ጥበበ-ቅኔ (የቅኔ ፍልስፍና)-፩

(በካሣሁን ዓለሙ)

‹ዕዉቀት ቢወዳደር ድርሰት ቢፎካከር፣

ሁልጊዜ ቅኔ ናት የድርሰቱ ጀምበር፡፡›

ከበደ ሚካኤል

መዳረሻ

የቅኔን ምንነት ተረድቶ ለማስረዳት የቅኔዉ ባለቤት መኾንን ይጠይቃል፤ ችግሩ አልጠግብ ባይ ወይም ችግረኛ ‹የማትሞላ ዓለም› እንደሚለዉ የቅኔን ፍልስፍና ለማስረዳት የዕዉቀት ሕጸጽ ስላለ አንዱ ሲሟላ ሌላዉ እየጎደለ ቅኔም በሰፊዉና በአግባቡ ሳይጠና ይቀራል፡፡ በአንጋረ ፈላስፋ አንድ ፈላስፋ ‹ጊዜ፣ ዕድሜ፣ ቦታ፣ ፈቃድ፣ ችሎታና ስምምነት እነዚህ ፮ (6) ነገሮች ከተረዳዱ ሥራ ኹሉ ይፈጸማል› እንዳለዉ የተሟላ መልስ በማግኘት የቅኔን ምንነት በአግባቡና በቅኔነቱ ለመግለጽም የሰዋሰዉ ሥርዓትን (እርባ ቅምርንና አግባብን) እና የቅኔ ስልትና ዓይነትን ጠንቅቆ ከማወቅም በተጨማሪ የፍልስፍና ዕዉቀትን ይዘትና ቅርጽ በአግባቡ መረዳት ያስፍልጋል፡፡ ይኹንና በዐቅም ዉስንነት ሰበብ ያሰቡትን ሐሳብ ሳይገልጹ ዝም ከማለትና የአስፈላጊ ነገሮችን መሟላት ከመጠበቅ የተገነዘብኩ የመሰለኝን ሞክሬ የቀረዉን ሊቃዉንቱ በቁጭት እንዲያሟሉትና እንዲተቹት ወይም እንዲያሻሽሉት መተዉ የተሻለ መስሎ ይሰማኛልና በግሌ ይህን ስሜቴንና የተገነዘብኩ የመሰለኝ  ሐሣብ ላካፍል ፈለግሁ፡፡

ደግሞም እኮ! ጥበብ የተሠራችዉና የበለጸገችዉ በቅብብሎሽና በመሻሻል እንጂ በአንድ ሰዉ ‹ኹሉ ዐወቅነት› እንዳልኾነ እናዉቃለን፤ እንኳን ሌላ የሐሳብ ግንብን ማቀበል ለጥበብ ግንባታ አስተዋፅኦ እስካለዉ ድረስ አንዳንድ ጊዜ ‹ማፍረስም መሥራት ነዉ› ብለዋል ከበደም ሚካኤል፡፡ እጓለ ገ/ዮሐንስም ‹አንድ (አንዳንድ)  ሰው ለራሱ የማይመስለውን ነገር ለማፍረስ ብቻ ይሰለፋል፡፡ ሌላው ደግሞ ማፍረስን ለሌላው ትቶ በገዛ ሐሳቡ መሠረት አዲስ ለመገንባት ያስባል፡፡ የተሻለው ዘዴ ሁለተኛው ይመስለናል፡፡›[1] እንዳለው፤ አስተዋፅኦ ካለዉ ያቅማችንን ማቀበሉ ጥቅም ይኖረዋል የሚል እምነት ስላለኝ የራስን ግንዛቤ ለማቅረብ ደፈርኩ፡፡ ስለዚህ የቅኔን ፍልስፍናም በሊቃዉንቱ የማጠንጠኛ መሠረተ-አሚን (Principle) ላይ ተመሥርቼ ለመቃኘት ጥረት አደረኩ (ደፋርና ጭስ!)፡፡

እንደምናውቀው የሀገራችን ሊቃውንት ትልቅ ዕዉቀት ቅኔ ነዉ፤ በቅኔ እሳትነት ያልተጣደ ዕዉቀትም በአግባቡ አይበስልም፤ ያለ ቅኔ የሚመረምር ሊቅም ምርምሩ የተስተካከለ አይኾንም ተብሎ ይታመናል፤ ያለባትሪ በጨለማ የሚደናበር ወይም ያለ መስታወት መልኩን ለማየት የሚጥር ሰዉን ይመስላል፡፡ አስተዋይነትን የታደሉ ብዙ ሊቃዉንትም ለቅኔ ያላቸዉ ፍቅር ልዩና ድንቅ ነዉ፤ አንድ ሰዉ ‹በቅኔ ነዉ የሚናገረዉ› ከተባለም ዕዉቀት ሰርጾታል ወይም መጠቅ ያለ ዕውቀት አለው ማለት ነዉ፡፡ በተለይ በሊቃዉንቱ ዘንድ የንግግር ኹሉ ለዛዉ፣ ምጣኔዉ፣ ጥልቀቱም ኾነ አይረሴነቱ የሚከብረዉ በቅኔያዊነት ደረጃዉ ነዉ፤ ስለኾነም የዕዉቀታቸዉ ዋና መለኪያም ሐሳብን በቅኔ የመግለጽ ችሎታ ነዉ፡፡ ለምሳሌ መጋቢ መርሻ የተባሉ የዲማ ጊዮርጊስ ባለቅኔ ‹የሰዉን የዕዉቀቱን መጠን የማዉቀዉ በቅኔዉ ነዉ› ይሉ ነበር ይባላል[2]፤ ምክንያቱም የቅኔ ‹ትምህርቱ የዕውቀት በር መክፈቻ፣ የአእምሮ መገመቻ፣ የጥበባት ኹሉ መግለጫ ምንጭ[3] ተደርጎም ይወሰድና ያገለግል ነበረና ነው፡፡

መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሔም፡

ሀገረ ቅኔ በኾነችው በኢትዮጵያ የቅኔ ትምህርት እጅግ በጣም የተከበረና የተወደደ ነው፡፡ ክቡርነቱና ተወዳጅነቱም በካህናት ወይም በቤተ ክርስቲያን ሰዎች ብቻ ሳይኾን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ባሉት ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ በመኾኑም ቀደም ባለው ወቅት ቅኔ የሚያውቁት ካህናቱ ብቻ ሳይኾኑ ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱና መኳንንቱም ጭምር ነበሩ፡፡[4] ይሉናል፡፡

ይህም ቅኔ ምን ያህል የሊቃዉንት የዕዉቀት ደረጃ መነጋገሪያ አቅማቸዉና ደረጃው ከኹሉም ጥበባት ከፍ ብሎ የተከበረ ዕውቀት እንደነበረና መኾኑን ያስረዳናል፡፡ ይህ ከኾነም ‹እንዴት ነገሩ!› የሚል ጥያቄ ቅኔን ለመመራመር እንድናነሳሳ ይጋብዘናል፡- ታዲያ ምን እንጠብቃለን? ‹ለምን የቅኔ ዕውቀት ደረጃ ከፍተኛ ክብር ሊያገኝ ቻለ?› ይህንን ጥያቄ ይዤ መልስ ፍለጋ ስባዝን ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማሪያም ወርቅነህ ‹ትምህርቱ የዕውቀት በር መክፈቻ፣ የአእምሮ መገመቻ፣ የጥበባት ኹሉ መግለጫ ምንጭ› ስለኾነ ከግዕዝ ቋንቋ ተሸምኖ መሠራቱ ሊቃውንትን ኹሉ እየሳበ ወደ እሱ ዕውቀት እንደሚያስገባ ገለጹልኝ፤ ቀጠሉ ታላቁ ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ‹ቅኔ ለድርሰት መልመጃ፣ ለቅዱሳት መጻሕፍት መክፈቻ፣ ለመንፈስ ማደሻ፣ ለአእምሮ ማጎልመሻ ሊኾን በቅዱሳት መጻሕፍት ሕግ› የተዘጋጀ መኾኑን ገለጹልኝ፡፡[5] እኔም መጠየቄን አላቆምኩም፤ ‹ምን ስለኾነ?› ብዬ የዱርየ ቅላጼ ያለው ጥያቄ አስከተልኩ፤ ‹ተቀንየ› ይልብሃል ሲሉኝ የዱርዬ ጥያቄን ትቼ እነሱ የሚሉትን መስማት ጀመርኩ፤ ‹ይበል!› ሲሉ ስሰማም በአድናቆት ኾኜ ወደ ዋናዉ ነጥቤ ገባሁ፡፡ እናንተም ‹ንግባ ሀበ ጥነተ ነገረነ› በሉኛ!

 ቅኔ ምንድን ነው?

በእንደ እኔ ዓይነቱ ‹ጥራዝ ነጠቅ› ዕውቀት ላይ ተሣፍሮ ለሚጋልብ ሰው የቅኔን ምላቱንና ስፋቱን ‹እንድህ ነው› ብሎ ለመግለጽ መመኮሩ ይቅር የማይሉት ትልቅ ድፍረት ነው፡፡[6] ምንም አይደል ‹ይቅር በለንሃል! ባይኾን ሊቃውንቱ ምን ብለው አንደተረጎሙት ተናገር› ካላችሁኝ ልቀጥል፡፡ ዘመኑ የምክንያት እንጂ የቅኔ አይደለም በሚል ‹ምክንያት› ካላችሁ፤ ‹የቅኔው ጠቢባን የኾኑት የኢትጵያን ሊቃዉንት ቅኔን ምን ብለዉ እንደሚተረጉሙት ማየት አስፈላጊ ስለኾነ መመርመር ግድ ይለናል› እላችኋለሁ፤ ስለኾነም መሠረታዊ ትርጉሙን ይዤ ለመግለጽ ልሞክር (ምክንያታሞች!)፡፡

የቅኔ[7] መሠረታዊ ትርጉም ‹አእምሮን ለምሥጢር ማስገዛት› የሚል ነዉ (በምክንያት ስትጀነን የነበርክ ባለአእምሮ ቅኔ ምሥጢር ይዞ መጣልህ/መጣብህ)፤ ይሁንና ‹ከአእምሮ የበለጠ መዝገብ የለም› እንዲሉ አበው የአእምሮ ግዛት ደግሞ ሰፊ፣ ምጡቅ፣ ዉስብስብና ረቂቅ ነው፤ ስለኾነም ይህንን ግዛት ተቆጣጥሮ ማስገዛትና መምራት የጥበብ የጠቢብነት ጣሪያው ነዉ፡፡ ስለዚህ የቅኔ ትርጉም ግዛቱን (አእምሮን)፣ ገዥውን (ቅኔን)ና የአገዛዙን ምሥጢር (አፈታት) ማወቅን ይፈልጋል፡፡ ለማንኛውም ሊቃውንቱ ከሰጡት ሥረዎ-ቃላዊ ትርጓሜ በመነሣት ምርምር እናድርግ፡፡ ተከተሉኝ!

የቅኔ ሥርዎ-ቃላዊ ትርጉም

የቅኔ ሥሩ-ምንጩ ‹ቆንቆነ› ወይም ‹ቀነየ› ከሚል ግስ (ቃል) እንደኾነ ይታመናል[8]፤ ትክክለኛው ሥርዎ-ቃል ‹የትኛው ነው› በሚለው ላይ ሊቃውንቱ በኹሉት ተከፍለውበታል (ወይም እኔ ከፈልኳቸው)፡፡ አንዳንድ ሊቃዉንት ቅኔ ‹ቆንቆነ› (ነቀዘ ወይም ቁንቁን ኾነ) ከሚል ቃል የተገኘ መኾኑን በመጥቀስ ቁንቁን እንጨትን በመሰርሰር እንደምትበላዉ ቅኔም የሐሳቡ ጥልቀት የሰዉን አእምሮ በመበርበር ሙሉ በሙሉ ለምሥጢር የሚያስገዛ በመኾኑ› ስያሜዉን ሊያገኝ ችሏል በማለት ይከራከራሉ፡፡ ይህም፡-

‹ቆለኛዉ ደገኛዉ ነዉና ወጌሻ፣

የነቀዝ መድኃኒት ፈልስፏል ሐበሻ፡፡›

እንደተባለዉ፤ ቅኔንም ከቁንቁንነት ፈልስፏታል ባይ ናቸዉ፡፡

 ሌሎች ደግሞ ሥርዎ-ቃሉን በመቀየር ቅኔ የወጣዉ ‹ቀነየ›[9] ከሚለዉ ግስ ነዉ፤ ትርጉሙም በቀጥታ ‹ግዛት፣ መግዛት›[10] ማለት ነዉ ብለዉ ይሟገታሉ፤ የአእምሮ ግዛት ሰፊና ዉስብስብ ነዉና፤ ‹ቅኔም አእምሮን  በምሥጢር ማስገዛት› የሚል ትርጉም የሚሠጠዉ ከዚህ ግስ የተገኘ ጥሬ ዘር ስለኾነ ነዉ ይላሉ፡፡ በኹለቱም በኩል የሚገኙት ሊቃዉንት የቅኔን ትርጉም ‹ሕዋሳትን ለሕሊና አስገዝቶ በተወሰነ ቁርጥ ሐሳብ ስለሚታሰብ ቅኔ›[11] በመባሉ ይስማማሉ፡፡ ለምሳሌ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬም ኾኑ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ‹የውስጥና የውጭ ሕዋሳትን ለሕሊና አስገዝቶ በሰከነ መንፈስና በተመስጦ በተወሰነ ወይም ቁርጥ ሐሳብ ላይ የሚታሰብ ስለኾነ ቅኔ የሚለውን ስያሜ ሊያገኝ› መቻሉን በመግለጽ ስማማሉ[12]፡፡ ስለኾነም ኹለቱም ወገን ሕሊና በሕዋሳት ላይ ያለውን ገዥነትና ተቆጣጣሪነት በማረጋገጥ ቅኔ የሌሎችን ሐሳብ ቀድሞ ከንግግር አያያዛቸው በመረዳት፣ ነገሮች ገላልጦና ገልብጦ በማየት እና በጥልቀት በማሰብ ያለውን ወሳኝነት በሚመለከት  ልዩነት የላቸውም፡፡

ይህም ሕዋሳትን ለአእምሮ ማስገዛት አእምሮን ሰብስቦ በመመሰጥ ለእግዚአብሔር ከፍ ያለና ልዩ ምስጋናን ለማቅረብ ያስችላል በማለት ይከራከራሉ፤ ስለዚህ ቅኔን ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋና ማቅረቢያ ጥበብ ያደርጉታል፡፡ ለምሳሌ መልአከ ብርሃን አድማሱ ቅኔን ሲተረጉሙ፡-

 ‹ቅኔ ማለት ተቀንየ ሙሾ አወጣ፣ ግጥም ገጠመ፣ አራቆ ተናገረረ፣ አዜመ፣ አንጎራጎረ፣ መራ ዘፈነ ካለው የወጣ ጥሬ ዘር› ስለኾነ ‹ሰው ከራሱ አንቅቶ ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋና ላቅርብ ባለ ጊዜ ምሳሌ መስሎ፣ ምሥጢር አሻሽሎ ግጥም በመግጠም የልቦናውን እውቀት፣ የአእምሮውን ርቀት የሚገልጽበት፣ የዕውቀቱን ደረጃ የሚያስታውቅበት፣ የሰሚንም ልቦና የሚያነቃበትና የሚያራቅቅበት ድርሰት ማለት ነው፡፡›[13] በማለት አስቀምጠዋል፡፡

‹ቅኔ ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋና ማቅረቢያ ነዉ› የሚለዉ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነዉ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ለእግዚአብሔር መቀኘት እንደሚገባ የሚገልጽ ቃል ስላለ[14]፤ እነ ቅዱስ ያሬድን የመሰሉ ኢዮጵያውያን ሊቃውንትም የምስጋና ቅኔን ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚገባ ስላስረዱ[15]፤ በዚህም ‹ቅኔ ለአምላክ ልዩ ምስጋና ማቅረቢያ ጥበብ ነዉ› የሚለዉ ከሃይማኖት አስተምህሮ ጋር ተገናዝቦ መሠረቱን የጣለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ በጣም የላቀ ነገርን የሚገልጸው ምጡቅ ነው ብሎ ባሰበው ችሎታው ልክ እንጂ በተራ ነገር (ንግግር) ሊኾን አይችልምና፤ ቅኔ ደግሞ አእምሮን በመመሰጥ፣ ትኩረትን ሰብስቦ በአምላክ ሥራ መደነቅን ሲለሚፈጥር ልዩ ኃይል ያለዉ ዕዉቀት ነዉ፡፡ አንድ ሰዉም የምስጋና ቅኔን ቢቀኝ ቅኔዉ ጥልቅ ከኾነ የአምላኩን ሥራ በጥልቀት አስተዉሎ መግለፅ በመቻሉ እየተደሰተበት ይኖራል እንጂ አይረሳዉም፤ የቅኔዉ ልቅናም (ከፍ ያለ መኾን) ኹልጊዜም ‹ይበል!› የሚያሰኝ ዐዲስ፣ ያቀረበዉንም ምስጋና አይረሴና ተብሰልሳይ ልዩ ያደርገወል፤ በተለይም ይህ ሁልጊዜ አዳዲስ የምስጋና ቅኔን መቀኘት በመቻል ሲገለጽ ክብርም ይሰጠዋል፡፡

ኾኖም እዚህ ላይ ‹የላቀ ወይም ልዩ ምስጋና ማቅረቢያ› የሚለዉ አገላለጽ ጥንቃቄን የሚሻ ይመስለኛል፤ ማለትም ምንም እንኳ ‹የሰዉ ልጅ የተፈጠረዉ ለፈጣሪዉም ምስጋና በማቅረብ ክብሩን ለመዉረስ ነዉ› ከሚለዉ መርህ ጋር ተገናዝቦ ‹ቅኔ ለአምላክ ልዩ ምስጋና ማቅረቢያ ነዉ› የሚለዉ አግባብ ቢኾንም ከቅኔ ዘርፈ ብዙ አገልግሎትም አንጻር መቃኘትም አስፈላጊ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ቅኔ በዓለማዊ ሕይወታችን የደስታንና የሐዘንን ጥልቀት ለመግለጥ[16]፣ የጊዜዉን ክስተትና ኹኔታ ከተለያየ አተያይ አመሥጥሮ ለማሳየት፣ የፍቅር ስሜትን በጥልቀት ለመግለጽ፣ ከዚያም ባለፈ ብልግናን፣ መጥፎ ግብርን፣ ስድብን፣ መከፋትን እና የመሳሰሉ እኩይ ተግባራትን ደብቆ በለዛና ቁምነገር እያዋዙ በምጣኔ ለመግለጽና ለማሳወቅ ይዉላል፡፡ አገልግሎቱም በጣም ሰፊና ዘርፈ ብዙ ስለኾነ ቅኔን በምስጋና ማቅረቢያነት ወስኖ ማስቀመጥ የቅኔን ምንነት የተሟላ አያደርገዉም፡፡

 እንዳዉም እኮ ባለቅኔዎች አያስችላቸዉም የሚተች ነገር ካገኙ አያልፉም ያመሰገኑ አስመስለዉ ይሰድባሉ፤ ያሞካሹ መስለዉ ያዋርዳሉ፤ መንግሥትንም ኾነ እግዚአብሔርን ለመንቀፍ አይመለሱም፡፡

አሁን ባለቅኔን ማን ይቃወመዋል፣

እንዳሻዉ ሊናገር ሥልጣን ተሰጥቶታል፤

ሊመርቅ፣ ሊሰድብ ሥልጣኑ በእጁ ነው፣

ሲያማ እንኳን ሰው ቀርቶ እግዜርም አይተርፍው (አይቀረው)›

እንዳሉት ነው አቢዬ መንግሥቱ ለማ፡፡[17]

ለዚህ ማሳያ የሚኾን አንድ የጉባኤ ቃና ቅኔ እንጥቀስ፡

‹ኮንኖ ኃጥአን ኩሎሙ ኢይደልዎከ ምንተ፣

አፍቅሩ ጸላዕትክሙ እንዘ ትብል አንተ፡፡›[18]

ትርጉም፡-

እኛን እያዘዝከን ጠላቶቻችንን እንድወድ፣

አንተም አይገባህ በኃጥያተኞች መፍረድ፡፡

ይህ ቅኔ ባለቅኔዎች ምን ያህል ደፋሮችና ቆራጦች እንደኾኑና እግዚአብሔርን ሳይቀር ከመሞገት እንዳማይመለሱ ጥሩ ማሳያ ነው፤ ባለቅኔው በዚህ ቅኔው የእግዚአብሔርን ፍርድና ትእዛዝ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፤ ‹ትእዛዝህ ትክክል ከኾነ የአንተም ጠላቶች ኃጥያቶኞች ናቸውና በእነሱ ላይ ሳትፈርድ ቅርና ዐሳየን፤ አንተ በጠላቹህ ላይ በጥፋታቸው ልክ እየፈረድክ እኛ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ ብለህ አትዘዘን፤ ለአንተ ያቀተህን እንዴት እኛን ፈጽሙ ትለናለህ?› በማለት ይሞግታል፡- ባለቅኔው፡፡ ይህንን ደግሞ መዳፋር ወይም መሞገት እንጂ ምስጋና ማቅረብ ልንለው አንችልም፡፡

ከዐፄ ምንሊክ ጋር በተያያዘ አንድ የአንኮበር ሚጣቅ ዐማኑኤል ደብር አለቃ የነበሩ ሊቅ የደብር አለቅነታቸው ከሳቸው ተወስዶ ለአንድ የመጽሐፍ ገላጭ ለኾነ ደብተራ ስለተሰጠባቸው የሚከተለውን ቅኔ ተቀኝተው ለንጉሡ በመላክ የደብር አለቅነታቸውን አስመልሰዋል፡፡

‹በባሕር ዝንጀሮ በገደል ላይ ዓሣ፣

መቅደስ ለዛር ፈረስ ነጋሪት ለአንካሳ፣

ጌታዬ መንግሥትህ ተበላሽቷል እሳ፡፡›[19]

ስለዚህ ቅኔ ለአምላክ ምስጋና ማቅረቢያ ብቻ አድርጎ መዉሰድ ሙሉዕ ገለጻ አይደለም፤ ከመንፈሳዊነት አንጻር ግቡ ላቅ ያለ የምስጋና ማቅረቢያ ጥበብ መኾኑ አንደተጠበቀ ኾኖ፡፡ ያዋረዱ መስለዉ ማወደስም በቅኔ የተለመደ ነዉና፤

‹ይቆርጡኝም እንደሁ፣ ይፈልጡኝም እንደሁ እስኪ እንየዎ፣

ያለምጣም ምኒልክ ብዬ ሰደብኩዎ፡፡›

እንዳለዉ አዝማሪ፡- ‹ለምጣም› ያለ አስመስሎ ‹የዓለም ጣዕም› ብሎ ሲያወድስ፡፡

ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰዉም ቅኔ ሐሳብን በመሰብሰብ አእምሮን ማስገዢያ ነዉ የሚለዉ ነጥብ ስምምነት ያለው  የቅኔ መሠረታዊ ትርጉም ነዉ፤ ኹለቱም የቅኔ ትርጉም መመንጫ ግሶችም (ቆንቆነ፣ ቀነየ) በዚህ አእምሮን በምሥጢር ማስገዛት በሚለዉ ነጥብ መስማማታቸውን ገልጸናል፡፡ የሰዉ ልጅ አእምሮ የሚያስታውስ፣ የሚመረምር፣ የሚፈትሽ፣ የሚያብላላና የሚተነብይ ኃይል ያለዉ በመኾኑም ቅኔ ‹ቆንቆነ› ከሚለዉ ግስ ወጣ ቢባል ‹ቀነየ› ከሚለዉ ግስ ጋር ያስማማዋል እንጂ አያቃርነዉም፤ ቁምነገሩ ከመበርበር አቅሙ ጋር ይያያዛልና፤ በጥልቀት ማብሰልሰል መበርበርም አእምሮን ስለሚቆጣጠረዉ ‹ቅኔ አእምሮን ለምሥጢር ማስገዛት ነዉ› ቢባል ጸዳቂ ያደርገዋል፡፡ እንዲሁም ‹ቀነየ› የሚለዉ ቃልም በቀጥታ ‹ገዛ› ወይም ‹መገዛት› በሚል የሚፈታና ቅኔ ማለትም ቀጥታ ከግሱ የወጣ ጥሬ ዘር ስለሚመስል ‹አእምሮን በምሥጢር ማስገዛት› የሚለዉን ይተረጉማል፡፡ ማርዬ የተባለ ምሁርም የቅኔን ምንነት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ‹አእምሮን ለምሥጢር ማስገዛት› ብለዉ ከተረጎሙት ጋር በማስማማት እንደሚከተለዉ ይጠቅሰዋል፡፡

አንድ ሰዉ ስለ አንድ ነገር/ድርጊት ያገኘዉን ዕዉቀት ወይም ምሥጢር ምሳሌ መስሎ፣ ምሥጢር ወስኖ፣ ቃላት መጥኖ፣ በዐዲስ ግጥም የሚያቀርብበት ድንገተኛ ድርሰት ነዉ፤ ቅኔ ዕዉቀቱንና የአእምሮዉን ርቀት (ምጥቀት) የሚገለጽበት፣ የዕዉቀቱን ደረጃ የሚያስታዉቅበት (የሚያሳይበት) የሰሚንም ልቦና የሚያነቃቃበትና የሚያራቅቅበት ድርሰት ነዉ[20]፡፡

በአጠቃላይ ‹ቅኔ አእምሮን ለምሥጢር ማስገዛት ነዉ› የሚለዉ መሠረታዊ ትርጉም ጥልቅ እሳቤን አምቆና አመሥጥሮ የያዘ መኾኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፤ የፍልስፍናው ጥበብም የሚሸከረከረው በዚህ ላይ ነው፡፡

ዘይቤያዊ ትርጉም

ሊቃዉንት ቅኔን ከሥርዎ ቃላዊ ትርጉም ባለፈ የሚተረጉሙበት ዘይቤም አላቸዉ፤ ከዘይቤው አንጻር ቅኔን ‹መጽሔተ-ጥበብ›፣ ‹ብርሃነ-ዕዉቀት›፣ ‹የመጽሐፍ መነጽር›፣…› እያሉ ይተረጉሙታል፡፡ እነዚህም ቃላት ጥልቅና ዕምቅ ሐሳቦችን ይዘዉ ይገኛሉ፡፡ የቅኔን ምንነት ከግጥም ጨዋታ ባለፈም የጥበብ መስታወት ወይም ገልጦ ማሳያ ያደርገዋል፤ ማለት መስታወት የራስን መልክና ቅርጽ ወይም አጠቃላይ ኹኔታ በትክክል ለራስ ማሳየት ይችላል፤ ቅኔም የምናፈቅራትን ጥበብ ምንነቷንና ይዘቷን ለይቶ በማጉላት ለማሳየትና ለማወቅ ማሳያ፣ ማነጻጸሪያና መመርመሪያ ይኾናልና፡፡ እንዲሁም የሰዉ ልጅ የማየት አቅም ከብርሃን መኖር ጋር የተያያዘ ነዉ፤ ዕዉቀትም በአግባቡ ፍንትዉ ብሎ የሚታየዉ ቅኔን ማወቅ ሲቻል ነዉ፤ እንዳዉም ‹ቅኔን እንደ ‹ፓዉዛ› መብራት በጨለማ የተሸፈነ ዕዉቀትን መንጥሮ መመልከቻና መለያ ነዉ› የሚሉ ሊቃዉንት አሉ[21]፤ ማለትም ዘመናውያ ሳይንቲስቶች የጨለመዉን ለመግለጥ መብራት፣ የራቀዉን አቅርቦ ለማየት ቴሌስኮፕ፣ ጥቃቅኑን ነገር አጉልቶና አግዝፎ ለመለየት ማይክሮስኮፕ እንደሚጠቀሙት የቅኔ ሊቃዉንትም ‹ይህን ድፍንፍን፣ ዉስብስብ፣ ስዉርም ግዙፍም እና ስፉህ የኾነ አጽናፈ-ዕዉቀት ለመረዳትም ቅኔ ወሳኝ ነዉ› ይላሉ፡፡

መጻሕፍትን ለመመርመርም መሪ ባትሪና ማስተዋያ መነጽር በመኾን የሚያገለግል የዕዉቀት ስልት ስለኾነም የመጻሕፍቱን ምሥጢር በማፍታታት፣ የማይስማሙ የመሰሉ ሐሳቦችን ወይም ገለጻዎች ምሥጢራቸዉን ተረድቶ በማስማማት፣ አንድምታቸዉን ለመፍታት ቅኔ የወሳኝነት ሚና ይጫወታል፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱም ‹በቅኔ ድልድልይነት ካለማወቅ ወደ ማወቅ ተሸጋግረው የመጻሕፍትን ጥልቅ ምሥጢራቸውን በቅኔ ማይስክሮፕነት አጉልተው ተመልክተው ብሉያትን ከሐዲሳት፣ ሐዲሳትን ከሊቃውንት በማስማማት እያብራሩ ተርጉመው ጉባኤ ሠርተው ሲያስተምሩ የኖሩ ሊቃውንት እጅግ ብዙ ናቸው›[22] ይሉናል፡፡ ስለኾነም  የቅኔ ትርጉም ጥልቅና የዕዉቀት መሠረቶችን ያቀፈ መኾኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

መቼም ቢኾን ጥልቅና ምጡቅ የሐሳብ ግንዛቤና ገለጻ ሊኖር የሚችለው ሊገልጹበት የሚያስችል ስልት ወይም መሣሪያ ሲኖር ነው፤ ቅኔ ደግሞ ተፈጥረውምና ተግባሩም ከዚህ ጋር ይያያዛል፡፡ ስለኾነም የቅኔን ምንነት የሊቃውንቱን የዕውቀት ደረጃና የዕውቀቱን ተወዳጅት የጨመረው፡፡ እዚህ ላይ ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲሰጠን ከሊቃዉንቱ ገለጻ አንድ ተጨማሪ ማሳያ መዉሰድ ይጠቅማል፤ ለማብራሪያው የቅኔው ሊቅ መጋቤ ምሥጢር ወልደሩፋኤል ፈጣሒን እንጋብዛቸው፤ እሳቸውመ ከመልአከ ብርሃን ገለጻ በተመሳሰል ገለጻ ቅኔን፤

‹…የዉስጥና የዉጭ ሕዋሳትን ለሕሊና አስገዝቶ በሰከነ መንፈስና በተመስጦ በተወሰነ ወይም ቁርጥ ባለ ሐሳብ ላይ የሚታሰብ ስለኾነ ቅኔ የሚለዉን ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ በተመስጦ ቅኔ በመቁጠር ላይ ያለና በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተሰወረ ሰዉ ቅኔ በሚቆጥርበት ወይም በሚያስብበት ጊዜ በአጠገቡ ወይም በፊቱ የሚደርሰዉን ወይም የሚደረገዉን ነገር እያየ አያይም፤ እየሰማም አይሰማም፡፡… የቅኔ አጠቃላይ ትርጉሙ ሰዉ ከራሱ ከልቦናዉ አንቅቶ፣ አመንጭቶ ለፈጣሪዉ አዲስ ምስጋና ለማቅረብ በፈለገ ጊዜ ምሳሌ መስሎ፣ ከምሥጢር ምሥጢር አማርጦና አራቆ ቤት በመምታትና ግጥም በመግጠም በልቡ ዉስጥ ያለዉን ዕዉቀትና የአእምሮዉን ርቀት ወይም ምጥቀት የሚያሳዉቅበት፣ የዕዉቀቱን ደረጃ ለሌላዉ የሚገልጽበትና የሚያስረዳበት፣ የሚሰማዉንም ልቡና የሚያነቃቃበት፣ የሚያራቅቅበትና የሚመስጥበት ድርሰት እንደኾነ ሊቃዉንት ያስረዳሉ፡፡› በማለት ያስቀምጡታል፡፡[23]

የሊቁ ገለጻ ሰፊዉን መጥኖና ወስኖ፣ ማብራሪያዉን አሳጥሮ፣ አስዉቦና ጨምቆ ስላቀረበዉ እያንዳንዱ ቃልና ሐረግ ለትንታኔ ይጋብዛል፤ ኾኖም ትንታኔ ከተደረገበት ለዛዉን ስለሚያጣ ዕምቅነቱን በማስተዋል ቅኔ ምን ያህል የምሥጢር ቋትና የሊቃዉንቱ የዕዉቀት ሀብት መኾኑን መገንዘብ በቂ ይኾናል፡፡ ለማንኛዉም የቅኔን ምንነት በዚህ መልክ ከቃኘን ፍልስፍናዊ ዳራዉን ደግሞ እንቃኝ፡፡ ፍልስፍናዉም ከምንነቱ ወይም ከትርጉሙ ጋር የተገናዘበ ነዉ፡፡

 (ይቆየን! ያቆየን!)

[1] እጓለ ገ/ዮሐንስ (ኹለተኛ ዕትም 2003 ዓ.ም)፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 10

[2] ማርዬ ይግዛው፣ ቅኔያው የዕውቀት ፈጠራ (2006)፣ ገጽ 11

[3] ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማርያም ወርቅነህ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፣ ገጽ 280

[4] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም፣ ገጽ 143

[5] መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ (1963)፣ መጽሐፈ ቅኔ (ዝክረ ሊቃውንት)፣ ገጽ 15

[6] ደፋርና ጭስ ኾኖ እንጂ፤ ድፍረቴን ለመቀነስ ግን መከራከሪያዬን በቅኔ ማሳያዎች በማዋዛት ማቅረቡን ትቸዋለሁ (ባቅም ምክንያት)፤ ምንነቱንም ለማብራራት ማጣቀሻ አላበዛሁም ፍልስፍናውን ለማሳየት ይረዳኛል ያልኩትን ወሰነ-ትርጓሜ (ብያኔ) ነው የተጠቀምኩት፤ ባይኾን ሊቃውንቱን ለማስቀናትና ለማስቆጨት (ተናደው የተሻለ እንዲጽፉ ለማድረግ ብሎ መውሰድም ይቻላል) በሚል  የቅኔ ትርጉሟ፣ በትርጉሙም ላይ የሚያጠነጥነው ፍልስፍናው ይህ ነው ብያለሁ፡፡

[7] ዓለማየሁ ሞገስ ደግሞ ቅኔን ሲተረጉሙ ‹ጥልቅ ምሥጢርን የምንገልጥበት ዘዴ የንግግር ስልት ሲኾን ኹለትና ሦስት ትርጉም ኑሮት ተጣምሮ አንድ ሐሳብ ለመግለጥ የተነገረ እንደኾነ ቅኔ ይባላል› ይላሉ (መልክዐ-ኢትዮጵያ፣ ገጽ 9)፡፡

[8] ከእነዚህ (ቀነየ፣ ቆንቆነ) ግሶች የወጣ ነው መባሉን የማይስማሙ ሊቃውንትም አሉ (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማሪያም ወርቅነህ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፣ ገጽ 172)

[9] ‹ቀነየ› የሚለው የግዕዝ ግሥ በስድስት መንገዶች ‹ገዛ፣ አሸነፈ፣ አቀና፣ አበጀ (ሠራ)፣ ተቀኘ (ዘመረ) እየተባለ ይፈታል (ሰዋሰው ግእዝ፣ ገጽ 49)፡፡ የመጨረሻውን ተቀኘ (ዘመረ) የሚለውን ፍች በመውሰድ ‹ቀነየ› ማለት ‹ጮኸ፣ አጉረመረመ፣ ቆዘመ፣ ሙሾ አወጣ፣ ቀነቀነ፣ መራ፣ ተቀኘ፣ ዘፈነ፣ ገጠመ ግጥም አወጣ፣ ባለቅኔ ኾነ፣ ተፈላሰፈ፣ ፈላስፋ ኾነ› ማለት መኾኑን የሚገልጹ ሊቃውንት አሉ (ሐመር መጽሔት፣ ሐምሌ/ነሐሴ 1991፣ ገጽ 30፤)፡፡ ሊቀ ሥልጣናትም ቅኔ ‹የምስጋና ግጥም ወይም የግጥም ምስጋና› መኾኑን በመግለፅ በማሳያነትም ቅዱስ ዳዊትና ቅዱስ ያሬድ ‹ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት› (ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተቀኙለት) ማለታቸውን በመጥቀስ ተከራክረዋል (ዝኒ ከማሁ)፡፡

[10] ሰዋሰው ግእዝ 146

[11] መጽሐፈ ቅኔ፣ ገጽ 9፤ ቅኔያዊ የዕውቀት ፈጠራ ገጽ 9-10

[12] መጽሐፈ ቅኔ፣ ገጽ 9፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም፣ ገጽ 130

[13] መጽሐፈ ቅኔ፣ ገጽ 9

[14] 2ኛ ሳሙ. 6፡-5፤ 22፡-1፤ መዝ 144፡-9፣ 149፡-1፤ ኣሳ 26፡-1፤ 38፡-20፤ ኤፌ 5፡- 19፤ ቆላ 3፡- 16፤ ራእ 14፡- 10፤ 15፡- 4

[15] ቅ. ያሬድ ‹ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሐት› በማለት ዘምሯል፡፡

[16] 2ኛ ሳሙ 1፡- 17፤ 3፡- 34

[17] በቃል ማስታወስ የተጠቀሰ ስለኾነ ተስተካክሎ ላይቀመጥ ይችላል፡፡

[18] የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልደት ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም.፣ ገጽ 145

[19] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 146

[20] ቅኔያው የዕውቀት ፈጠራ፣ ገጽ 11

[21] ንቡረዕድ ክፍለ ዮሐንስ የተባሉት የቅኔ ሊቅ አንድ ጊዜ በ‹ስምዐ ጽድቅ› የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጣ ላይ ቅኔ እንደ ‹ፓውዛ መብራት› በመውሰድ ማብራራታቸውን አስታውሳለሁ፡፡

[22] መጽሐፈ ቅኔ፣ ገጽ 31

[23] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000)፣ ገጽ 130-131

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply