ጥበበ-ፊደል (የፊደል ፍልስፍና)

ጥበበ-ፊደል (የፊደል ፍልስፍና)

የፊደል ዘይቤ፣ ባጭር ቃል ሲፈታ፣

የቋንቋ ድብኝት፣ የቃል ኹሉ ጎታ፤

የመጻሕፍት ምንጭ፣ የምሥጢራት ነቅ፣

ቢቀዳ ቢቀዳ፣ ውሃው የማያልቅ፡፡› ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

የዐዋቂ ሰዎች ፍልስፍና ተፈጥሮን መሠረት ያደርጋል፤ በማስተዋል፣ በማንጠር ነጥሎ በማዋሃድ፣ በመለያየትና በማያያዝ የተፈጥሮን ሥሪት ይፈትሻል፤ ከዚያም ምሥጢሯን በርብሮ በማወቅ የራሱን ቀላልና አመቺ የአኗኗር ኹኔታ ይፈጥራል፡፡ በዚህ እሳቤ የተቃኘው የፊደል ፍልስፍናም ጥልቅና አስተውሎቱም ወደር የሌለው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ፊደል (አልፋቤት) ልዩ ንጥር የሆነ የፍጥረት ሥሪት ወካይ፣ የሰው ልጅን አስተሳሰብ ከተፈጥሮ ዑደታዊ ክዋኔ ጋር በማገናዘብ የሕዝቦችን ማንነት፣ ታሪክና ዕውቀት ማስተላለፊያ መሠረታዊ ምልክትና ማስታወቂያ፣ በሥሪቱም የሥልጣኔ ደረጃን፣ በምልክቱም የግዛት ወሰንንና የመንግሥት ኃይልን መስካሪና ማስረጃ ነው፤ የጥንታዊ ሥልጣኔ ማንነት ከዘመናት ጋር የማናበቢያ መሣሪያ በመሆኑም የጥበባት ሁሉ ጉሉላት የሆነ ጥበብ ነው፡፡ በተለይም የድምፅ፣ የቅርጽ፣ የጥቅልና የዝርዝር ፍጥረታት መስተጋብራዊ ሥሪት ወካይ መሆኑ ከየትኛውም ጥበብ የላቀ ያደርገዋል፡፡

የፊደል የውክልና አገናኝነትም በሁለት በኩል ነው፤ ሐሳብን በማግዘፍ ሰዎች ከውስጣቸው ያለውን አስተሳሰብና አመለካከት አውጥተው ለሌሎች በምልክቶች መስተጋብር በመከተብ እንዲገልጹና እንዲያስተላልፉ ይረዳል ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የግዙፍና የረቂቅ ፍጥረታትን በመወከል ሰዎች ብዙውን፣ ብትኑንና ውስብስቡን በሐሳብነት አርቅቀው እንዲገነዘቡት፣ እንዲመረምሩትና የተረዱትንም ለትውልድ አበልፅገው እንዲያስተላልፉት መሣሪያ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ሐሳብ ረቂቅ ነው፤ ይህንን የሚታሰበውን ሐሳቡንም ለሌሎች ለማስተላለፍና በራሱም እያስታወሰ ለማገናዘብ አስተሳሰቡን በሁለት  መንገድ የመግለጽ አማራጭ አለው፤ አንድም በቀጥታ በድምፅ፤ አንድም በምልክት ወይም በጽሕፈት በመከተብ፤ የድምፁን (በዘመናዊ መቅረጫ ዘመን) በመቅዳት ማስተላለፍ የሚችል መሆኑ ግልፅ ነው፤ በጽሐፍ ለማስተላለፍም መጻፊያው ፊደል ያስፈልጋል፡፡ የፊደል ፍልስፍና የሚመሠረተውም በዚህ ላይ ነው፡- በምንና እንዴት ዓይነት የመጻፊያ ስልትንና ሥርዓትን በተፈጥሮ ክስተት ወክለንና ምልክት ሰጥተን እንጠቀም? ውስብስቡንና ብዙን የተፈጥሮ ክስተት በምልክት አቅልለን፤ በአእምሯችን ውስጥ የሚርመሰመሰውንና የሚፈሰውን ሐሳባችንን እንዴት በወከልነው የተፈጥሮ ምልክት መልክና ሥርዓት ሰጥተን በማግዘፍ እንግለጸው? የሚል ነው መነሻው፡፡

ፊደል ልዩና ንጥር የፍጥረታት ክስተት ማወቂያና ማስታወቂያ የሆነ ምልክት ነው፡፡ በመሆኑም የዓለማችንን የትኛውንም ፍጥረትና የድምፅ ዓይነት ምልክት ሆኖ እንዲታወቅና ከአንዱ ወደ ሌላው ሰው፣ ማኅበረሰብ፣ ትውልድና ሥልጣኔ እንዲተላለፍና እንዲወራረስ ያደርጋል፡፡ በዚህም ፊደል ልዩ ነው ስንል ራሱን የቻለ ክስተትና አንድን ነገር ለመወከል አመልካች የሆነ ብቻ ነገር ስለሆነ ነው፤ ብዙ ምልክቶች አሉ፤ ለምሳሌ ሥዕል፣ ግራፍ፣ ድያግራምና የመሳሰሉት አንድን ነገር ወክለው የሚያሳዩ ናቸው፤ ፊደል ግን ከነዚህ ይለያል፤ ሌሎቹ ምልክቶች ያልሠሩትን ወክሎ ያሳውቃል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ ፊደላት ተጣምረው የተለየ መልዕክትን እንዲያስተላልፉ ያደርጋቸዋል፤ የተጣመሩት ፊደላት ትርጉም ያለው ነገር እንዲሠጡ ልዩ ቋንቋን ይፈልጋሉ፤ ሌሎች ምልክቶች ግን ቋንቋን የሚፈልጉት ለተጨማሪ ማብራሪያነት ነው፤ ተጣምረው የተለየ መልዕክትን የማስተላለፍ ተግባራቸውም ውስን ነው፡፡ በተጨማሪም ፊደል ምልክትነቱ በምጣኔ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህ ማለት በቅርጹ መጠንና በዓይነቱ ብዛት የተወሰነ ቀላል ምልክት ነው፡፡ ስለሆነም ፊደል የተለየ ንጥር የፍጥረታት ወካይ ምልክት ነው የምንለው፡፡

ለምሳሌ ሳይንስ ዓለማችን ከ93 በማያንሱ ንጥራተ ነገራት መሠራቷን በመለየትና እነዚህን ንጥራተ ነገራት በመለየትና በማወሃድ የፍጥረትን ምንነት፣ ሥሪትና መስተጋብር አነጻጽሮ በማወቅ የቁሱን ዓለም ምንነት ይተነተናል፡፡ እስካሁን ሳይንስ የደረሰባቸው ዋናዎቹ የቁሱ ዓለም መሠረታዊ ንጥራተ ነገራት እነዚህ ናቸው፤ ተጨማሪዎቹ በውህደትና በፍልጠት ስልት የተፈጠሩ ንጥራተ ነገራት ናቸው፡፡ እነዚህ ንጥራተ ነገራትም የፍጥረታት ሥሪት መሠረት እንደሆኑት ሁሉ ፊደላትም የጽሑፍ ሁሉ መሠረቶች ናቸው፡፡ ንጥራተ ነገራቱ በራሳቸው የአቶም መጠንና የኤሎክትሮን ብዛት መጠን እንደሚለያዩት የፊደላቱም ተፈጥሮ በመነገሪያቸው የሥነ ልሳን ቃና አወጣጥና የድምፅ መፈጠሪያ ሁኔታ ይለያያሉ፤ ሆኖም የራሳቸው ንጥር የሆነ ጠባይና የውክልና መልዕክት አላቸው፡፡ ስለሆነም አንዱ ፊደል ከሌላው በመልክ፣ በድምፅ፣ በቅርጽ፣ በትርጉምና በመጠሪያ ይለያል፡፡

በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትርጓሜ ከምናገኛቸው ፅንሣተ ሓሳባት አንዱ ፊደል ‹የድምፅና የቃል መልክ ሥዕላዊ መግለጫ› ነው የሚለው ነው፡፡ እውነትም በቀላል ዕይታ ስናየውና ስንገልጸው ፊደል መልክ ያለው ሥዕል ብቻ ይመስላል፡፡ በአውነታው ግን ይህ መልክ ያለው ሥዕል በድምፀት እየተለየ ተጣምሮና ተቀናብሮ ቃልን ያስገኛል፡፡ ፊደል መልክ ያለው ሥዕል ነው ስንል በልሳናዊ መገለጫ ቅርጹንና የቀለም መልኩን መናገራችን ነው፡፡ ለምሳሌ የግዐዝ ፊደል መጀመሪያ የሆነውን የ‹ሀ›ን ቅርጽ ብንመለከት፤ የቅርጹ ወደ ላይ መከፈቱ ወደ ሰማይ ማንጋገጠጥን መወከሉን ይገልጻል፤ በመሆኑም ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የሚያደርጉትን ጸሎት ይነግረናል፤ የአንድምታ ትርጓሜውም ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› የሚለውን የዳዊትን ምሥክርነት በሥዕል ወክሎ ይገኛል፡፡ በዚህም መልክ ሁሉም ፊደላት የራሳቸውን ሥዕላዊ ውክልና እና ትርጓሜ ይዘው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪ ለፊደል ሥዕል መሆን  የግብጽ ሄሮግሊፊክ ሥዕላዊ ፊደልም ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ የግብፅ ሥዕላዊ ፊደል የፍጥረታትን ቅርጽና ዓይነት በመወከል ሥዕሉን በማያያዝ ይነበባል፤ በተለይም ይህ ሥዕላዊ ፊደል የተፈጥሮ ቀጥተኛ ግልባጭ መስሎ ይታያል፡፡ ካስተዋልነው ግን የትኛውም ፊደል ቢሆን ከሥዕልነት አይወጣም፤ ቃልንም የሚያስገኛው ሥዕላዊ መልኩንና ቀለሙን በማቀናበር ነው፡፡ በአብዛኛውም ቃላዊ ትርጉም ከመስጠቱ በፊት የትኛውም ፊደል ትርጉም የሌለው ሥዕል ይመስላል፡፡

ፊደል ልክ እንደ ቃል፣ ዐ.ነገርና አንቀጽ የራሱ የሆነ ትርጉማዊና ንጥል ፍልስፍናዊ ትንታኔም አለው፤ ሲጣመርና ሲዋሐድም የተፈለገውን የቃል መልዕክት ይገልጻል፤ በቃላት ብዛት ተቀናብሮም በዓ.ነገር ይብራራል፡፡ በተለምዶ ግን የምሁራን ትኩረት ቃላት ላይ ሲያይል፤ ለፊደል የሚሰጠው ግምት ያነሰ ይሆናል፤ በዐ.ነገር ላይ ሲያጠነጥን ደግሞ የቃላት ጉዳይ በአጋዥነት ይታያል፤ የፊደል አገልግሎትም ከቃላት ትኩረት የበለጠ ያንሳል፤ በአንቀጽ ዙሪያ የዕውቀት ትንታኔና ዕይታ ሲያጠነጥን ደግሞ ፊደላት የማይታወቁ ሠራተኞች መስለው ይታያሉ፡፡ ስለዚህ ሊቃውንት ስለ አንደ መጽሐፍ ይዘት በጥቅል ሲገልጹ የእያንዳንዱ ዐ.ነገር፣ ዐ.ነገሩ ስለተዋቀሩበት ቃላት፣ ቃላቱንም ስለፈጠሩት ፊደላት ያላቸው ትኩረት በየደረጃው ይቀንስባቸዋል፡፡ የፊደል ሥዕላዊ መልክና ቀለም ትርጓሜው፣ ፍልስፋናውና ልሳናዊ ቅንብሩ በትኩረት እያነሰና ዕውቀት ከቃላት ጀምሮ በዐ.ነገር መዋቅርና በአንቀጾች አደራደርና መሰል የሐሳብ መግለጫ ስልቶች እየጎለመሰ የመጣው በዚህ መልክ ይመስላል፡፡

የፊደልን ሥዕላዊ ሥሪት ምንነትና ትርጓሜያዊ ፍልስፍና ትኩረት በማጣቱ ከመሠረታዊ ዕሳቤው ጋር በአግባቡ መናበብ ባይቻልም አሁን ባለው ሁኔታ በግርድፉ ሲመረመር ግን ሥዕላዊ ሥሪቱ፣ ምጣኔውና ጥበቡ ያስደንቃል፡፡ ስለሆነም የፊደል ሊቃውንትም ስልቱን ለይተው ሥዕላዊ ውክልናውን መዝነው ከራሱና ከሌላው ጋር በማነጻጸር በአግባቡና በአመቺነት ቀርጸው አገልግሎት እንዲሰጠን አድርገውታል፡፡ በዚህ መልክም ሥዕልነቱ በተፈጠረበት ሥርዓት፣ ባህልና ፍልስፍና ጋር እየተገናዘበ ሊመረመር ችሏል፤ይችላልም፡፡ በዚህ መልክ የሚመረምሩ ሊቃውንትም የፊደልን መልክ ያለው ሥዕልነት ያደንቃሉ፤ መሻሻልና መቀየር ወይም መጨመር አለበት የሚሉት ፊደላዊ ሥዕል ካለም አስተውለውና መርምረው ለአገልግሎት ያውላሉ፡፡ በአጠቃላይ ፊደል የቃላትና የድምፅ ሥዕል ስለሆነ በቀለምነት የተፈጥሮ ክስተትን አርቅቆና የሐሳብን መንፈስነት አግዝፎ በመመጠን የሚያሳውቅ ጥበብ ነው፡፡

ፊደል የቃልና የድምፅ መልክ ነው፤ ቃል በድምፅ ይገላጻል፤ ድምፅ ግን የቃል ክፍል ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ቃል በምልክትም የመገለፅ ዕድል አለው፡፡ ፊደል በድምፅ የተገነባ የቃል ምልክትና መልክ ስለሆነ የውበቱ መገለጫና መለያውም ይሆናል፡፡ ያለ ፊደል ድምፅ ቃናው አይጠበቅም፤ ያለ ፊደል የቃል ትርጉምና መልዕክት በአግባቡ ተጠብቆ ከአንዱ ወደ ሌላው ወይም ወደ ሌላ ጊዜ ማስተወሻነት አይተላለፍም፡፡ ስለሆነም ፊደል የድምፅ ምልክትና ማስተላለፊያ፣ የቃላት መፍጠሪያ አጥንት፣ ሥጋና ደም ነው፤ በእሱም የቃል ሰውነት ተገንብቶና ደምግባት አግኝቶ መልዕክት በማስተላለፍ በተለያዩ ሥፍራ፣ ጊዜና ሁኔታ የሚገኙ ሰዎችን ወይም ማኅበረሰቦችን አርክቶ በተወዳጅነት ይኖራል፡፡

የፊደል መልክ ገና በቀለምነት የተገለጸ የድምፅ ወካይ የቃል መፍጠሪያ ዘር ነው፡፡  ይህም ማለት ፊደል ልዩ የሆነ ምርጥ ዘር እንጂ እንደተደፋ ቀለም እንደተገኘ የተቀባ ቅብ አይደለም፡፡ የፊደል ምርጥ ዘርነትም በልዩ አፈጣጠሩና የዕውቀት ሁሉ ዘር፣ መነሻ በመሆኑ ይታወቃል፡፡ ዘር አንድ የተለየ ተክል፣ ዛፍ፣ ሣር ወይም እህል መነሻ፣ መገኛ፣ መራቢያ መሠረት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ዘር የተፈጥሮ መለያውን መሠረት በማድረግ ይበቅላል፤ በተለያየ አቅጣጫ ሥር ሰዶ፣ በቅሎ በማደግ ያፈራል፤ ይባዛል፤ በእሱ መሠረትነትም ማንነቱ እየተራባ ይቀጥላል፤ በእሱ ምክንያትም የፍጥረታት ሕይወት ይቀጥላል፤ አካባቢው አየር ንብረት ይጠበቃል፤ በልምላሜም አካባቢው ይዋባል፡፡ የፊደል ልዩ ተፈጥሮም ከዚህ ዘር ጋር ተመሳሳይ ጠባይ ይታስተዋልበታል፡፡ ምክንያቱም በፊደል ቀለምነት ቃላት ይሠራሉ፤ በእነሱም ገላጭነት የሰው ልጅ የቃላቱን ፅንሣተ-ሐሳብ በቀላሉ አንጥሮ በማነጻጸርና የሚሰጡትን ጥቅም ለይቶ በመረዳት የተፈጥሮን ምንነትና መስተጋብራዊ አኗኗር ይረዳል፤ ዕውቀቱንም አከማችቶ ለሌሎቹ ያስተላልፋል፡፡ አንድ የዘር ፍሬ መሬት ላይ ወድቃ በመብቀል ሥሯን በመሬት ውስጥ እንደምታንሠራፋው፣ ቅርንጫፏንም ወደ ከባቢ ዐየር እንደምትዘረጋው፤ በፊደል ዘርነት የበቀለች ቃልም በሰዋሰው ሥርዓትና ስልት በጊዜና በሁኔታ እየተለዋወጠች ቅርንጫፏን ታንሠራፋለች፡፡ ስለዚህ የዕውቀት ሁሉ መሠረት ልዩ የሆነችው የፊደል ዘርነት፣ መነሻነት ነው፡፡

ሆኖም መታወቅ የሚኖርበት ፊደል የፍጥረት አምሳል እንጂ እውነተኛ ግልባጭ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፊደል የተሣለ ቀለም ነው፤ ቀለምነቱም ከተፈጥሮ የተቀዳ ሰው ሠራሽ ፈጠራ ነው፡፡ ይህም ማለት ፊደል ውስብስብ ፣ ግዙፍ ወይም ረቂቅ፣ ብዙና የተለያየ የሆነውን የተፈጥሮ ክስተትና መስተጋብራዊ ሁኔታ በቀለም አቅለለን፣ ሥለንና መጥነን የምንገልጽበት የሰው ልዩ ፈጠራ ጥበብ ነው፡፡ ስለሆነም ፊደል በቅርጽ፣ በመልክ፣ በድምፅና በመጠን ተመትሮ የተሠራ ትርጉም ሰጪ የሰው ልጅ የማቅለም ጥበብ ነው፡፡

በጥቅሉ የፊደል ፍልስፍና የሚከተሉትን የሊቃውንት ገለጻ መሠረት አድርጎ ይብራራል፡፡

  1. ፊደል ማለት መጽሔተ አአምሮ ማለት ነው፤ ምክንያቱም ያለ ፊደል ምንም አይታወቅምና፤ የአእምሮ መገመቻ የምሥጢር መመልከቻ ማለት ነው፡
  2. ፊደል ማለት ነቅዓ ጥበብ ማለት ነው፤ ምክንያቱም የጥበብ ኹሉ ምንጭ መገኛ ፊደል ናት
  3. ፊደል ማለት መራሔ ዕውር ማለት ነው፤ ምክንያቱም የሰውን ልጅ ኹሉ ከድንቁርና አውጥቶ ወደ ብርሃን ይመራልና፡፡
  4.  ፊደል ማለት ጸያሔ ፍኖት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ድንቁርናን ጠርጎ አጽድቶ ከፍጹም ዕውቀት ያደርሳልና፤
  5. ፊደል ማለት ርእሰ መጻሕፍት ማለት ነው፤ የመጻሕፍት ኹሉ ራስ እናት ፊደል ናትና፤ ለ ፊደል ማንኛውም መጽሐፍ ሊነገር አይቻልም፤ ‹ኢተወልድ መጽሐፍ ዘእንበሌሁ ለፊድል› ይላልና፡፡ (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማሪያ ወርቅነህ ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፤ ገጽ 18)

(ቀሪው ለሚቀጥለው ይቆየን!)

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

  1. Impressive! well expressed and keep it up! It helped me to understand Ethiopians’ own philosophy towards alphabet and nature as well. I crave to see the second part.

  2. Impressive! well expressed and keep it up! It helped me to understand Ethiopians’ own philosophy towards alphabet and nature as well. I crave to see the second part.

Leave a Reply