ግብረሶዶማዊነትን ለምን እንቃወማለን?

(ካሣሁን ዓለሙ)

አንዳንድ ጊዜ የግብረ ሰዶማዊነት የዚህን ያህል አሟጋች መሆኑን ሳይና በአለማቀፍ ተቋማት ድጋፍ አግኝቶ እንዲስፋፋ ሲደረግ ስመለከትና ስሰማ ይገርመኛል፤ ግርምቴ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ይልቁንም ግብረሰዶም ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ውጭ የሆነ ተግባር መስሎ ስለሚታየኝና የሚሰጠው ጥቅም አልገለጽልህ ቢለኝ ነው፡፡ ስለዚህ የራሴን መሟገቻ ነጥቦች ላቅርብ ፈለግሁ ይህ ጽሑፍም በዚህ ዕይታ የተቃኘ ነው፡፡ መልካም ንባብ!

ለመሟገትም ‹ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሮ የሚደግፈው ድርጊት ነው ወይ?› በሚል ጥያቄ መነሣት የግድ ይላል፤ መልሱም ‹ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ ነው› የሚል ከሆነ ቢያስ መሠረታዊ መሥፈርትን ማሟላት ችሏል ማለት ይሆናል፤ ‹አይ! ግብረሰዶማዊነትማ ከሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ጠባያት ውጭ የሆነ ወይም ከስብዕና ተፈጥሮ ጋር የማይስማማ ድርጊት ነው› የሚለው ስምምነት ካገኘም ከተፈጥሯችን ውጭ ያሉ ድርጊቶችን የማከናወን መብት አለን ወይ? በድርጊቱስ የሚገኝ ኅብረተሰባዊ ጠቀሜታ ይኖራል? ጉዳትስ የለውም? ከሁለቱ ውጤቶችስ (ከጥቅሙና ጉዳቱ) የሚበልጠው የትኛው ይመስላል? የሚሉ ጥያቄዎች ፊት ለፊታችን መጥተው ያፈጣሉ፡፡ በእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ብንስማማ እነኳን ሌሎች ጥያቆዎችም መምጣታቸው አይቀርም፤ ለምሳሌ የሞራል ጥያቄዎች፣ የማኅበረሰብ ደኅንነት፣ የመንፈሳዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጉዳይና የመልካምነት ጉዳይ በቀላሉ የሚገፉ ወይም የሚተው አይሆኑም፡፡

እስቲ ከመነሻ ጥያቄያችን እንጀምርና አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት፤ ‹ግብረሶዳማዊነት ከሰዎች ተፈጥሮ ጋር ይስማማል?› የሚለው ጥያቄ ቀላል ቢመስልም ዘመን ወለድ ጥንቃቄን የሚሻ ጥያቄ መሆኑም መረዳት ይፈልጋል፤ ቀላል የሚሆነውም በልምዳችን ስንመልሰው እንጂ የተፈጥሯችንን ውስብስብ ጠባያት ሰንፈትሽና ግረሶዶማዊነት አሁን ያለበትን ደረጃ ተመልክተን ‹ለምን?› የሚል ጥያቄን ስናነሣ አስጨናቂነትን ይላበሳል፡፡ እንዲሁም በቀላሉ ከቋጨነው ምንም አታካራ አያስፈልግም፤ ማለትም ሙግቱን ‹የሰው ልጆችን ተፈጥሮ የሚቃወም ነገር ሁሉ አግባብ ስላልሆነ መቃወም ይኖርብናል፤ ስለዚህ ይህንን ከስብዕናችን ውጭ እንድንሆን የሚያደርገንን ድርጊት ማስወግደና ማጥፋት ያስፈልጋል፤ ስብዕናችንን ከማጥፋት የበለጠ ምን መጥፎ ነገር ሊመጣ? ምንም አይኖርም› ብለን መጠቅለል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ከዚህ በላይ ማየትን የሚጠይቅ ይመስላል፤ እንዲሁም በቀላሉም በዚህ መልክ ከዘጋነው የነገሩን አሳሳቢነትና ውስብስብነት ሳናስተውለው እንድንቀር ሊያደርገን ይችላል፡፡ ይልቁን በዚህ መልክ ነገሩን ከመደምደም ይልቅ ግብረሰዶማዊነት ከተፈጥሯዊ ጠባያችን ጋር በሚኖረው መስተጋብር በሚፈጥረው ነገር በመመሥረት አንዳንድ ነጥቦችን ለመመልከት እንሞክር፡፡

እንደሚታወቀው የትኛውም የተፈጥሮ ክስተት ዝም ብሎ በዘፈቀደ አልተሠራም፤ አንድ ነገር ወይም ሥራም በሥርዓትና በሕግ ነው ውበት አግኝቶ የሚስበው፣ ጥሞም ለጤናማ ሕይወት የሚጠቅመው፤ በዚያው በተሠራበት መሠረት ሲከወንነው መልካምነት የሚኖረው፡፡ የተፈጥሮ ሥርዓት ከጾታ አንጻር ካየነው ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ በሁለት እንደሚመደቡ ይታወቃል፤ መመደባቸው ብቻ አይደለም እርስበራስ እንዲሳሳቡም በተፈጥሯቸው የፍቅር ኃይል ተሠጥቷቸዋል፤ ይህም በየደረጃ የተመደበ ነው፡፡ ለምሳሌ እጽዋት ወንዴና ሴቴ ጾታቸው በተለያየ ሥፍራ ቢያድግም፤ እነሱም መንቀሳቀስ ባይችሉም፤ የሚስቡበት የነፋስ ኃይል አላቸው፤ ነፋስ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ወንዴው ተስቦ ሴቴዋም ስባ ተፈላልገው ስለሚገናኙ ሌላ ሕይወትን ለማስገኘት/ዘራቸውን ለማስቀጠል ችለዋል፡፡

ከእጽዋት አልፈን ወደ እንሳሳት ስናድግ በጾታዊ ግንኙነት የመሳሳብ ተፈጥሯቸው በጊዜና በሁኔታ ተገድቦ ግንኙነት እንዲፈጽሙም የተፈጥሮ ጠረንና ስሜት ተሰጥቷቸው በዚያው መሠረት እየተደሰቱና እየተራቡ የመኖር ግደታ አለባቸው፤ ለጫወታ ካልሆነ በስተቀር ወንድ እስሳ ወንዱን፤ ሴት አንሳሳም ሴቷን ፈልገው የመገናኘት ዝንባሌ አይታይባቸውም፤ እንዳውም ከጊዜ ገደባቸው ውጭ ‹ለካ ይህም አለ› በማለት በዝሙት ሲጠመዱ ዐይታዩም፡፡ ይህም ምን ያህል ተፈጥሮ በተፈጥሮ ኃይል የምትሳሳብና በተቃራኒ ጾታ ግንኙነት ሥርዓት የተቃኘች መሆኗን ይመሰክራል፤ የሰው ልጅ ደግሞ ከእንስሳት የበለጠም የዕውቀት ሀብት ስላለው ተፈጥረውን የመጠበቅ ኃላፊነትና ግደታ አለበት፡፡

እንዳው ይሁንና አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት በላይ ግንኙነት ቢያደርግ በተፈጥሮ ሕግ መሠረት ድርጊቱ አግባብ መሆኑን የሚደግፈው መከራከሪ ይኖረዋል፡- ሴቷም እንደዚሁ፤ ምንም እንኳን ይኸ ራሱ አሳማኝነት ቢጎድለው፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ‹ለምን አሳማኝነት ይጎድለዋል? አንድ ወንድ ከብዙ ሴቶች ጋር ወይም አንድ ሴት ከብዙ ወንዶች ጋር ግንኙነት ቢያደርግ/ብታደርግ ከብልቶቻቸው መጠንና ዓይነት አንጻር ችግር አለበት ወይ? ይህስ ማንም ከፈለገው ጋር እንዲገናኝ መፈቀዱን ዐያሳይም?› ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፤ ነገር ግን በዚህም ላይ ቢሆን ማዕቀብ እንዳለበት መረዳት ቀላል ነው፡፡

ምክንያቱም የአንድ ሰው በብዙ የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት እንደፈለገ ማድረጉ አንደኛ የመዋለድ ሕግና ሥርዓትን ይቃወማል፤ ምክንያቱም የመዋለድ ሕግ ልጅ ወልዶ ማሳደግን ይጨምራል፤ ልጅ ወልዶ ለማሳደግም አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ወይም አንዲት ሴት አንድን ወንድ ብቻ አግቦቶ/አግብታ ቤተሰብ መመሥረትን ይፈልጋል (አንዳንድ ልዩ ክስተቶችና ድርጊቶች ቢኖሩም በጠቅላላው ሕግ ይሸፈናሉ፤ ይዋጣሉ ምክንያቱም ልዩ ክስተቶች ከጠቅላላው በማፈንገጥ የሚከሰቱ ናቸው፡- ይህ የሚጠይቀው ልብ ብሎ ማስተዋልን ብቻ ነው)፡፡ ሁለተኛም የሴትና የወንድ የፍቅር ሕግ አስተሳሰብን ወጥሮ የሚያላትመው ከአንድ ሰው ጋር ነው፤ ለዚያም ነው ብዙ ሰዎች ለአንድ ሰው ብለው እራሳቸውን መስዋዕት እስከማድርግ የሚደርሱት፤ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ብዙ ወንዶች አንዲትን ሴት ወይም ብዙ ሴቶች አንድን ወንድ ወይም ‹ሁሉም እንደፈለጉ› ሆነው ማኅበረሰብ ሁሉ አሁን ባለው መልኩ በመሆን ትርጉም አይኖረውም ነበር፤ያ ሳይሆን ግን የዓለም ኅብረተሰብ ሁሉ በተለያየ የባህል ዘይቤ እየኖረ አንድ ለአንድ በመፋቀር ቤተሰብ ወደ መመሥረት ያዘነበለ ነው፡፡ ሦስተኛ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአ ያዕቆብ እንዳስተዋለው የዓለም የሴትና የወንድ ብዛት ተመጣጥኖ የሚገኝ መሆኑ አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የተፈጠረ መሆኑን ይገልጻል፤ በተፈጥሮ በዚህ መልክ ባይመጣጠን ኖሮ ሰው በተፈጥሮው አንዱ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ መወሰን አለበት ለማለት ይከብድ ነበር፤ ነገር ግን ወንድና ሴት ተመጣጥነው እየተገኙ ሁለትና ከዚያ በላይ ተቃራኒ ጾታን የሚፈልግ ከልኩ በማለፍ የተፈጥሮን ሥርዓት አፍራሽ ይሆናል፡፡ በዕውቀቱ ሥዩም በአንድ ጽሑፉ ዝሙትን እንደፈለግን እንድንፈጽም ተፈጥሮ እንደማይፈቅድልን ሲገልጽ የጾታ ብልታችን ግንባራችን ላይ ሳይሆን ጉያችን ውስጥ መወተፉ ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ስለዚህ ወንድና ሴት እንኳን ለሚያደርጉት ግንኙነት አንድ ለአንድ እንዲወሰኑ የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት ያስገድዳቸዋል፤ ከታሪክ የተገኘ ልምድም እንደፈለጉ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግን አይመሠክርም፤ ለምሳሌ አፍላጦን (ፕሌቶ) የማኅበር አኗኗርን ለማስለመድ በካምፕ ውስጥ ልጆች አባትና እናታቸውን ሳያውቁ እንዲወለዱ ለማድረግ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፤ በግርክ ምድር እውን ሆኖ ግን አልተተገበረም፤ ምክንያቶች ከሚመስሉኝ አንዱ ከተፈጥሮ ሥርዓት ጋር አለመስማማቱ ነው፡- የአባትና የእናትነትን፣ እንዲሁም የልጅነትን ትርጉም ያሳጣልና፤ ያ እውን ሆኖ በዓለም ላይም ተለምዶ ቢሆንም ልጆች ወላጆች፤ ወላጆችም ልጆች አይኖሯቸውም ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈ በግብረ ሰዶማዊያን እንደሚባለውና እንደሚደረገው ወንድ ከወንድ ጋር ወይም ሴት ከሴት ጋር የጾታ ግንኙነት አድርጋለሁ ቢል ግን ከሰዎች ብቻ ሳይሆን ከአጠቃላይ የተፈጥሮ ሥርዓት ጋር መላተም ይከሰታል፤ የሰው ልጅ ባህርያዊ ተፈጥሮና የአኗኗር ዘይቤም ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ ይህም ማለት ግብረሰዶማዊነት የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ሙሉ ለሙሉ ይቃረናል፡፡ ምክንያቱም አንደኛ የግብረሰዶማዊ ግንኙነት ምሉዕ ጾታዊ አይደለም፤ የሚከናወነው በጾታአይደለምና (ከወንድነት ወይም ከሴትነት ብልትውጭ ጾታነት አለ እንደ!)፤ ምን ማለቴ ነው ሴት ልጅ ከሴት ጋር ግንኙነት እንድትፈጽምበት የተዘጋጀ ብልት የላትም፤ ወንድም ልጅ እንደዚሁ ያለው ብልት ከወንድ ጋር ግብረ ሥጋ ሊፈጽምበት የሚችል አይደለም፤ ከወንድትና ከሴትነት ብልቶች ውጭ ያለው ደግሞ ጾታነት የለውም፤ ከጾታነት ውጭ በሆነው የጾታ ግንኙነት መፈጸም የተፈጥሮ ሕግን የጣሰ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛም እነዚህ የወንድነትና የሴትነት ጾታዎች የተሠሩበት ተግባርና ዓላማ  አላቸው፤ ተግባራቸው ሴትና ወንድ በፍቅር ተሳስበው ግንኙነት እንዲፈጽሙ ማድረግ ሲሆን ዓለማቸው ደግሞ በመዋለድ ትውልድን ማስቀጠል ነው፤ በተፈጥሮ ደግሞ ሕግና ሥርዓት የሌለውና በዚያም መሠረት የማይከናወን የለምና፤ ከዚህ ውጭ የሚከናወን የዘር ማስቀጠል ተግባር ሁሉ ፀረ-ተፈጥሮ በመሆኑ ከሥርዓት ውጭ ነው፤ ያ ማለት ከሚያመጣው ጥቅምና መልካምነት ይልቅ ጉዳቱና መጥፎነቱ ይበልጣል፤ ስለዚህ ከግብረ-ሰዶማውነት ጋር ተያያዥ የሆኑ የዘር ማስቀጠል አማራጮችና ተግባራቸው አካሄዱውም ውጤቱ በችግር የተተበተበ መሆኑን በፀረ-ተፈጥሮነቱ ብቻ መረዳት ይቻላል፡፡ ሦስተኛ ጾታ በሁለትነት ሳይበዛና ሳያንስ ወይም ጾታ አልባ ሳይኮን በተቃራኒነት ብቻ መፈጠሩና ከእነዚህ ስሜቶች ውጭ የሚፈጸሙ ግንኙነቶችም ተያያዥ ችግሮችና በሽታዎች ያሉባቸው መሆኑ የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት ሰዎችን በሴትና በወንድ የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት ብቻ እንዲወሰኑ የሚያስገድድ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ እስቲ ልብ ብለን እናስተው በአንዳንድ የተፈጥሮ መዛነፍ ከሚፈጠር ውጭ ማንም ሰው ከአንድ ጾታ በላይ አማራጭ ጾታ ኖሮት ወይም ጾታ አልባ ሆኖ የሚፈጠር የለም፤ ምናልባት ‹ጾታየን ልቀይር› ቢል እንኳን የተፈጥሮ ማዛነፍ ችግር ሰለባ ይሆናል እንጂ በተፈጥሮው እንዳገኘው ዓይነት መልካምነት አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ግብረ ሰዶማዊነት የተፈጥሮን ሕግ በቀጥታ መጣስና ሥርዓቱንም ማዛነፍ ነው፤ የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሮ ከተሰጠው ሕግና ሥርዓት ውጭ ሊሆን የሚችልበት አቅምና አግባብ የለም፤ ሁሉ ነገሩ መልካምነትና ጠቃሚነት የሚኖረው በተፈጥሮ ሥርዓት መሠረት ሲከናወን ብቻ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልብ ብለን ካስተዋልን እንስሳትም ሆኑ እጽዋት የጾታዊ ግንኙነትና የመራባት ተግባራቸውን የሚያከናውኑት በተሰጣቸው የተፈጥሮ ሥርዓት ሕጉን ጠብቀው ነው፡- ምንም እንኳን ማሰብ ባይችሉም፤ የማሰላሰል አቅም ባይኖራቸውም፤ በተፈጥሮ የተሠጣጨውን ሥርዓትን የመጠበቅን ኃላፊነት አያፈርሱም፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ድንዙዝ ከሆኑ እጽዋት፣ የማሰብ አቅማቸው ውስን ከኾነባቸው ከእንስሳት በላይ የማሰብ፣ የተፈጥሮ ሥርዓትን በአግባቡ የመገንዘብና በዚያ ሥርዓት ውስጥ መሥራትና አለመሥራት የሚገባውን ከሚያመጣው ችግር/መልካምነት እያነጻጸረ የማኅበረሰቡንና የትውልድን ቀጣነት ሁኔታ፣ የመኖርን ትርጉምና የኃላፊነትን ድርሻ ይረዳል፤ ይህ ከሆነና ግብረሰዶማዊነት እንስሳትና እጽዋት እንኳን የማይተገብሩት ተግባር ከሆነ፤ ይህንን ግብር ካልፈጸምኩ የሚልባት ምክንያት የልክፍት ሱሰኝነት ብቻ ነው የሚሆነው፤ በዚህ ተግባር በመጠመድም የአዕምሮ ጤነኝነት ይኖራል ማለት አይቻልም፤ ስለዚህ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገራት ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ ማድረግም የሰው ልጆችን የተፈጥሮ አኗኗር በቀጥታ ለማስወገድ የሚደረግ ተግባር ነው፡፡

ሁለተኛው ግብረሰዶማዊነትን የምንቃወምበት ምክንያት ከማኅበረሰባዊ ምሥረታ፣ ግንኙነትና ዕሴቶች ጋር አያይዘን ስናየው አደጋው የከፋ በመሆኑ ነው፡፡ የወንድነትና የሴትነት ብልቶች የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ብቻ አይደለም የተፈጠሩት ተያያዥ የሆኑ ማኅበራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ምክንያትም ናቸው፡፡ የወንድና ሴት ግንኙነት የመሳብ ኃይል መነሻነት ነው መልካም ቤተሰብ የሚመሠረተውና የሚሥፋፋው፤ በእነዚህ ግንኙት በመግባባት የባልና ሚስት ግንኙነት ሲዳብር ነው ወደ ኅብረተሰብና ማኅበረሰብ የሚያድገው፡፡ እውነቱን ለመናገር የዓለም ሕዝብ ተግባብቶ በመገናኘት መኖር የቻለው በጾታ ብልቶቻችን መስህብነት በፍቅር እየተጎተተ ነው፡፡ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ግን እነዚህን ሀብቶች ያጠፋል እንጂ አያዳብርም፡፡ እንዳው እንበልና ወንዱና ወንዱ በተፈጠረባቸው የዘመን/የበሽተኛነት ሱስ የተነሳ ተስማምተው ቢጋቡ ከዚያ ቀጥሎ በኅብረተሰብና በቀጣይ ትውልድ የሚያመጡት መልካምነት ምንድን ነው? ማንም ሰው በውስጡ የሚሰማው የአሉታ መልስ ነው፡፡

ግብረሰዶማዊነት የማኅበራዊ እሴቶችንና ግንባታዎችን ያዛንፋል፤ ያጠፋል፡፡ መታወቅ የሚኖርበት ያለፉ ትውልዶች በተከታታይ መጥፎውን ከጥሩው እያነጠሩ በማስወገድ፤ መልካሙ ነገር ለትውልድ በሚጠቅም መልኩ በመገንባት እንዲገለገሉበት አድርገው ለእኛ አስረክበውናል፤ ይህም ካወቅነው ትልቅ ሀብት ነው፤ ምናልባት ‹እነ ሁሉን ዐወቅና የዐዲስ ነገር ዘማዊያን› ያለፉ ትውልዶች ያወረሱን የሥነምግባርና የማኅበረሰብ እሴቶች ኋላ ቀር እንደሆኑ ቢሰብኩንም፤ ካስተዋልናቸው ትልቅ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ያለፉ ትውልዶች ያለፉበትና ያስረከቡን የዕውቀት፣ የሥነምግባርና የባህል ዕሴቶች ናቸው፡፡ ልብ ካልን(አንዳንድ ከልማዶች የተነሣ የተከሰቱና ያሉ ችግሮች ቢኖሩም) መሠረታዊ የተፈጥሮ ሥርዓትን የመጠበቅ ዝንባሌያቸውና የማኅበረሰብ ጠቀሜታቸው የላቀ በሥርዓት የተሠሩ ዕሴቶች አሉን፤ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ በኩል በጣም ዕድለኞች ነን፡፡ እስቲ እናስተውል የሥነ ምግባር ዕሴቶቻችን፣ የባህላዊ ሕግና ሥርዓት አጠባበቃችን፣ ለመኖራችን የምንሠጠው ትርጉምና አጠቃላይ አኗኗራችን በመልካምነት የተቃኘ፣ በሥነምግባር የተጠበበ፣ ለምንፈጽመው ድርጊት ሰውን የምናፍር እጊዜርን የምንፈራ (በፈለግነውም ብናምን)፣ ነግበኔን የምናውቅና የምንጠብቅ ሕዝቦች ነን፤ ይህ ሁሉ የማኅበረሰብ ሀብት ነው፡፡ ግብረሶዶማነት ግን ይህን የተገነባ የማኅበረሰብ ሥርዓት ከሥሩ ቆርጦ ነው የሚጥለው፤ እንዴት?

አንድኛ ኅበረተሰብ የሚገነባው ከቤተሰብ ምሥረታ ነው፤ ግብረሰዶማዊነት ቤተሰብ የመመሥረት ሥርዓትን ያጠፋል፤ በዚህ የተነሣም የማኅበረሰባችንን ዕሴቶች ለቀጣይ ትውልድ የማውረስና የማስቀጠል ኃላፊነት አናገኝም፤ ምናልባት ወንድ ለወንድ፣ ሴት ለሴት በመጋባት መዋለድ ይቻላል የሚል ካለ ያስረዳን፤ መከራከሪችንን እናስተካክላለን፤ በእውነታው ግን ስለሌለ ግብረሰዶማዊነት ማኅበረሰብን በጣሽ ነው ማለታችን ትክክል ነው፡፡ ሁለተኛም ዕሴቶቻችን የተገነቡት በሴትና በወንድ የጾታ ግንኙነት አስተሳሰብ ነው፤ በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አስተሳሰብ ሲቃኙ ግን ዕሴቶቹ ትርጉም ያጣሉ፤ በመጥፎ ባህልነትም ሊፈርጁ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ የወረሱትን ሀብት በእሳት ማቃጠል ነው (ሞኝ ልጅ!)፤ ዕሴቶቻችን በመጥፎነት ሲፈረጁም አባቶቻችንና እናቶቻችን በእኛ ላይ መጥፎ ነገር እንደጫኑብን አድርጎ መፈርጀ ይከሰታል፤ ይህ ግን አግባብ አይሆንም፡፡ ሦስተኛ የግብረሶዶማዊነት ተግባር አግባብ/ትክክል ከሆነ ሌሎች መጥፎ የምንላቸው ነገሮችና ድርጊቶች ከግብረሰዶማዊነት በልጠው እንዴት መጥፎ ሊሆኑ ይችላሉ? ለምሳሌ አንድ ሰው ከፈለገው ጋር በአደባባይ እንደፈለገ ጾታዊ ግንኙነት ቢያደርግ ለምን መጥፎ ሊባል ይችላል? ከቤተሰብ ጋርና በማኅበር የዝሙት ግንኙነት ማድረግስ መጥፎ ነው ልንል የምንችልበት የሞራል አቅምስ ከምን ልናገኝ እንችላለን? እንዴትስ ግብረሰዶማዊነትን በአግባብነቱ ተቀብለን ከተቃራኒ ጾታ የሚፈጸሙ የዝሙት ግብሮች በመጥፎነት ልንፈርጅ እንችላለን? ግብረሰዶማዊነት መጥፎ የሚሆነው ከሁለት ሰዎች በላይ ግንኙነት ሲፈጽሙ  ነው ልንል ነው ወይስ በተመሳሳይ ጾታ የሚደረግ ግንኙነት ያለ ገደብ ከፈለጉት ሰው ጋር ሁሉ መፈጸም ይቻላል በማለት ልንሟገት ነው? (አውጣን!)…፡፡እነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ አግባባዊ መልስን ይፈልጋሉ፤ በቀላሉም እንዳንመልሳቸው መልሱ የበለጠ ጥያቄን እየጎለጎለ ይወሳሰባል እንጂ አይቋጭም፡፡ ስለዚህ ግብረሰዶማዊነት በመልካምነት ከተወሰደ እነዚያ ያልናቸውና የምንጠቀምባቸው የሥነምግባርና የማኅበረሰብ ዕሴቶቻችን ትርጉማቸው ይጠፋል፣ አገልግሎታቸው ይዛነፋል (እነ ይሉኝታ፣ ነግበኔ፣ ሰውን ማፈር፣ እጊዜርን መፍራት … ወደ ቆሻሻ ገንዳ ይጣላሉ)፤ በአጠቃላይ ትውልዱ ዐዲስና ልዩ ማኅበረሰብ መሥርቶ ለመገንባት ይገደዳል፡- ከቻለ፤ የትውልድ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚሆን ታሳቢ ሆኖ፡፡

ሦስተኛው ግብረሰዶማዊነትን የምንቃወምበት ምክንያት ከሃይማኖት ዕሴቶቻችንና ሥነምግባሮቻችን ጋር ስለማይስማማ ነው፡፡ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያ አብዛኞቹ ባህላዊ ዕሤቶችቻን ሃይማኖትን መሠረት የሚያደርጉ ናቸው፤በሃይማኖት መጽሐፎቻች ደግሞ የግብረሰዶማዊነት መጥፎነቱ እንጂ መልካምነቱ አልተጠቀሰም፤ አልተነገረም፡፡ ስሙን ራሱ ‹የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት› ከማለት ይልቅ ‹ግብረሰዶም› የተባለው የሰዶም ሰዎች ይፈጽሙት የነበረ ግብር ስለነበርና እነሱንም እግዚአብሔር ተቆጥቶ በእሳት እንዳጠፋቸው ስለምናውቅ ነው፤ በዚህ ድርጊት ያልተባበረውን ሎጥን ግን ከዚያ መአት እንዳዳነው ስለተነገረን ነው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት አለን የምን ከሆነ፣ በሃይማኖታችንም ይህ ድርጊት የተከለከለና ጥፋትን ያስከተለ ከሆነ ግብረሰዶምን የምናከብርበት፣ ድርጊቱንም ሳንቃወም ዝም የምንልበት ምክንያት የለም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የሃይማነተኞች ሀገር እንጂ ሃይማኖት አልበኞች የሚፈነጩባት አይደለችም (ይህ ራሱን የቻለ ሌላ አጨቃጫ ርእስ ስለሆነ እንለፈው)፤ ስለዚህ የሃይማኖታችንን ዕሴቶችና ሀገራችንን ለመጠበቅ ስንል ግብረሰዶማዊነትን እንቃወማለን፡፡

በአጠቃላይ ግብረሰዶማዊነት የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓትን ስለሚጥስ፣ ማኅበራዊ ዕሤቶቻችን ትርጉም ስለሚያጠፋና ፀረ-ሃይማኖት ድርጊት ስለሆነ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ ሥፍራ እንደሰው መስፋፋቱን ልንቃወመው እንጂ ልንደግፈው ወይም ‹ምን አገባን ብለን› ዝም ልንለው አይገባም፡፡ አሁን የሚሆነው ጥያቄ ‹ግብረሰዶማዊነት ከሰው ልጆች ተፈጥሮ፣ ከማኅበረሰብ ዕሴቶችና ከሃይማኖታዊ ትዛዛት ጋር የማይስማማ ተግባር ከሆነ ለምንና እንዴት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኃያላን መንግሥታት ተቀባይነት ሊያገኝና ለታዳጊ ሃገራት ደግሞ የዕርዳታ ለማግኘት እሱ እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊወሰድ ቻለ? ኃያላኖቹ መጥፎ ድርጊትን መቃወምና የሚቃወሙትንም መደገፍ ይገባቸዋል እንጂ በተቃራኒው እንዴት ይህን ያደርጋሉ?› በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ተግባር ሱሰኛና ምርኮኛ የሆኑትስ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ባለማወቅ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት? የሚጠቅም ካልሆነስ ለመተው ከመጣር ይልቅ እንዴት ድርጊቱን ለማስፋፋት ይተባበራሉ?የሚሉ ጥያቄዎችመነሣታቸው አይቀርም፡፡

መልሱን ለመስጠትም የግድ መከራከሪያችን ትክክል መሆኑን መመልከትና ምክንያታቸውንም መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መከራከሪያዎቻችንም ግልጽ ናቸው፤ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ሥርዓት ይቃወማል ብለናል፤ አለመቃወሙን በተጠየቅ አቅርቦ የሚያሳምነን እስከምናገኝ ድረስ ከላይ እንዳስቀመጥነው ትክክል ስለሆንን ግብረሰዶማዊነት ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፤ በባህርያችን ተወስኖ የተሰጠንን የተፈጥሮ ገደብና ተግባር አልፎ መሄድ ይቻላል ከተባለም፤ መከራከሪያቸው ከሰው ልጅ ስብዕና ውጭ መሆን መቻልን ስለሚገልፅ ከሰውነት ወይም ሰው መኖር ከሚችለው በላይ ሄደው ይኑሩ እንጂ የእኛን መብት አይጻረሩ እንላለን፡፡ ከድርጊቱና ከሚያመጣው ውጤት ተነሥተን ስንገመግመው የምንረዳው ማኅበረሰባዊ ዕሴቶችን ስለሚያጠፋ ግብረሰዶም አደገኛና ጠንቀኛ ተግባር ነው ብለናል፤ ይህንን የሚያፈርስ መከራከሪያ ሲያቀርቡ ደግሞ አይታዩም ይልቁንም ‹ሰው በተሰጠው ገላው እንደፈለገ የመሆንና የማድረግ መብት አለው› ነው የሚሉት፤ ነገር ግን  መታወቅ የሚኖርበት አንደኛ ግብረሰዶማዊነት የአንድ ሰው ድርጊት ብቻ አይደለም፡- ከሌላ ሰው ጋር የሚፈጸም ድርጊት ነው፡- ይህም ወደ ቤተሰባዊነትና ማኅበረሰባዊነት ያድጋል፤ ሁለተኛ መከራከሪያው በአንድ ሰው መብት ተጠግቶ ማኅበረሰብን የመረፍረፍና የማጥፋት ግብ ያለው ይመስላል፤ ነገር ግን አንድ ሰው ያለ ኅብረተሰብ አይፈጠርም፤ ኅብረተሰብና ማኅበረሰብም ያለ ግለሰቦች ድምር አይኖሩም፤ ስለዚህ ግብረሰዶማዊነት ማኅበረሰባዊነትን የሚንድና የሚያጠፋ ከሆነ፤ ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት ያለበት ሁሉ በአንድ ሰው መጥፎ ድርጊት እንዳይጠፋ የመጠበቅ ኃላፊነት ይኖርበታል፤ ደግሞስ ድርጊቱን የሚፈጽመው አካል መብት ከተከበረለት ‹ይህ ድርጊት ለእኔ በኅበረተሰቤ፣ በሃይማኖቴና በሥነልቦናዬ ላይ ችግር ይፈጥርብኛል› የሚለው የብዙዎች መብትስ አይታይም ወይ? ኅበረተሰቡ እኮ በግብረሰዶማዊነት ባህል ሳይሆን በተቃራኒው የተገነባ ነው፤ ይህ ከሆነ ግበረሰዶማዊነትን የሚያስፋፋው አካል ለምን የሌላውን ሀብት ለማጥፋት መብት ያገኛል?ሃይሞኖት እኮ የግበረሰዶማዊነት ተቃራኒው እንጂ ተባባሪው አይደለም ታዲያ ለምን ሃይማኖት የገነባውን ማኅበራዊ ተቋም ለማፍረስ ግብረሰዶማዊነት መብት ያገኛል? የማኅብረሰቡ ሥነልቦና ግብረሰዶማዊነት የሚቀፈው ከሆነ እንዴት ግድ ተባበር ተብሎ የማይፈልገው ነገር ይጫንበታል? ስለዚህ ከላይ የጠቀስናቸውን መከራከሪያዎች የሚያፈርስ መከራከሪያ አያቀርቡም፤ ይህ ከሆነም መቃወማችን ትክክል ነው፡፡ ሆኖም ‹ለምን ይህን ያደርጋሉ?› የሚለው ጥያቄ ግን አልተመለሰም፤ ጥያቄውን በአግባቡ ለመመለስም አስቸጋሪ ይመስላል፤ ስለዚህ በመጠርጠር የተመሠረተ መላምት ለመስጠት እንገደዳለን፡፡ እንጠርጥር!

አንደኛው ጥርጣሪያችን ‹በዓለም የተለየ እኛ የማነውቀው የሻጥር (የሤራ) ዕቅድ ይኖራቸው ይሆን?› ብለን ለመጠየቅ ያስገድደናል፡፡ ይህን ስንጠይቅ ደግሞ ከጥርጣሪያችን ጋር የተያያዙ የምሥጢር ማኅበራት ዓላማ፣ ዕቅዳቸውና ዓለም የመቆጣጠሪያ ስልቶቻቸው ለጥርጣሪያችን አጋዥ በመሆን ይመጣሉ፡፡ የምሥጢር ማኅበራቱ ዕቅድና የዓለም መቆጣጠሪያ ስልቶች ውስጥ ደግሞ አንዱ የአንድን ማኅበረሰብ ጠንካራ ዕሴቶች ማፍረስና እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ውስጥ ማስገባት ዋናው መሆኑን ስናይና ስንረዳ ጥርጣሪያችን ይጨምራል፤ በተለይ ደግሞ ጠንካራ ዕሴቶችን ለማፍረስ ሃይማኖትን ማረካስና ማጥፋት፣ ከዚያም የራሳቸውን በመተካት በዐዲስ መልክ መገንባት መሆኑን ስንመረምር መጠርጠራችን ትክክል ነው እንላለን፤ ለዚህም ከሚያገለግሉት የዕሴቶች ማፍረሻ መዶሻዎች (ለምሳሌ የሕዝብ ብዛት ቅነሳ፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋችነት፣ የሃይማኖት አይጠቅሜነትና ትርጉም አልባነት፣…) መካከል አንዱ ግብረሰዶማዊነት መሆኑን ስንረዳ ‹ታዲያ በግብራቸው እየነገሩን አይደለም ወይ?› ማለታችን ስህተት አይሆንም፡፡ ስህተት የሚሆነው እንዳውም አለመጠርጠራችን ይሆናል፡፡ ያ ካልሆነ ለምን ከሰው ልጆች ስብእና ውጭ ለሆነ ነገር ገንዘብ መድበው፣ ኃይላቸውን ተጠቅመው ጥብቅና ይቆማሉ? እንዳውም እንዲስፋፋና ዓለምን እንዲቆጣጠር በትጋት ቆርጠው ይሠራሉ? ስለዚህ ሻጥር እንዳለባቸው መጠርጠራችን ካለመጠርጠራችን የተሻለ መልስ ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ‹ከግብረሰዶማዊነትና ከአሸባሪነት የትኛው የባሰ መጥፎ ሆኖ ነው አሸባሪነትን በዓለም ላይ ለመቆጣጠርና ለማጥፋ ሌት ተቀን እንሠራለን እያሉ ግብረሰዶማዊነትን ግን በጀት መድበው የሚያስፋፉት?› እናስ ‹የሆነ ሻጥር› እንዳለባቸው መጠርጠራችን አይሻልም፡፡ ባይሆን የጥርጣሬ መከራከሪያችን ካለረካ የግደይ ገ/ኪዳንና የተክሉ አስኳሉን ‹ህልም አጨናጋፊዎቹ› የሚለውን መጽሐፍ መመልከት ወይም ‹ሉላዊ ሤራ› የሚለውን የግደይን ጦማር (ብሎግ) መጎብኘት፤ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆኑናል በሚል ጥቁምታ ወደ ሁለተኛው የጥርጣሬ መልሳችን እንለፍ፡፡

ሁለተኛው ጥርጣሬያችን ሊሆን የሚችለው ‹ምናልባት የሠይጣን እጅ ይኖርበት ይሆን እንዴ?› የሚል የሃይማኖታዊ ሰው ፍርሃት ነው፤ ምክንያቱም አንደኛ ‹ግብረ ሰዶማዊነት የሃይማኖት ዕሴቶችን ይቃረናል (ይቃወማል) ባልነው መሠረት፤ ሠይጣን ደግሞ በሃይማኖት ጋር ከሚገናኘው እግዚአብሔር ጋር ፀበኛ ስለሆነና የሰውና የአምላክን ግንኙነት ለመበጠስ ስለማይተኛ በእነዚህ ኃያላን መንግሥታት ላይ አድሮ እየተቆጣጠረ ዓለም እያጠፋ ይሆን ወይ?› የሚል ጥርጣሬ ስለሚያሳድርብን ነው፤ ሁለተኛም ከላይ ከጠቀስናቸው ከምሥጢር ማኅበራት ጋር ተያይዞ ‹ዓለምን በሠይጣን ሃይማኖት ለማስገዛት እንቅስቃሴ አለ፤ ለዚህም የተወሰኑ ሰዎች የዓለምን ተቋማት፣ ሚዲያዎች፣ ትምህርትና ሌሎች ነገሮችን በመቆጣጠር ሠይጣን የሚመለክበት ሥርዓት ተነድፎ ይተገበራል፤ ለዚህም አንዱ የግብረሰዶማዊነት ተግባር ነው› የሚል ሐሜት ስለሰማን እንጠረጥራለን፡፡ እንዲሁም 666 የሚባለው የሠይጣን ምልክትና እሱንም ለማስፋፋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ስለምንመለከት ጥርጣሬያችን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ ለጥርጣሬያችን አጋዥ የሆነን ደግሞ የጠቀስናቸው ‹ኃያላን መንግሥታት› የዓለምን ሀብት፣ የጦር አቅምና የዕውቀት አውታር ተቆጣጥርው ‹ይህንን ተግባር ካላስፈጸማችሁ ሽራፊ ሣንቲም ወይ ቅምሽ!› ማለታቸው ነው፤ እና ካለመጠርጠራችን መጠርጠራችን አይሻልም እንደ?

ሦስተኛም በአፍሪካዊነታችንና በጥቁርነታችን የምንጠርጥራቸው ግምቶችም ይኖሩናል፤ ይህም ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ይህን ተግባር እንድንቀበል ተጽዕኖ የሚያደርጉብን አካላትና የሚቆጣጠሯቸው፤ አፍሪካን ማዳከምና ጥቁር ሕዝብ እየተርመጠመጠ እርስ በራሱ እየተባላ እንዲኖር፤ በዚህም የሞራል መላሸቅና የስብእና መበላሸት እንዲፈጠርበት እንጂ በራሱ ቀና ብሎ ሞራሉን በመገንባት መበልፀጉን የማይፈልጉ አካላት ያሉባቸው መሆኑን ከታሪክና ከሚታዩ የተጽዕኖ አዝማሚያዎች ስለምንረዳ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ለምን በተለየ በአፍሪካ በብድርና በዕርዳታ ስም በማስፈራራት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችም ግብረሰዶምን ለማስፋፋት ዕንቅልፍ አጥተው ይሠራሉ? በተለይ የታላላቅ ፈላስፋዎቻቸው (ዓማኑኤል ካንትንና የሔግልን የመሳሰሉ) የ‹ጥቁር ሙሉ ሰው አይደለም› አስተሳሰብ በአንዳንድ ነጮች ላይ የፈጠረውን ተፅእኖ የሚያስተውል በሞኝነት በባዶ እጁ ‹እሳት እየተጫወተ ተቃጥሎ› ማሰብ አለመቻሉን መመስከር የለበትም፤ ይህ ከሆነም በዚህ መልክም ቢሆን መጠርጠራችን አይከፋም፡፡ ያ ካልሆነ እንዴት ግብረሰዶምን በአፍሪካ ለማስፋፋት በጀት መድበው በማማለል እንቢ ስንል ያስፈራሩናል? ሁልጊዜ ‹የእነሱ የሠገራ ቤት መሆን አለብን እንዴ? › በአጠቃላይ ካለመጠርጠራን መጠርጠራን ሳይሻል አይቀርም በሚል መልሳችን እንዝጋው፡፡ ለዚህም ቢሆን ዶክተር ሥዩም አንቶኒዮስ Africa say no for Homosexuality በሚል ያቀረቡትን ዶክመንተሪ ፊልም ከእንተርኔት ላይ መመልከት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ይህንን በዚህ መልክ ጠርጥረን ብንዘጋም ሌላው ጥያቄ ግን አፍጦ ይጠብቀናል፡- ከላይ የጠየቅነው ‹ለግብረሶዶማዊነት ተግባር ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች ጉዳይስ? ለምን ግብራቸውን ከመተው ይልቅ ለማስፋፋት ይጥራሉ? ያለማወቅ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አላቸው?› የሚሉት ጥያቄዎች መልስ አምጡ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ማለትም ‹ግብረሰዶማዊነት ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የማይስማማ ከሆነ፣ በዚህ ተግባር የተሠማሩ ሰዎች እንዴት ተስማምቷቸው ድርጊቱን ከመተውና መጥፎነቱን ከማስረዳት ይልቅ ተግባሩ እንዲስፋፋ ምክንያት ይሆናሉ?› መባሉ የማይቀር ነው፤ መልሱም አስቸጋሪነት ይታይበታል፡፡ በግብረሰዶም መጥፎ ግብርነትና ለሰው ተፈጥሯዊ ባህርይ ተቃራኒ በመሆኑ ከተስማማን ግብሩን መተው አለባቸው ማለታችን ትክክል ይሆናል፤ ከሰውነት ውጭ የሆነ ሥራን መሥራት መልካም አይደለምና፡፡ ለመተው እንዲችሉም ይህንን ተግባር እንዳይተው ምክንያት የሆኗቸው፣ እንዳውም ድርጊቱን እንደመልካም ነገር ለማስፋፋትና ተቀባይነት እንዲያገኝ መሥዋዕትነት ለመክፈል የሚጥሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ምክንያት ከሚመስሉን መካከል ማሰያ የሚሆኑ ነጥቦችን እንጥቀስ፡፡

አንደኛ እነዚህ ሰዎች ወደውት በመፈለግ የገቡበት ተግባር አይደለም፤ አንድም ሳያውቁ በመታለል፣ በመደፈር፣ በገንዘብና በተለያዩ ምክንያቶች በመደለል ነገሩን ለጊዘው ብንፈጽም ምንም አይደል በሚል ሞኝነት ጀምረውት ከዚያም እንደልማድ ስለሆነባቸው ነው ለዚህ የበቁት፤ ከዚያም ተለማምደውት መልካም ተግባር መስሎ እስከመታየት አድርሷቸዋል፤ አስከፊነቱና የሚያመጣው ተጽዕኖ አልተገለጠላቸውም፡፡ ስለዚህ እንደሌላው ወይም እንደተቃራኒ ጾታ ግንኙነት መስሎ ስለሚሰማቸው የሚያመጣው አስከፊ ገፅታ አልተስተዋላቸውም፤ እንዳውም ‹ከአፈርኩ አይመልሰኝ› በማለት መብታቸው እንደሆነ እስከመቁጠር ደርሰዋል፤ ሌሎችም ሲያጣጥሏቸው ‹መብታችን› በሚለው ሰበብ እራሳቸውን ለመከላከል ይጥራሉ፤ አዕምሯቸው እንደሚወቅሳቸው ግን ከተሠሩ አንዳንድ ‹ዶክመንተሪ› ሥራዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ሌላው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ሰለባ የሚያደርጓቸው አካላት ተፅዕኖ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይህንን ተግባር ለማስፋፋት በገንዘብና በሌሎች መሣሪያዎች ተፅእኖ ያደርጋሉ ካልን እጃቸውን በእነዚህ በተጠቂ ሰዎች ጀርባ ደብቀው ተግባሩ እንዲበረታታና እንዲስፋፋ አያፋፍሙም ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ስለሚሉ እንሱ የሚያራምዱት ነገር ሁሉ መልካም ሊመስላቸው ይችላል፡- የተለከፉት ሰዎች፤ በዚህ የተነሣ ‹ማንኛውም ሰው በገላው እንደፈለገው ማዘዝና መሆን ይችላል› የሚለው ስብከት ችግር የሌለበትና አግባባዊ መከራከሪያ ሊመስላቸው ይችላል፤ ይህም ማለት እነሱ ሱስ የሆነባቸውን ነገር መፈጸማቸውን እንጂ ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚመጠው ችግር አይገለጽላቸውም፡፡ እንዲሁም ከዘመኑ የአኗኗር ሁኔታና ተፅእኖ አንጻር ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን በእነሱ በኩል የሚያገኙበትን መንገድ ስለሚያመቻቹላቸው፤ መጥፎ መሆኑን ቢያውቁና ተግባራቸው ቢያስዝናቸውም ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ በእንደዚህ ዓይነት ተግባር ውስጥ ሊሠማሩ ይችላሉ፤ ይህንን ከሴተኛ አዳሪዎች ሕይወት ጋር አያይዞም መገንዘብ መልካም ነው፡፡ እንዲሁም ተጽዕኖ የሚያደርጉ አካላት እጃቸው ሰፊና መረባቸው ብዙ ነው፤ በመሆኑም ሚዲያውን ተቆጣጥረው፣ ምሁራንን ተጠቅመው የሚያደርጉት ስብከት ‹ጥቁሩን ነጭ ነው፤ ነጭንም ጥቁር ነው› በማለት የማሳመን ኃይል አለው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎችንም ሰለባቸው ካደረጓቸው በኋላ በተለያየ ስልት በመጠቀም ተግባሩን እንዲስያስፋፉ ያድርጋሉ እንጂ በቀላሉ አይተዋቸውም፤ እንዲሁም በሠለጠኑ ሀገራት የተግባሩን መፈጸም እንደ ጀብዱ አድርገው በመውሰድና ያንንም በማራገብ ‹እነሱ ይህንን የሚያደርጉት ችግር ባይኖርበት ነው› የሚል አስተሳሰብ በውስጣቸው እንዲሰርፅ አድርገው የቀረጽዋቸው ይመስላሉ፡፡ በአጠቃላይ የግብረሶዶም ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ብዙ ተጽዕኖዎች እንደሚኖሩባቸው ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

እነዲሁም ግብረሰዶማዊነት ሠይጣናዊ የሆነ ልክፍት አይኖርበትም በማለት መደምደም አይቻልም፤ ከላይ ‹ግብረሶዶምን በዓለም ላይ እንዲስፋፋ እያደረገው ያለው ሠይጣን ነው› ባልነው መሠረት፤ ድርጊቱን በማስፋፋት ሥራ ሠይጣን እጁ አለበት ማለት ነው፤ ይህ ከሆነም ‹በእዚህ ተግባር የተጠቁ ሰዎች በሱሰኝነት ተግባር እንዲጠሙዱና አገልጋዮቹ እንዲሆኑት አያደርጋቸውም› ልንል አንችልም፤ ይህ ከሆነም እነዚህ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ አካል (ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁት) ስለሚቆጣጠራቸውና ከእግዚአብሔር ስለሚለያቸው እሱን ለማስደሰትና የሰው ልጆችን ለማጥፋት ይሠራሉ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ከመንፈሳዊ አስተምህሮ አንጻር ከተመለከትነው አበው ሰባቱ ዐበይት ሐጢያት ከሚሏቸው አንዱ የ‹ግብረሰዶም መስፋፋት› ነውና በትንቢት መልክ የተገለፀው በእውን እየተተገበረ መሆኑን ይመሰክራል፤ ይህም ምን ያህል አስቸጋሪ ወቅት ላይ እንደሆንን ያስረዳናል፡፡ የሠይጣን ሥራን ደግሞ መቃወም ግድ ይለናል (ሰዎቹን አይደለም ተግባሩን ነው ያልኩት)፤ ሠይጣን እንደመሣሪያ የሚጠቀምበት ግብረሰዶማዊነት የመልካም ነገርና የሰው ልጆች ጠላት ነውና፡፡

በአጠቃላይ የዚህ ድርጊት አራማጆቸ  ወደውም ይሁን ሳይወዱ ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የተነሣ ተግባሩን እንደሱስ ለምደውት ሊያስፋፉት ይችላሉ፤ በተጽእኖ የተነሣም የድርጊቱ ተባባሪና ፈጻሚ ሆነው ሊሆን ይችላል፤ በሠይጣን ልክፍትና ቁጥጥርም የድርጊቱ አከናዋኝ ለመሆን ተገደው ይሆናል ወይም ሌሎች ችግሮችም (ምክንያቶችም) ሊኖሯቸው ይችላሉ፡፡ በማንኛውም ምክንያት ያከናወኑት ምንም ዓይነት ችግር ይኑርባቸው ድርጊቱን ማስፋፋታቸው አደገኛ መሆኑን ግን ዐሌ ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም ግብረሰዶማዊነት መጥፎ ድርጊትና የስብዕና ተቃራኒ ተግባር ነውና፡፡ ስለዚህ የችግር መዓት መደርደራችንን ትተን፤ ተጠቂዎቹን መውቀሳችንን አቀዝቅዘን ‹‰ረ! ምን ይሻላል?› ማለት ይኖርብናል፤ ዋናው ቁም ነገር ችግሩን ማስወገዱ እንጂ በችግሩ ላይ ማለዛን አይደለም፡፡ እናም ‹ለዚህ ችግር መፍትሔው ምንድን ነው?› ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል፤ መፍትሔው ደግሞ ከችግሩ እንደሚነሳ ግልፅ ነው፡፡

ከችግሩ በመነሣት ልብ ብለን ካስተዋልነው የ‹ግብረሰዶማዊነት ወረራ› ከቅኝ ግዛት ይበሳል እንጂ የተሻለ አይደለም፤ ምክንያቱም ሀገርን ወሮ በመንጠቅ ብቻ የሚመለስ አይደለም ይልቁንም የትውልድን መንፈስ መጦ በማውጣት የሰው ልጅን ማንነትና የትውልድን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ስለዚህ ‹ሳይቃጠል በቅጠል!› ማለት እዚህ ላይ ነው፤ ትውልዱን ለመጠበቅ፣ ሀገርን ከዚህ ጥፋት ለመታደግም ‹ጦርነት› ሊታወጅበት ይገባል፤ ያለበለዚያ ችግሩ ተቆጣጥሮን ልጆች እንዳያሳጣን፣ በሀገራችን ተንሠራፍቶ መንቀሻቀሻ እንዳናጣ ያሰጋል፤ ለዚህ ለዚህማ የመውለድ ትርጉሙስ ምን ሊሆን ነው? ስለዚህ ግብረሰዶማውነትን እንደቀላል ነገር እንዳናየው፤ ‹ልጆቻችንን አስጨርሰንም› በጸጸት እያለቀስን እንዳንሞት ከአሁኑ ማጤን ይኖርብናል፡፡

እንደሰማሁነት ከሆነ ግብረሰዶማውያ በሀገራችን የሕግ ድጋፍ እንዲሠጣቸውም ጠይቀዋል ይባላል፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ላይ ‹ጋብቻ ሁለት ወንድና ሴት የሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚፈጽሙት ተግባር ነው› (በቀጥታ የተጠቀሰ አይደለም) የሚለውን አንቀጽ ‹ሁለት ሰዎች በፈቃደኝነት ሚፈጽሙት ተግባር ነው› በሚል ይስተካከል ብለው ጠይቀዋል ተብሏል፤ ይህም ምን ያህል ስልታዊ እንደሆኑ ያሳየናል፡፡ ስለዚህ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በሕግ ማዕቀፍ ተደግፈው በአደባባይ ወጥተው እንዳይቆጣጠሩን እያንዳንዷን እንቅስቃሴቻውን ቢቻል እንዳያከናውኑ ማድረግ፤ ከልተቻለም ተቃውመን ለማስቀረት መሞከር ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጓደኛየ ስለዚህ ጉዳይ ስናወራ ስጋቱን ሲገልጽልኝ ‹ከዐሥር ዓመት በኋላ በሕገ-መንግሥት የተደገፈ መብት እንዳይኖራው ያሰጋል› ብሎኛል፤ ስጋቱ እንደማይደርስ ማረጋገጫ የለንም፡፡ ስለዚህ በሕግ ተደግፈው እንዳይቆጣጠሩን አስፈላጊውን ጥንቃቄና ክትትል ማድረግ ያስፈልገናል፤ በተለይ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ጉዳዩ በቀላሉ የመብት መጠበቅና የዕርዳታ ማግኛ ስልት አድርገው በንዝህላልነት እንዳያሰወሩሩን መጠንቀቅ አለባቸው፡፡

በግልፅም ይሁን በስውር በዕርዳታና በመያዶች ስም የሚከናወኑ ተግባራትንም ማየት ያስፈልጋል፤ በተለይ በሀገራችን ግብረሰዶማዊነት የሚስፋፋው አንድም በዕርዳታና በብድር ስም ገንዘብ ለማግኘት ሲባል በሚፈጠር ተፅዕኖ ነው፤ ሌላም በትምህርትና በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ውጭ ወጥተው የሚመለሱ ሰዎች የድርጊቱ ሰለባ ሆነው ስለሚመጡ በሱስኝነት ድርጊቱን ስለሚቀጥሉበት ነው፤ አንድም ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ተያይዞ በመመሳሰል በሚፈጠር የማታለልና ተመሳሳይ ጾታን የመድፈር፣ የማስለመድና የማስፋፋት እንቀስቃሴ ነው፤ ወይም ለዚህ ድርጊት ማስፋፊያ በጀት የመደቡ አካላት በሚነድፉት የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡ በየትኛውም ይሁን ወይም ሌላ መንገድ ይኑራቸው የእኛ ዋናው ጥያቄ ‹እንዴት እንቆጣጠረው?› የሚል ነው መሆን ያለበት፤ በተለይ ደግሞ የሀገራችን ድህነት በመጠቀም ዕርዳታ እንስጣችሁ በሚል ሰበብ መያዶችን እያደራጁ ለቀውብናል ወደፊት ይብሳል እንጂ መቀነሱ ያጠራጥራል፤ በዕርዳታና በብድር ስምም መንግሥትን አፉን ሊዘጉት ይሞክራሉ እንጂ ዝም አይሉም፤ ከአሁን በፊትም ይህንን እንዳደረጉ ባለፈው የሃይማኖት አባቶች ለመቃወም ሊያደርጉ የነበረውን ስብሰባ በማገድ ተንፀባርቋል፡፡ ስለዚህ ‹በእዚህ በኩል ያሉትን የማነቂያ ስልቶች እንዴት ልንቋቋማቸው እንችላለን?› ብለን ራሳችንን መጠየቅ ግድ ይለናል፤ በዚህ በኩል የሚመጡ ዕርዳታዎችንና የብድር መደራደሪያዎችን ‹በአፍንጫችን ይውጣ!› ብለን መቃወም ይኖርብናል፡፡ ለዚህ የዚህ ጉዳይ አሳሳቢነት የሚሰማቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ያስፈልጉናል፤ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የመንግሥት ኃላፊዎች ያላቸው ጠንካራ አቋም ወሳኝ ይሆናል፡፡

ሌላውና ዋናው የችግሩን አሳሳቢነትና በሀገራችን የሚያመጣውን ችግር በመነጋገርና በመከራከር ለኅበረተሰባችን ማሳወቅ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ በአግባቡ ከተሔደበት ኅበረተሰባችን ግብረሰዶማዊነትን ቀድሞውንም የሚጠየፈው ተግባር ስለሆነ በቀላሉ የዚህን ተግባር መስፋፋት ለመቆጣጠርና ሰለባ የሆኑትንም በተለያየ መንገድ ተንቀሳቅሶ መመለስ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ የተለያዩ ኃላፊዎነት የሚሰማቸው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ትልቅ ሚና መጫዎት ይችላሉ፤ መገናኛ ብዙሃንም ትልቅ ኃላፊነትን በመውሰድ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ሁሉን የሚመለከት፣ ሀገራችን ይዛቸው የኖረቻቸውን ዕሴቶች ትርጉም የሚያሳጣ ኃይልና አዝማሚያ ያለው ነውና፤ የሀገራችንና የማኅበረሰባችንን ዕሴቶች ደግሞ የመጠበቅና የማስቀጠል ኃላፊነት የሁሉም አካላት ድርሻ መሆን ይኖርበታል፤ ችግሩን ለማስወገድ መረባረብ አለባቸው፤ ሁላችንም እንደዚሁ በግልም ሆነ በኅብረት ጉዳዩ ይመለከተናል ብለን ማኅበረሰባችንም ለመታደግ መሥራት ይኖርብናል፡፡

ለማንኛውም ከእንስሳት ብቻ አይደለም ከእጽዋትም ከሚያሳንስ ከዚህ ከግብረሰዶማዊነት ተግባር ፈጣሪ ይጠብቀን! አሜን!

 

 

 

 

 

Please follow and like us:
error

4 COMMENTS

Leave a Reply