ጥበበ-አመክንዮ ዘጥንታዊት ኢትዮጵያ

በዚህ ርዕስ ዙሪያ የሚከተሉት ጉዳዮች ግልፅ ሆነው መታየት ይኖርባቸዋል፡፡

 1. የአመክንዮ መርሆዎች
 2. የጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተምህሮ ሁኔታ
 3. የጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተምህሮ ከአመክንዮ መርሆዎች ጋር አብሮ የሚሔድ መሆኑ

ከዚህ በላይ የጠቀስናቸውን መሠረታዊ ነጥቦች ይዘን የጥንታዊ ኢትዮጵያን አመክንዮአዊ አስተምህሮ  ከአመክንዮአዊ መርሆዎች ጋር እያገናዘብን እንመርመር፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ አመክንዮ የሚያጠነጥንባቸውን ነጥቦች መለየት ያስፈልገናል፡፡ ሥነ አመክንዮንም ስንመረምር ዋና ማጠንጠኛው ኾነው የምናገኛቸው ምክንያታዊ ክርክር (አስተሳሰብ) እና ቋንቋ ናቸው፡፡ እነዚህ ማጠንጠኛዎቹንም ሥርዓት የሚያስዝባቸው ሦስት መሠረታዊ መርሆዎች አሉት፡፡ እነሱም፡-

 1. ያለ መቃረን ሕግ
 2. የማዕከል መገለል ሕግ
 3. የኑባሬ ሕግ

ሌሎች ሕግጋት (መርሆዎች) የእነዚህ ሕግጋት ዝርዝር ማብራሪያዎች ናቸው፡፡

አሁን የሚሆነው ጥያቄ ‹እነዚህ የሥነ-አመክንዮ መርሆዎች በጥንት ኢትዮጵያዊያን ይታወቁ ነበር?› የሚለው ይሆናል፡፡ ካልታወቁ ‹እና ኢትዮጵያዊያኑ አመክንዮን አይጠቀሙም ነበር?› የሚለው ጥያቄ ይከተላል፡፡ ከታወቁ ‹በዋናነት በየትኞቹ አስትምህሮዎቻቸው ውስጥ ተንፀባርቀዋል?› የሚል ጥያቄ ይመጣል፡፡

ከዚህ በላይ የሥነ አመክንዮ ትምርህርት ማጠንጠኛው ምክንያታዊ ክርክር (አስተሳሰብ) እና ቋንቋ ነው ብለናል፤ በኢትዮጵያ ደግሞ  ከጥንት ጀምሮ በጽሑፍ የታወቀ ቋንቋ (ግዕዝ)፤ የራሳችን የሆነ የሙግት ሥርዓት (ለምሳሌ ተጠየቅ ልጠየቅ እና በልሃ ልበልሃ የክርክር ስልቶች) እንደነበረን መካድ አይቻልም፡፡ እነዚህ የቋንቋና የክርክር የአስተምህሮ ማጠንጠኛዎችም ከሥነ አመክንዮ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው ካልን የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አስተምህሮ በምን ዓይነት መልኩ ነው የሥነ አመክንዮ ዝምድናው? ነው ምንም ዓይነት የሥነ አመክንዮ ይዘትና ቅርፅ የለውም? የሥነ አመክንዮ ይዘትና ቅርፅ የለውም ካልን የሥነ አመክንዮን ማጠንጠኛ ጥያቄ ውስጥ እናስገበዋለን፡፡ ምክንያቱም የግእዝ ቋንቋችን በሥነ ጽሑፍ የዳበረ እና የራሱ የኾነ ልዩ መዋቅራዊ ፍሰት ያለው ስለኾነ የሥነ አመክንዮ ተጠየቅን መጠየቁ የግድ ነውና፡፡ የክርክር ስልታችንም ቢኾን በአቀራረብ ፍሰቱ የዳበረ፡- ‹የትልቅ ሰውነት› መለኪያ እስከ መኾን የደረሰ፡- ስለኾነ የሥነ አመክንዮ ማጠንጠኛ ለመኾን ያቅተዋል ለማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የጥንታዊ ኢትዮጵያ አስተምህሮ ሥነ አመክንዮአዊ አስተምህሮን ምን ዓይነት ይዘትና የመዋቅር ፍሰት እንደነበረውና እንዳለው መመርመር የግድ አስፈላጊ ነው ማለት ይቻላል

እዚህ ላይ መታወስ የሚኖርበት መሠረታዊ ጉዳይም አለ፡፡ የሀገራችን አስተምህሮ አዕማዳትን ለይቶ ማወቅም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም አዕማዳት በሃይማኖት ትምህርት (በተለይም በክርስትና ሃይማኖት) ዙሪያ፣ በኅበረ ቋንቋ ሐሣብን በመግለፅ (በተለያየ አቅጣጫ በማየት) ስልት የደባሩ ናቸው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ አዕማዳት ሳይረዱና ሳይጠነቀቁ አስተምሯቸውን መተቸትና መተንተን ይቅር የማይባል ስህተት ያመጣል፡፡ ባይሆን አስተምህሯቸው  በሃይማኖት ላይ መመሥረቱ እና ኅብረ ቋንቋን መጠቀሙ መሠረታዊ የሥነ አመክንዮ መርሆዎችን ይጥሣል አይጥሥም የሚል ክርክር ማንሳት ይቻላል፡፡ መሠረታዊ የሥነ አመክንዮ መርሆዎችን የሚጥስ ከሆነ እኛ የኢትዮጵያዊያን አስተምህሮ ምክንያዊ አስተሳሰብ የለውም ማለት ነው? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ምክንያታዊ አስተሳሰብ በኢትያጵያዊያን አስተምህሮ አልነበረም፤ የለምም የምንል ከሆነ ‹ምክንያታዊ አስተሳሰብ በኢትዮጵያዊያን ትምህርት ውስጥ አይገኝም› ማለታችን ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነም (አላቸው፤ የላቸውም የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ) እንዴት ታዲያ ያለመክንያታዊ አስተሳሰብ የቋንቋ ሥርዓትን (ከሰዋሰው እስከ መጽሐፍ ድርሰት) መሥራትና ማዳበር ቻሉ ብለን እንጠይቃለን፡፡  በተቃራኒው ግን ‹ኢትዮጵያዊያን ምክንያታዊ አስተሳሰብን ያዳበሩ ነበሩ፤ ናቸውም የምን ከሆነ ይህ ምክንያታዊ አስተሳሰብን የያዘ አስተምህሮ በየትኛው ትምህርታቸው ውስጥ ይገኛል የሚል ጥያቄን በማንሳት የትምህርት መስኮቹን መመርመር ይናርብናል ማለት ነው፡፡

እንደ እኔ አረዳድ ከኢትዮጵያዊያን ጥንታዊ አስተምህሮ መካከል የሚከተሉት ከፍተኛ አመክንዮአዊነት አላቸው፡፡

 1. ጥበበ-ፊደል
 2. ጥበበ-ሰዋሰው
 3. ጥበበ-ቅኔ
 4. ጥበበ-ክርክር
 5. ጥበበ-አንድምታ
 6. ጥበበ-ባህል

እነዚህን አዕማዳተ ጥበባት ለወደፊቱ በሰፊው እየፈታታን ለማየት እንሞክራለን፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply