ጠባያተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ባሕሪያት)

(በካሣሁን ዓለሙ)

(ማስታወሻ፡- (1) የሻይ ቤት ሙግት ከሚለው የቀጠለ እና ‹ሀልዎተ እግዚአብሔር› በሚለው መጽሐፌ በምዕራፍ ሦስት የተካተተ ነው፤ (2) ህልውናን በሚመለከት የተሰጠው ወሰነ ትርጉምም (definition) በኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት የባሕርይና የአካል አተረጓጎም አንጻር ነው፤ ኾኖም ግን የግል አቀራረብ ስላለበትና ከጽሑፍ አብሮ እንዲሠምር ታስቦ ስለተጻፈ የሊቃውንቱን እምነትና አተረጓጎም በቀጥታ አይወክልም፡፡)

በኬክ ቤት ተገናኝተን በእግዚአብሔር መኖር ዙሪያ ተጨቃጭቀን ከተለያየነው ወደጄ ጋር ኢ-ሜይላችንን ተለዋውጠን ስለነበር በኢ-ሜይል አድራሻዬ እግዚአብሔር በምን እንደሚታወቅ እንድጽፍለት ጠየቀኝ እኔም ከዚህ በታች ያሰፈርኳቸውን የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ጽፌ ላኩለት፡፡  ጽሑፉን ካነበበ በኋላም በነጥቦቹ ዙሪያ በኢ-ሜይል በመጻጻፍ በጠባያቱ ዙሪያ ክርክሮች አደርገናል፡፡ ክርክራችንም በእግዚአብሔር ጠባያት ዙሪያ የተቃውሞ ጥያቄ ያላቸውን ሰዎች ስሜት ያንጸባርቃል፤ እንዲሁም የሚስማሙትንም ግንዛቤ ያሰፋል በሚል እሳቤ ከዚህ በመቀጠል በተከታታይ ይቀርባል፤ እዚህ ግን የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ምን ምን እንደሆኑ ቀርበዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን እግዚአብሔር የሚለው ስም በአጭሩ ሲተረጎም ምን ማለት እንደኾነ እንመልከት፡፡

  1. ሀልዎተ-እግዚአብሔር-

“ሀልዎት” የሚለው ቃል መሠረቱ ሀልወ የሚለው የግዕዝ ግሥ ነው፡፡ ሀልወ ማለትም አለ ወይም ኖረ ማለት በመኾኑ ሀልዎት የሚለው ቃል መገኘት ወይም መኖር የሚል ፍችን[1] ይሰጣል፡፡ ህልውና ሲል ደግሞ የአኗኗር ኹኔታን ይገልጻል፡፡

እግዚአብሔር የሚለው የአምላክ ስምም “እግዚእ” እና “ብሔር” ከሚሉ ኹለት የግዕዝ ቃላት የተጣመረ ስያሜ ነው፡፡ “እግዚእ” ማለት ጌታ ፣ ገዥ ወይም አስተዳዳሪ ማለት ሲኾን እንደ ግዛቱና የኃላፊነት ድርሻው የወሰነ ትርጉም (definition) አፈታቱ ይለያያል፡፡ “ብሔር” ማለትም ሀገር ወይም ዓለም ማለት ነው፡፡ የዚህ ወሰነ ትርጉምም ከአንድ ጎጥ አካባቢ እስከ አይወስኔ ክልል ድረስ እንደኹኔታው ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ “ዘብሔረ-ቡልጋ” ሲል የተወሰነ የጎጥ አካባቢን ፣ “ዘብሔረ ኢትዮጵያ” ሲል የተወሰነ ክልል የተበጀለት ሰፋ ያለ ሀገርን ፣ “ብሔረ መልአክት” ፣ “ብሔረ ጻድቃን” ሲል ደግሞ እኛ ወሰኑን ከዚህ እስከዚህ ብለን ልንገልጸው የማንችል ነገር ግን መልአክትና ጻድቃን የሚኖሩበት የተከለለ ሥፍራ መኖሩን ይገልጻል፡፡ በዚሁ መልክ እግዚአብሔር የሚለው ትርጉምም የዓለም ወይም የሀገር ገዥ ፣ አስተዳዳሪ ወይም ጌታ ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሀገሩ ወይም ዓለሙ ደግሞ ዓለመ-ፍጥረቱ (Universe) እስከእነ ፍጥረቱ በመኾኑ እግዚአብሔር ስንል ዓለመ-ፍጥረቱን ከእነ ግሳንግሳዊ ፍጥረቱ ፈጥሮ እየጠበቀ እና እያስተዳደረ የሚገኝ አካል ማለታችን ነው፡፡

  1. የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት

ማንኛውም በህልውና የሚገኝ ነገር የራሱ ባሕርይና አካል[2] ይኖረዋል፡፡ የአንድ ህልው ነገር ባሕርይና አካልም የተለያዩ ናቸው እንጂ ተለያይተው አይገለጹም፡፡ ማለትም ያለ ባሕርይ አካል አይኖርም ያለ አካልም ባሕርይ አይገለጽም፡፡ ስለኾነም አካል በመገለጫነት ባሕርይ ደግሞ የአካልን ማንነት ወይም ምንነት ለይቶ አሳዋቂ በመኾን በአንድነት ይከሰታሉ፤ ይኖራሉ፡፡

የአንድ ህልው ነገር ባሕርይም ምንጊዜም አንድና ወጥ ነው አይለዋወጥም አካሉ ግን በቅርጽ ፣ በኹኔታ ፣ በመልክና በጊዜ ቆይታ ሊቀያየርና ሊለያይ ይችላል፡፡

ባሕርይ ማለት የአንድ ህልው ነገር ጥንተ መሠረት ወይም የተፈጥሮው ምክንያት ማለት ነው፡፡ ባሕርይ በአካል ህልው ኾኖ ከአካል ሳይለይ የአካልን ጠባይ ወይም ስሜት ይገልጻል፡፡ በመኾኑም አንድ አካል ተለይቶ የሚታወቀው ባህርዩ በስውር አብሮት ኾኖ ማንነቱን ወይም ምንነቱን ሲያንጸባርቅለት ነው፡፡ ኾኖም ባሕርይ በረቂቅነት በኅሊና ይጻፋል እንጂ ይህ ነው ተብሎ አይገለጽም፡፡ ባሕርይ ጥንት መሠረት ወይም የተፈጥሮ ምክንያት ነው ስንልም ህልው ነገሩ የተፈጠረበት መሠረተ ነገር ነው ማለታችን ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው እንደ ሃይማኖት አስተምህሮ ከኾነ ከሰባት ጥንታት (ባህርያት) ተሠርቷል፡- ከአራት ባህሪያተ ሥጋና ከሦስት ባህርያተ ነፍስ፡፡ አራት ባህሪያተ ሥጋ (ጥንታተ ሥጋ) የሚባሉት ክቡድነት (አፈር) ፣ እርጥብነት (ውኃ) ፣ ተንቀሳቃሽነት (ነፋስ) ፣ ሞቃታማነት (እሳት) ሲኾኑ ሦስት ባህሪያተ ነፍስ የሚባሉት ደግሞ አስተዋይነት (ለባዊነት) ፣ አሰላሳይነት ወይም ተናጋሪነት (ነባቢነት) እና ነዋሪነት (ሕያውነት) ናቸው፡፡ በእነዚህ ጥንታት ኅብረት አማካይነትም ሰው የሚለው ባሕርይ ተገኝቷል፡፡ እነሱም በአካል አማካይነት ተገልጸው የሰውን ማንነት ከሌለው ፍጥረት ተለይቶ እንዲታወቅ ያደርጋሉ፡፡ ስለኾነም ሰው የሚለውን ባሕርይ በአእምሯችን ውስጥ በመሳል ወይም በመቅረጽ አስነብበው የሚያሳውቁን ናቸው፡፡ በዚህም አንድ ባሕርይ የተገለጸበትን አካል የሚያሳውቅባቸው መሠረታዊ ጠባያት ወይም ጥንታት እንደሚኖሩት መረዳት እንችላለን፡፡

አካል ባሕርይ በስውር የሚገለጽበት ነገር ነው፡፡ ረቂቅ (መንፈስ) ወይም ግዙፍ ሊኾን ይችላል፡፡ የትኛውም ቢኾን የባሕርይ መገለጫ ህልው ነገሩ የሚያካትታቸው ነገሮች በሙሉ የሚገኙበት ነው፡፡ አካል እንደ ዓይነቱና ምንነቱ ወይም ማንነቱ ወጥነት ያለው አንድ ዓይነት ሊኾን ወይም በመልክ ፣ በቅርጽ ፣ በኹኔታና በጊዜ ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሰው አካል ተለዋዋጭና የተለያየ ነው፡፡ ህጻን ፣ ወጣት ፣ ጎልማሳና ሽማግሌ በመኾን ከተወለደበት ጊዜ እስከ እርጅና ጊዜው ድረስ በመጠን ፣ በገጽታና ኹኔታ ይቀያየራል፡፡ ሴትና ወንድ በመኾን ይለያያል፡፡ በመልኩም ጥቁር ፣ ቀይ ፣ ቢጫና ነጭ በመኾን ልዩነት አለው፡፡ አካለ ሙሉና አካለ ጎደሎ በመኾን ግለሰቡ ራሱ የተለያየ የአካል ቅርጽና ገጽታ ሊፈጠርበት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን የሰው አካል ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ያለውን ሰብዓዊ መገለጫ ያጠቃልላል፡፡

ምንም ዓይነት የአካል ገጽታ መልክ ወይም ኹኔታ ይኑረው ኹሉም የሰው ዘር አንድ ሰው የሚል ባሕርይ ብቻ ነው ያለው፡፡ በዚህም ከእንስሳት፣ ከድንጋይ ፣ ከዛፍ ወዘተ… ተለይቶ በሰብዓዊነት ሊታወቅ ችሏል፡፡ አካሉም የህልው ነገር ባሕርይ የሚገለጽበት ፣ ህልው ነገሩም በዓይነት ፣ በመልክ ፣ በቅርጽ ፣ በኹኔታና በጊዜ ተለያይቶ የሚዘረዘርበትና በረቂቅነት ወይም በግዙፍነት የሚገኝ ነገር ነው፡፡

በአጠቃላይ ስለ ባሕርይና አካል ምንነት (ጽንሰ ሐሣብ) ይህንን ያህል ከተነጋገርን እስቲ ደግሞ የእግዚአብሔርን ባሕርይና አካል እንመልከት፡፡ ህልው ነገር የራሱ ባሕርይና አካል እንዳለው እግዚአብሔርም በህልውና ሲኖር ባሕርይና አካል እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም፡፡ ያለ ባሕርይና አካል ህልውና ሊኖረው አይችልምና፡፡

2.1. የእግዚአብሔር ባሕርይ መታወቂያ ጠባያት

የእግዚአብሔር ባሕርይ አንድ ነው ፤ እሱም ከሀሊነት (ኹሉን ቻይነት) ነው፡፡ ከሀሊነቱ የሚታወቅባቸው ጠባያትም (ጥንታት) አሉት[3]፡፡ ምንም እንኳን እነዚህን ጠባያት ለያይቶ በመዘርዘርና በማብራራት ማስረዳት አስቸጋሪ ቢኾንም ቢያንስ የተወሰኑትን ጠቅሶ ማሳየቱ እግዚአብሔርነቱን ለማወቅ ወሳኝነት አለው፡፡ የእግዚአብሔር ከሀሊነት መታወቂያዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. ዘላለማዊነት

እግዚአብሔር በጊዜ አይለካም፡፡ ጊዜ የዚህ ዓለም ወይም የፍጥረት መለኪያ ነው፡፡ መለኪያም የሚያስፈልገው ተለኪ ሲኖር በመኾኑ ጊዜና ፍጥረት (ዓለመ-ፍጥረቱ) ሳይለያዩ በአንድነት ተገኝተዋል፡፡ ማለትም ጊዜ የፍጥረቱ ህልውና መለኪያ ፣ ፍጥረቱ ደግሞ የጊዜ ተለኪ ኾነው በአንድነት ተፈጥረዋል፡፡ እግዚአብሔር ግን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ አሁኑም ዓለምን ፈጥሮ በማስተዳደር ላይ የሚገኝ እና ወደ ፊት ዓለሙ ሲያልፍ (ሲጠፋ) የሚኖር ነው፡፡ “ለሀልዎቱ ጥንትና ፍጻሜ የለውም” እንዲሉ አበው፡፡ በመኾኑም በእግዚአብሔር ዘንድ ጥንትና ፍጣሜ ፣ አሁንና ወደፊት የሚል የጊዜ ቅድድሞሻዊ መለኪያ አይሠራም፡፡ በሌላ አገላለጽ የጊዜ ልውውጥና ቅድድሞሽ የሚሠራው በጊዜ (በዕድሜ) ለሚለኩት የዓለመ-ፍጥረቱ ፍጥረታት ብቻ ነው፡፡ ስለኾነም እግዚአብሔር ጊዜ የማይወስነው ወይም የማይለካው ለፍጥረታት መለኪያነት ግን ጊዜን የፈጠረ ዘላለማዊ አምላክ ነው፡፡

2. ፈጣሪነት

በዓለመ-ፍጥረቱ የሚገኙ ፍጥረታት በሙሉ በእግዚአብሔር ተፈጥረዋል፡፡ በእሱም ያልተፈጠረና ያልተወሰነ ፍጥረት ምንም የለም፡፡ ስለኾነም ከረቂቅ ነገሮች (ፍጥረታት) እስከ ግዙፋን አካላት የእሱ ሥራዎች ናቸው፡፡ የፍጥረታቱንም ብዛትና ዓይነት የሰው ልጅ ምንም ዓይነት ቴክኖሎጂ ቢጠቀም ከዚህ እስከዚህ ብሎ ወስኖ ማወቅና መግለጽ አይችልም፡፡ ከእሱ ሥርዓትና ሕግ ውጭም ሊኖር ወይም ሊኾን የሚችል ምንም ዓይነት ፍጥረት የለም፡፡ የፈጠራቸው ፍጥረታትም በዓይነት ፣ በመገኛ ፣ በአኳኋን ፣ በርቅቀትና በጊዜ ይለያያሉ፡፡ ስለኾነም ምንም ዓይነት ድግግሞሽ የኾነ ፍጥረት የለም፡፡ ማለትም ኹለት ወይም ከዚያ በላይ አንድ ዓይነት ፍጥረታት የሉም፡፡ ፍጥረታቱንም በዓይነትና በደረጃ ፀጋውን አድሎ በሕግና በሥርዓት ያኖራቸዋል፡፡ ስለኾነም ፍጥረታቱ “ከየት መጣችሁ” ቢባሉ ከእግዚአብሔር ወይም “ማን ፈጠራችሁ” ቢባሉም እግዚአብሔር በማለት መልሱን ሳያብሉና ሳይክዱ ይሰጣሉ፡፡

3. አዋቂነትና ጥበበኛነት

እግዚአብሔር የነበረውን፣ ያለውንና የሚመጣውን እያንዳንዱን ነገር ምንም ሳይቀር ያውቃል፡፡ በእርሱ ዘንድ ቅጽበት ዘላለም ሲኾን ዘላለምም ቅጽበት ነው፡፡ በዕውቀቱም የዘላለሙን ኹሉንም ነገር በቅጽበት ፣ የቅጽበቱን እያንዳንዷን ነገርም ለዘላለም ያውቃታል፡፡ በመኾኑም ለእርሱ እረስቶ ማስታወስና ገምቶ መተንበይ አስፈላጊው አይደለም ፤ አማካሪና አስታዋሽም አያስፈልገውም፡፡ “ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን ያውቃል፡፡” እንዳሉ አበው፡፡ “በእግዚአብሔር ፊት ሁላችንም እኩል ብልህ እኩልም ሞኝ ነን” እንዳለ አይንስታይን፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔር የማያውቀው ምንም ነገር የለም፡፡ ፍጥረቶቹንም ከምናቸው እስከ ምናቸው ምንም ሳያስቀር ያውቃቸዋል፡፡

የእግዚአብሔር የማወቂያ ህዋሳትም እንደ ሰው ልጅ (ፍጥረት) ህዋሳት በመጠንና በዓይነት የተወሰኑ ፣ እንዲሁም በጊዜ እርዝመት የማወቅ ችሎታቸውን የሚቀንሱ ወይም የሚያሻሽሉ አይደሉም፡፡ አዕምሮውም የህዋሳቱን መልእክት በቅደም ተከተል በመቀበል የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ በመኾኑም የአዕምሮና የማወቂያ ህዋሳት ውስንነት የለበትም፡፡ ኾኖም ያለ ምንም ወሰንና ምርጫ ከፍጥረቱ ጋር በእነዚህ ሕዋሳት ግንኙነት ያደርጋል፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ከዓይነ ስውር ጋር በድምፅ (በንግግር)፣ መስማት ከተሳነው ሰው ጋር በምልክት መግባባት እንደሚችለው እግዚአብሔርም ፍጥረቱ ሊረዳው በሚችል መልክ እራሱን ያሳውቃል፡፡ ከፍጥረቱም (በተለይ አዕምሮ ካላቸው) ጋር ግንኙነት ይፈጥራል፡፡

ፍጥረት በሥርዓት ተነድፎ የተሠራ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ምጡቅ ጥበበኛነት ይመሰክራል፡፡ ሌላውን ኹሉ ትተነው የሰውን ተፈጥሮ ብቻ ብናስተውል የጥበቡንና የእውቀቱን ምጥቀትና ጥልቀት ለማድነቅ እንገደዳለን፡፡ ለምሳሌ ሰው የሐሳብና የአካል ሥሪት መኾኑ ያልተፈታ የጥበብ እንቆቅልሽ ነው፡፡ የሰው አንጎል ሥሪት ውስብስብነት ፣ የአስተሳሰቡ መጠን አለመወሰን ፣ ከመጥፎው ይልቅ ደጉን መምረጥ..ወዘተ፡፡ “ከምን ዓይነት ጥበብ ቢሠራ ነው” እያሉ ከመደነቅ ውጭ የሥሪት ምሥጢሩን ሊፈታው የቻለ ጥበበኛ (ዐዋቂ) ሰው አልተገኘም፡፡ በአጭሩ ፍጥረታት በሥርዓትና በሕግ ተጠባብቀው ፣ በዓይነትና በመጠን በዝተው እያንዳንዳቸውም አስደናቂ ጥበብን ይዘው መገኘታቸው የእግዚአብሔር ጥበብ ከፍጡራን አእምሮ በላይ ነው ብሎ ዝም ከማለት ውጭ ለመናገርም የማይቻል ምጡቅ መኾኑን ይመሰክራል፡፡

4. ኃያልነት

እግዚአብሔር ለማድረግ የፈለገውን ነገር የመፈጸም ችሎታና ስልጣን አለው፡፡ ለምሳሌ ዓለመ-ፍጥረቱን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቷል (የመፍጠር ኃይል) መልሼም ላጥፋው ቢል አፍታ አይፈጅበትም (ወደ አለመኖር የመመለስ ኃይል) ፤ በሌላ ልቀይረው ቢልም ኃይልና ሥልጣኑ አለው፡፡ የትኛውንም ነገር ማድረግ ብቻ ሳይኾን መኾንም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ምሉዕ አካሉ ሳይጎድልና ሳይሰበሰብ በአንድ ነገር ላይ ለፍጥረቱ ራሱን መግለጽ ወይም ነገሩን ኾኖ መታየት ይችላል፡፡ እንዲሁም ኹሉንም ፍጥረት እንደጠባዩ ሕግና ሥርዓት ሠርቶ ያስተዳድራል፡፡ በአጭሩ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ከእሱ ችሎታና ሥልጣን በላይ የኾነ ምንም ነገር የለም፡፡

5. አለመወሰን

እግዚአብሔር በጊዜ ፣ በቦታ ፣ በአኳኋንና በእርቅቀት የተወሰነ አይደለም፡፡ ከጊዜ አንጻር ዘላለማዊ ነው ፤ ጊዜ አይለካውም፡፡ ከቦታ አንጻር ፍጥረቱ ወይም ዓለመ-ፍጥረቱ በውስጡ ይገኛል እንጂ በእሱ ብቻ የተሰበሰበ እኩል ወይም በዚያ በተወሰነ ክፍል ብቻ የሚገኝ ወይም ከዓለመ-ፍጥረቱ ተለይቶ የሚገኝ አካል አይደለም፡፡ በዓለመ-ፍጥረቱና ከእሱ ውጭ ጭምር ይገኛል እንጂ ኾኖም ከየት እስከየት የሚለውን የሰው ልጅ ወስኖ ሊያውቀውና ሊረዳው አይችልም፡፡ ከኹኔታው አንጻርም እግዚአብሔርን በመልክ ፣ በቅርጽ ፣ በመጠንና በእንቅስቃሴ ወስኖ መግለጽ አይቻልም፡፡ የእግዚአብሔር ርቅቀትም በአእምሮ ጠባይዕ የማይረዱት መንፈስ ነው፡፡ ኾኖም እንደ ነፋስ ዝርውነት ያለበት ፣ እንደነገሮች መድቀቅም የተበተነ አይደለም፡፡ በየትኛውም ነገር ውስጥ ሰርጾ በመግባት መገኘት ይችላል እንጂ፡፡ ማለትም ግዙፍም ኾነ ረቂቅ እሱ ሰርጾ የማይገኝበት ነገር የለም፡፡ መንፈስነቱ “ነፍስ ከእሱ ዘንድ እንደ ተራራ የገዘፈች ናት፡፡” እንዳሉ አበው ከምንም ነገር የረቀቀ ነው፡፡ በመኾኑም በጊዜ ፣ በቦታ ፣ በአኳኋንና በእርቅቀት ሳይወሰን በየትኛውም ሥፍራ በአንድ ጊዜ በፈለገው ነገር መገለፅ ይችላል፡፡

6. አለመለዋወጥ

ፍጥረታት ኹሉ በኹኔታ ፣ በጊዜ ፣ በመጠን ፣ በዓይነት ወይም በሌላ ነገር ይቀየራሉ ፤ ይለዋወጣሉም፡፡ እግዚአብሔር ግን በኹኔታ የማይገዛ ፣ ከጊዜ ክበብ በላይ፣ መጠን የማይወስነው ፣ አቻ የኾነ ሌላ ዓይነት የሌለው በመኾኑ ከአንዱ ወደ ሌላው ተቀያሪ ወይም ተለዋዋጭ አይደለም፡፡ ማለትም ጥንት ዓለሙን ከመፍጠሩ በፊት የነበረው እግዚአብሔር ዓለምን

ከፈጠረ በኋላም ኾነ ወደፊት ያው እሱው ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ፍጥረታት እንዲለዋወጡ ያደርጋል እንጂ እሱ ተለዋዋጭ አይደለም፡፡

7. ሞራላዊነት

እግዚአብሔር የሞራል ሀብታም ነው፡፡ ከዚህ ከበዛ ሀብቱም ኅሊና ላላቸው ፍጥረታት በተለይም ለሰው ልጆች በኅሊናቸው በመጻፍ የሞራል ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ እነዚህም የእግዚአብሔር ሞራል መገለጫዎች ቅድስና ፣ ፈቃደኝነት ፣ ሐቀኝነት፣ ፈታሒነት (ትክክለኛ ፍርድ ሰጪነት) ፣ ሩህሩህነት ፣ ቸርነት ፣ ታጋሽነት፣ አፍቃሪነት… ናቸው፡፡

እግዚአብሔር በቅድስናው ኃጢያት የማይስማማው ንፁህ ፣ ልዩ ፣ ጽኑዕና ክቡር ነው፡፡ በንፅህናው ምንም የኃጢአት እድፈት የሌለበትና የማይስማማው ከፍጥረት ኹሉ የተለየ ነው፡፡ በዚህም ልዩ በኾነ ንፅህናው ፍጥረት ኹሉ ያከብረዋል፡፡ የንፅህና ክብሩን ለማግኘትም ፍጥረት የተባለ ኹሉ ምስጋና ያቀርብለታል፡፡ በዚያም ከቅድስናው በፀጋ ይሳተፋል፡፡ እሱም ከቅድስናው ምንም ሳይቀንስበት ወይም ሳይጨምርለት እንደተመሰገነና እንዳደለ በንፁህ ጸአዳዊ ልዩነቱ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡

እግዚአብሔር ዓለሙንና በዓለሙ ውስጥ የሚገኙትን ፍጥረታት ፈጥሮ የሚያስተዳድረው በፈቃዱ ነው፡፡ ስለኾነም በፈቃድ አልባነት የሚኖር አምላክ አይደለም፡፡ ከእሱ ፈቃድ ውጭ የምትፈጸም እንዲት ነገርም የለችም፡፡ ኹሉም ነገር በፈቃዱ ሥርዓትን ጠብቆ ይከናውናል እንጂ፤ ፈቃዱም ዘላለማዊ ነው አይቀያየርም፡፡

እግዚአብሔር እውነተኛ ፣ ትክክለኛና ሐቀኛ የኾነ ፍትሕን የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ማለትም የሚወሰነው የፍርድ ውሳኔ የማይዛባ ስለኾነም ያጠፋውን በትክክል ይፈርድበታል የተበደለውንም እንደሚገባው

ይፈርድለታል፡፡ ለፍርዱም የሌላን ምክር ፣ እማኝ ፣ ማስረጃና ምክንያት አቅራቢነት አይፈልግም፡፡ ኹሉንም ዐውቆ በትክክል ይፈርዳል እንጂ!

እግዚአብሔር ለፈጠረው ፍጥረት ኹሉ የሚራራ የሚያስፈልገውን ነገር ኹሉ በሕግና በሥርዓት የሚለግስ ቸር አምላክ ነው፡፡

ስለኾነም ፍጥረቱን ኹሉ የሚያየው በመልካምነት ነው፡፡ ፍጥረቱንም በጣም ይወዳል፡፡

2.2. የእግዚአብሔር አካል መታወቂያ ጠባያት

የእግዚአብሔር አካል በረቂቅነት (መንፈስ)፣ በስፉህነትና በሙሉዕነት ጠባያት ተለይቶ ይታወቃል፡፡

1. ርቅቀት

የእግዚአብሔር አካል የሚታይ ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ሳይኾን ፍጡር ከተባለ ከየትኛውም አካል የረቀቀ መንፈስ ነው፡፡ በመንፈስነቱም በየትኛውም አካል ውስጥ ሰርጾ ይገኛል፡፡

የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ከፍጥረት የመርቀቅ ደረጃ ጋር በማነጻጸር ማየት ይቻላል፡፡ የፍጥረት እርቅቀት ሲቀንስ ግዝፈቱ ይጨምራል፤ በተቃራኒው ግዝፈቱ ሲቀንስ እርቅቀቱ ይጨምራል፡፡ ይህ የፍጥረት እርቅቀትም ከዓለትና ብረት ጥብቀት እስከ ሐሣብ መንፈስነት ያለውን ደረጃ ይይዛል፡፡ ሐሣብ ደግሞ የትኛውም ግዙፍ ኾነ ረቂቅ ነገር ውስጥ መስረፅ ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር አካል ደግሞ ከሐሣብም የረቀቀ ስለኾነ በየትኛውም ቁስ አካል፤ ኃይል (Energy) እና መንፈሳዊ አካል ውስጥ ሰርጾ የሚገኝ መንፈስ መኾኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

2. ስፉህነት

የእግዚአብሔር አካል ረቂቅ (መንፈስ) ብቻ ሳይኾን ስፉህም ነው፡፡ የእግዚአብሔር አካል በቦታና በጊዜ የተወሰነ ስላልኾነ ከዓለመ-ፍጥረቱ ውጭ ጭምር ይገኛል፡፡ በሃይማኖት እንደሚባለው ሰማየ ሰማያትም ይሁን እምቀ እምቃት በእግዚአብሔር ውስጥ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ 12 ሰማያት አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሰማያት በምስጢር ማህተም ተመተው ተዘግተዋል፡፡ ምንም ዓይነት ፍጡር ሊገባባቸው፣ ሊያውቃቸው አይችልም፡፡ በ7ቱ ሰማያት ግን ከ100 የማያንሱ ዓለማት፣ ብዙ ከዋክብት እና ሌሎች አካላት በእነሱ ላይ ከሚኖሩ ፍጥረቶቻቸው ጋር ይገኛሉ፡፡ የፍጥረቱ ብዛትና የሰማያቱ ስፋት ከእዚህ እስከዚህ ተብሎ በፍጡራን አእምሮ ሊገመት አይችልም፡፡

በሳይንሱ ከሄድንም በዓለመ-ፍጥረቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት ያሉባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈለጋተ ከዋክብት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ከዋክብት ጋር የሚኖሩ ብዙ አካላት በአካላቱም ላይ የሚገኙ ፍጥረታት ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በአንዳንድ ፈለጋተ ከዋክብት ውስጥም በቢሊዮን የሚገመቱ ከዋክብት ይኖራሉ፡፡ ከአንዱ ኮከብ እስከ ሌላው ያለው ርቀትም በጣም ረዥም በመኾኑ በብርሃን ዓመት ካልኾነ በኪሎ ሜትር መግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡ በየትኛውም ይሁን በእግዚአብሔር ውስጥ የማይገኝ የዓለመ-ፍጥረት ክፍል የለም፡፡ ስለኾነም የእግዚአብሔርን አካል ስፋት የዓለመ-ፍጥረቱ መንፈሳዊ ክፍልም ይሁን ግዙፉ ዓለም አይወስነውም፤ በእሱ ውስጥ በእጅ መዳፍ ላይ እንደተቀመጠ እቃ ይቆጠራል እንጂ!

3. ምሉዕነት

የእግዚአብሔር አካል እርቅቀት (መንፈሳዊነት) እንደ ፍጥረቱ በዝርውነት ተበትኖ የሚገኝ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ያለው አካል ሦስትነት ያለው አንድ መንፈሳዊ አካል ብቻ ነው፡፡ ይህም አካሉ በየትኛውም ግዙፍና ረቂቅ አካል ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው ከነጥብ ያነሰ ክፍተት በመሀል ሳይኖርበት ወይም በፍጡራን አካል ቦታ ያዥነት በመለያየት የተቀጣጠለ ሳይኾን በሙሉዕነት የሚገኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜ ፣ ቦታና የፍጥረታት መኖር በእሱ ምሉዕ አካል ውስጥ ይገዛሉ እንጂ እሱን ሊቆጣጠሩት አይችሉም፡፡ ስለኾነም የእግዚአብሔር አካል የማይገኝበት ምንም ነገር የለም፡፡

በአጠቃላይ 7ቱ የሰው ልጅ ጠባያት የሰው ልጅን ማንነት እንደሚገልጽልን ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የእግዚአብሔር የባሕርይና አካል ጠባያትም አንዱ ከሌላው ጋር በመናበብ የእግዚአብሔርን ምንነት ወይም ማንነትና የፍጽምናውን ደረጃ ለማወቅ የግንዛቤ ሥዕል ይሥላሉ፡፡ ስለኾነም እግዚአብሔር በየትኛውም ጠባያቱ ፍጹም መኾኑን መረዳት አለብን፡፡

(ሙግቱ ከዚህ በኋላ ይቀጥላል)

[1] አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(1948)፣ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ፤ ሀልዎት፡- መኖር መገኘት፣ መኾን፣ መፈጠር፤ ኮነ እና መጽአ የዚህ አጋር ናቸው፤ህልው፡- ያለ፣ የኖረ፣ የሚኖር፣ ነባር፣ ቀዋሚ፣ እውነት፤ ህላዌ፡– መኖር መኾን አንዎር፣ ኑሮ፤ ወይም ህላዌ፡- አካል፣ ገጽ፣ አቋቋም ቁመት፣ አኳኋን፣ ኹኔታ፡፡ አካል ማለት ባህርይና ግብርን ሰብስቦ የሚይዝ ሰብሳቢ፣ ገዥ፣ አዛዥ፣ ባለቤት፣ ማለት ነው፤ ገጽ፡370-371፤ ሰዋሰው ግእዝ ገጽ 48

[2] የባሕርይና የአካል ፅንሳተ ሐሣባት የተወሰዱት ከሊቀ ጠበበት (ኋላ አለቃ) አያሌው ታምሩ ‹መች ተለመደና ከተኩላ ዝምንድና› ገጽ 75፣ 147፣ 151 ፣ 160 እና ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ‹መድሎተ አሚን› ገጽ 107፣ 144-148 መጽሐፎች ነው፡፡

 

[3] የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት በሥነ መለኮታዊያን ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውና የሌላቸው (communicable & incommunicable) በሚል ይከፈላሉ፤ እዚህ የተጠቀምነው ያንን መንገድ ሳይኾን ከባሕርይና ከአካል መገለጫ አንጻር ነው፡፡

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply