ሲደርገኝ፤ ካባ የተሸለምኩ ያህል ልቤ በኩራት ይኮፈሳል፡፡ አንድ ቀን እኔም እንቆቅልሽ ጠየቅሁት፡፡ እንቆቅልሹን የነገረኝ አንድ ሞኝ ሆዴ የሚባል ባልንጀራዬ ነበር፡፡
‹እንቆቅልህ አባባ ትልቁ›
‹ምናውቅልህ›
‹አንድ ቆንጅዬ ቅል ጠጉር አያበቅል፡፡› ስለው ግራ ተጋባና ከልቡ እየሳቀ የተለያዩ መልሶች ሞከረ፡፡ አልሆን ሲለው፡-
‹… እንዳትሰድበኝ በማር በወተት አምየሃለሁ፡፡ እንዳትረሳት ዕወቃት- እንዳትደፈር ጠብቃት ጦቢያን (ኢትዮጵያን) ሰጥቼሃለሁ፡፡› አለኝ፤ አገር ሰጠኝ፡፡ የሰጠኝ አገር ስም እንግዳ ስለሆነብኝ
‹ማነች ጦቢያ› ስል ጠየቅሁት፡፡ እንዴት እንደሚነግኝ ጨነቀው መሰል ዝም አለኝ፡፡ ደገምኩና ‹ጦቢያ ማናት- እናትህ ናት?› ብዬ ሳስጨነቀው ምንም ሳያናግረኝ ከኔ አባት ተነስቶ ወደራሱ ቤት ሄደ፤ ተከተልኩት፡፡ ክራሩን አነሳና ንጎራግር ጀመር፡፡ እኔ ደሞ ተበሳጨሁ፡፡ በቃ አንዴ ክራሩን ካነሳ እንኳን እኔን ሊያጫውት እግዚአብሔርም መሬት ወርዶ ቢያናግረው ኖር አይለውም፡፡ ክራሩን እየከረከረ፣ ዕንባው ጎርፎ ጢሙን እስኪያርሰው ድረስ ተመስጦ ያንጎራጉር ገባ፡፡
ወዜ ከቅስምሽ ነው፣ ሥጋዬ ካፈርሽ፣
ሕዋሴ ከትቢያሽ፣ ሥሬ ከሰፈርሽ፤
ሙቀቴ ከጉያሽ፣ ጠሌ ከከንፈርሽ፤
ምኞቴ ከተስፋሽ፣ አጥንቴ ከክብርሽ፤
ምሥጢሬ ከልብሽ፣ ሰንደቄ ከደብርሽ፡፡
የኔ ብቸኛ ቅርስ፣ አንቺን ከሚከፋ፣
እስትንፋሴ ትክሰም፣ የኔ ስሜ ይጥፋ፡፡
እምዬ ኢትዮጵያ- እናቴ ኢትዮጵያ
ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ማንነት ያስጨንቀኝ ጀመር፡፡ አንዳንዴ እሱ ከሚናገረው ስሰማ፣ ቀይ ጃኖ ቀሚስ ብሳ፣ ቢጫ ኩታ የተከናነበችና አረንጓደ ሻሽ ያሰረች፣ መልኳ ያማረ ሴት ወይዘሮ በምናቤ ድቅን ስትልብኝ ‹… ውይይ… ይቺስ ዘላለም ትኑር፡፡ የአባባ ትልቁ እናት ሳትሆን አትቀርም› እስከማለት እፈላሰፋለሁ፡፡
እኔም አጥንቴ እየጠኘከረ ሲመጣ፣ አያቴም የዚችን ሴትዮ ፍቅር ባያሌው እውስጤለመሸሸግ ሲጥር አጤንኩት፡፡ እኔም እንደሱ እንደዳፈቅራት ማንነቷን ለማወቅ ጥብጣቤን ጠበቅ አድርጌ ልፈልጋት ወሰንኩ፡፡ይችን ያያቴን ሴት ለመፈለግ ብዙ ቀኖች ተመኝቻለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ለፍልሰታ እንድቆርብ እናቴ በተስኪያን ስትወስደኝ ያያቴን ሴትዮ አገኘኋትና በደስታ መላዬ ጠፋ፡፡ የቅዳሴው ሥርዓት እስኪያልቅ ያችን ሴትዮ አትኩሬ ስመለከታት ዋልኩ፤ መቼም ሸግዬ ሴት ናት፡፡ ከበተስኪያን ወደ በታችን ስንመለስ ለናቴ ‹ያባባ ትልቁን ጦቢያ ዛሬ አየኋት አልኳት፡፡›
‹የት… ማናት?› ማለት እሷ፡፡
‹በተስኪያን ውስጥ አባባ ትልቁን (በሕጣንነቱ ነው መሰለኝ) ታቅፋው ተግርግዳው ላይ ተቀምጣለች› አልኳት፡፡
‹እሷ እኮ! ጦቢያ ሳትሆን እምዬ ማርያም- እማምላክ ነች› ብላ ሳቀችብኝ፡፡
‹ታዲያ የአባባ ትልቁ ጦቢያ እምን ውስጥ ነው ያለችው?›
‹እሷማ አገርህ ናት – አያትህ ዱሮ በጣሊያን ጊዜ ዘምተው የተዋጉላት›
‹አገሬማ ይችው› አልኩና መሬቱን አሳየኋት፡፡
‹አይ እንግዲህ አትበቅተኝ… ሂድና እሳቸውን ጠይቃቸው› አለችኝ፡፡
እኔም እቤት እንደገባሁ እንደገና አያቴን ያቺን ሴትዮ እንዲያሳየኝ እንደ ንፍፊት ፈትሬ ያዝኩት፡፡ በየቀኑ እየደጋገምኩ ስለኢትዮጵያ እንዲነግረኝና እንዲያሳየኝ ጠየኩት፡፡
‹ነፍሴ ተቆመች ስታድግ አሳይሃለሁ፡፡›
‹አሁንስ አድጌያለሁ፣ ይኸው አንተን ላክል አይደል›አልኩና እጎኑ ልጥፍ ብዬ ቁመቴን ከቁመቱ ላስተያይ ሞከርኩ፤ ግን ገና ከችኖቹም አልደረስኩ፡፡
‹ኢትዮብያ ቀድመ አያቶቼን ወለደች፣ ቅድመ አያቶቼም አባቶቼን ወለዱ፣… ስለዚህ ኢትዮብያ የሁላችን እናት ናት፡፡› አለኝ፡፡
‹የኔ እናቶች ብዙ ናቸው ማለት ነው?›
‹እነማን-እነማን?› እንደገና ጠየቀኝ፡፡
‹እምዬ፣ እማማ ትልቃ፣ እምዬ ማርያም፣ አሁን ደግሞ ጦቢያ፡፡ እነዚህ ሁሉእንዴት ወለዱኝ?› እንዴት እንደሚያስረዳኝ ግራ ገብቶት ዝም ብሎ ቆዬ፡፡ ወዲያ አንዲት ዶሮ ጫጩቶቿን አስከትላ ወደ ቤት ገባች፡፡
‹ጦቢያ ይች ዶሮ ነች› አለኝ፡፡ ‹አየህ ይቺ ዶሮ በአፏ እያነሳች ጫጩቶቿን ስትመግብ፤ ጦቢያ ይች ናት› አለኝ፡፡
የአያቴ ነገር ግራ አጋባኝ፡፡አንዳንዴ ከፀሐይ፣ ሌላ ጊዜ ከላም፣ ደግሞ ከእናት ጋር እያነጻጸረ ሲያወጋኝ ኖረ፡፡ ዛሬ ደሞ ዶሮ ናት ይላል እንዴ? ብዬ ተቆላጨሁ (ተበሳጨሁ)፡፡ ሽማግሌው ከርጅና የተነሳ የናላው መዘወር ተቃወሰ እንዴ? እስከመለት ደረስኩ፡፡ ደሞምይህ ሰው አገር የሚያስታርቅ፣ ያጠፋ የሚመክር፣ ያለማ የሚመርቅ፣ አገር ያከበረው አድባር ነው፡፡ እንዴት ጃጀ ይባላል? ብቻ ዘወትር ክራሩን እያነሳ ያጎራጉራል፡፡
የኮከቦች ውበት፣ የጨረቃ ድምቀት፣
(ከ… ከ… ከ… ከ… ትከተለዋለች፣ ነገረኛ ክራር)
የደመናው ግርማ የፀሐይዋ ሙቀት፣
የቡቃያው ተስፋ የዝናሙ ጥምቀት፣
የአበቦቹ ጠረን ባየር የሚናኘው፣
አንቺ ስትኖሪ ነው ትርጉም የሚያገኘው፡፡ (ከከከ…)
እንዴ ዬ… ጉድ ፈላ! ማነች ይች ሴትዮ? የአያጤ መልሶች ሁሉ አላረካህ ቢለኝ አንድ ቀን አባቴን ጠየቅሁት፡፡ ከቤታችን በላይ ሰማይ ላይ የተንጠለጠለ የሚመስለውን፣ ሌባ መስቀያ የሚባለውን ተራራ እያመለከተኝ ‹ስታድግ እዚያ ተራራ ላይ ወጥተህ ባራቱም ማዘን ስትመለከት ፍንትው ብላ ትታይሃለች› አለኝ፡፡ በአካል ብልጥ ብዬ ለረኝነት ከደረስኩ በኋላ ነው፡፡ አንድ ቀን ንፍሮዬን በኪሴ ሰንቄ ደበሎዬን ደረብኩና ፍየሎቼን እየነዳሁ ማንም ሳያጤነኝ ከሌባ መስቀያ ተራራ ላይ ወጣሁ፡፡ ከውሻዬ ከቀማው በስተቀር ማንም ከጎኔ ሳይኖር በዚያ ጥሻ እየተሱለከለኩ ያንን አቀበት ወጥቼ ከተራራው አናት መድረሴ ዛሬ ለእኔም ያስደምመኛል፡፡ በዚያን ቀን ወደ ሰማይ ባንጋጥጥ ወደ መሬት ብቧጥጥ በዕውን በራዕይም ያች ሴት አልታይህ አለችኝ፡፡ የዚያን ቀን ያተረፍኩት ነገር ቢኖር የሰማይ መጋጠሚያ የሌባ መስቀያ አለመሆኑን ማወቄ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ቀን በፊት የሰማዩ ብረት ጣሪያው እዚያ ተራራ ላይ የተገጠመ ይመስለኝ ነበር፡፡ በተረፈ ግን ጦቢያን አገኝ ብዬ ከተራራው ላይ ስንከረፈፍ ቀበሮ ሁለት ፍየሎቼን ቅርፍፍ!
ማታ ስገባ ግን አልተገረፍኩም፡፡ አባቴ ከፍየሎቹ ሁለቱ መበላታቸውን ተገንዝቦ ጨንገሩን በመመዥረጥ ሊመታኝ ሲመጣ ‹አባብዬ የዛሬን ማረኝ… ጦቢያ ልፈልግ ተሌባ መስቀያ ተራራ ወጥቼ ስቧዝን ነው የተበሉብኝ› ብዬ እርግጡን ስነግረው ልቡ እስኪፈርስ ሣቀ፡፡ ቤተ ወጣው ሁሉ ሣቀብ፡፡ አያቴ ግ አልሣቀም፡፡ ግንባሬን ሳም አድርጎ መረቀኝ!፡፡
‹አየህ ልጄ… አብርሃም የሚባል ጣድቅ ነበረ፡፡ የፈጠረውን አምላክ ለማወቅ እንዲህ እንዳንተ ዋተተ አሉ፡፡ አምላኩ አጠገቡ እያለ ከሩቁ የሚመለከታቸውን ፀሐይንም ጨረቃን እየፈተነ አምላክ አለመሆናቸውን አረጋገጠ፡፡ በመጨረሻ ግን እግዚአብሔር የልቡን ምኞት ተመልክቶ ተከሰተለት ይባላል፡፡ አነጋገረው፡፡ አንተም ጦቢያን የተፈጠርክባትን አፈር ለማግኘት በጨቅላ ልቦናህ ደከምህ፣ እሷ ግን አጠገብህ እግርህ ሥር ናት፡፡ አለኝ፡፡ ከዚያም ክራሩን…
የሰው ዘር መገኛ የሥልጣኔ ፍንጭ፣
የክብር ዘውድ ያላት የጥቁር ኩራት ምንጭ፣
ውበቷ እየሳበው ስንቱ ቢመኛትም፣
ክብሯን የገሰሰ ጦቢያ ባል የላትም፡፡
ሴቶች ወልዳ ብትድር ወንድ ጅ ብታደርስ፣
በድንግልና ነው ክብሯ ሳይገሰስ፡፡
የላይኛው ደጅ ይከፈትለትና ዛሬ አያቴ በሕይወት የለም፤ እመቃብሩ ላይ የተተከለው ዛፍ ግን ተንሰራፍቷል፡፡ እኔ ውስጥ ዘርቶ ያበቀለው የጦቢያ ፍቅር ግን ከመጫሚያ እስከ አናቴ ሥሩን ሰዶ ፣ ቅርንጫፉ እመቃብሩ ላይ ካለው ዛፍ የገዘፈ ይመስለኛል፡፡
አያቴን እስከ ዛሬ አንድ ነገር ሳልጠይቀው ክንዱን መንተራሱ ግን እስከ ዛሬ የልብ ቃር ሆኖብኛል፡፡ ከባቱ ላይ ትልቅ ጣባሳ ነበር፣ አሁን አባቴ ሲያወጋኝ በጠላት ጊዜ በጥይት ተምቶ ኖሯል፡፡ ግን አያነክስም፡፡ ያ የሚያህል ጠባሳይዞ እንዴት እንደማያነክስ መጠየቅ ነበረብኝ፡፡ ምን ዓይነት ጥብቅ አካል ቢኖረው ነው! እናንተው ይህን ሳልጠይቀው ማለፉ ግን….
አባቴ ደሞ ተራውን ለኔ ልጆች እንዲህ እያለ ሲያንጎራጉር በጆሮዬ ሰማሁ፡፡ መቼም ያልዘሩት አይበቅልም ብያችኋለሁ፡፡ ‹የዜርን ብለቅ ያንዘርዝረኝ› ይባል የለ!
የገበናዬ ቁልፍ የምሥጢሬ ሙዳይ፣
የእምነቴ ምስክር የመኖሬ ጉዳይ፤
ሐጥዕ የማይረግጥሽ የታፈርሽ መቅደስ፣
የወይዛዝርት ጌጤ የኮረዶች አደስ፤
ፍቅርሽ የሚያማልል ጠረንሽ የሚያውድ፣
ቅድስት ነሽ ጦቢያ ብርቅ ነሽ- ዕንቁ-ውድ፡፡
ካዳራሽሽ ማዕድ እንዳልተጋበዙ፣
ታዲያ ምን ያደርጋል ምቀኞችሽ በዙ፡፡
እጅሽ አመድ አፋሽ መቼስ ምን ታደርጊ፣
እስቲ ወደ እግዚሐር እጆችሽን ዘርጊ፡፡
ክፋቱ አባቴ ክራር መጫወት አያውቅበትም! እኔ ደግሞ ክራርም መጫወት ማንጎራጎርም አልችልበትም! በዳንስ ግን ማንም አይስተካከለኝም!

Please follow and like us:
error

Leave a Reply