ፅርፈት ለማን ?ስለ አለቃ አያሌውና መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ መልስ አሠጣጥ


(ካሣሁን ዓለሙ)

ሰሞኑን አንድ በትምህርት ምክንያት ከተዋወቅኳቸው ትልቅ የቤተክርስቲን አባት ጋር ‹ሀልዎተ እግዚአብሔር› ስለሚለው መጽሐፌ እየተወያየን ነበር፡፡ በመሃል አንድ ጥያቄ አነሱብኝ፡- ‹የመጽሐፉን መታሰቢያ ለምን ለአለቃ አያሌውና ለመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ልታደርግ ቻልክ?› የሚል፡፡ ምክንያቴንም ነገርኳቸው፡- አንደኛ ኹለቱን አባቶች በመጽሐፎቻቸው ስለማውቃቸውና በሊቅነታቸውም ስለምደነቅ የቤተክርስቲያኔቱን ሊቃውንት ሊውክልሉኝ ይችላሉ ብዬ፤ ኹለተኛም እንደነዚህ ዓይነት ተመዋጋቾች እንደነበሩንና እንዳሉን ማሳያ ይኾናሉ በማለት፤ እንዲሁም እነሱ ለቤተክርስቲያንቱ ዶግማ፣ ተውፊትና ቀኖና በአደባባይ ግንባር ቀደም ኾነው በመከራከር አቃቢያን እምነት እንደኾኑት እኔም በመጽሐፌ ኢ-ኣማንያንን ለመሞገት ስለመኮርኩ ለማሳያነት ላስታውሳቸው ብዬ ነው አልኳቸው፡፡ ጥሩ ነው በርታ ብለው ከመከሩኝና ከመረቁኝ በኋላ ስለ ኹለቱ አባቶች አንዳንድ ነገሮችን አነሳን፡፡

በመጀመሪያም ስለ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ነገሩኝ፡፡ የነበራቸውንም የሊቅነት ደረጃና እምነታቸውን አብራሩልኝ፡፡ ሊቅነታቸውን መድሎተ አሚን›፣ ‹ኩክሐ-ሃይማት›ና ዝክረ-ሊቃውንት› የሚሉት መጽሐፎቻቸው እንደሚመሰክሩላቸው፣ በተለይ በመድሎተ አሚን ያቀረቧቸውን የመከራከሪያ ነጥቦችና የአቀራረብ ስልት በምሳሌ እያብራሩ አስረዱኝ፡፡ በእውነት መጽሐፍ እየደጋገሙ ከማንበብ የበለጠ በሊቃውንት ጠጋ ብሎ መጠየቅ ብልህነት መኾኑን ያወቅኩት በዚህ ነው፡፡ ከዚያም ቀጥለው ‹መልአከ ብርሃን አድማሱ እኮ አሉኝ ዐዋቂ ብቻ አይዱሉም የሞተ ልጃቸውን በጸሎት ያስነሱ ብርቱ አማኝም ናቸው፡፡ በዚህ ዕውቀት ነግሥዋል ተብሎ ሃይማኖት በተናቀበት ዘመን ያዕቆብ ‹ካልባረከኝ አለቅህም› እንዳለው ልጄን በዚህ ሰዓት ልትወስድብኝ አይገባም› ብለው ካምላካቸው ጋ በመሟገት የሞተን ያስነሡ አባት ናቸው› አሉኝ፡፡ እኔም ምንም እንኳን ታሪኩን ባውቀውም አነጋገራቸው ግን እየመሠጠኝ አዳመጥኳቸው፡፡ ከዚያ ቀጥለውም ስለ አለቃ አያሌው ታምሩ ማብራሪያ ሠጡኝ፡፡

አንድ ጊዜ ምን ኾነ መሰለህ አሉኝ፤ በሊቃውንት ጉባኤ ኹለቱ አባቶች ባሉበት ክርክርና ውይይት ሲደረግ ይውላል፤ መጨረሻም ሲወጡ መልአከ ብርሃን ወደ ኋላ ቀረት ብለው አንዱን አባት ምን አሏቸው መሰለህ ‹እኛ እኛ! እንኳን ብንሔድ (ብንሞት) የሚተካን ሞልቷል ሀገሬ ግን ይህንን ዕውር (ዓይነ-ሥውር) ለመተካት መቶ ዓመትም አይበቃት›፡፡

‹ለምን እንዲህ አሉ?› አልኳቸው፡፡

‹ለምን እንደኾነ ታውቃለህ በአለቃ አያሌው ዕውቀትና አቀራረብ ሲደነቁ ውለው እኮ ነው!፤ ደግሞ ራስን ዝቅ አድርጎ የሌላውን መመስከር ትልቅነታቸውን ያሣያል› አሉኝ፡፡ ከዚያም አለቃ አያሌው ስለጻፏቸው መፅሐፎችና ስለ ነገር ዐዋቂነተቻው አብራሩልኝ፡፡

እኔም በመሃል ላይ አንድ ነገር አነሣሁ፡፡ ‹እነዚህ ኹለት ሊቃውንት አንድ አባ አየለ ተክለ ሃይማት የሚባል የካቶሊክ ምሁር የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያ እምነት በሚመለከት ለጻፈው መጽሐፍ መልስ የሚኾን መፅሐፎች ጽፈዋል፤ በአቀራረባቸው ግን ይለያያሉ፤ ለምሳሌ አለቃ አያሌው ወደ ስድብና ዘለፋ ያዘነበሉ ይመስላሉ፤ መልአከ ብርሃን አድማሱ ግን አቀራረቡን እያረሙ ወደ መተቸት ያዘነበሉ ናቸው፤ ይህ እንዴት ይታያል?› ብዬ ጠየቅኳቸው እንደ ኢቲቪ ጋዜጠኛ!

‹እንዴት መሰለህ› አሉኝ፤ ‹በቤተ ክርስቲያናችን አንድን ሰው ለማስተማርና ከስህተቱ ለማረም አራት ደረጃዎችን ልብ ብሎ ማወቅን ይጠይቃል፤ እነዚህም ደረጃዎች አንደኛ ምክር፣ ሀለተኛ ምዕዳን፣ ሦስተኛ ተግሣፅና አራተኛ ዘለፋ ናቸው› አሉኝ፡፡ እነዚህንም በደረጃቸው መሠረት እያስተዋሉ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ቀጠሉ ‹ምክር የሚሠጠው ሳያውቅና ሳያስተውል ለሚሳሳት ሰው ወይም ሳውያውቅ እንዳያጠፋ ለማደርግ የሚሠጥ ነው፤ ስለኾነም ምክር ወደ ጥፋት እንዳይገባና ስህተት እንዳይሠራ ማድረጊያ ነው፡- ከስህተት ለመጠበቂያ፣ ለማስተማሪያ ነው፡፡ ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን እንዲለይ ‹ልጄ! ይህንን አታድርግ! ከዚህ ይልቅ ይህንን ይህንን ብታደርግ፤ ወይም ይህንን መጽሐፍ አንብብ፣ እንደዚህ ብለህ ፀልይ!› እየተባለ ይመክራል፡፡ በዚህ መልክ የተዘጋጁ የምክር መጽሐፎችም ብዙ ናቸው፤ ለምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች፣ መጽሐፈ-ምሳሌን፣ ሢራክንና መሰሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ነገር ግን ማስተካከል የሚያስፈልገው ስህተት ሠርቶ ከተገኘም ዕርማት ወይም ማስተካከያ ይሰጠዋል፤ ይነገረዋል፤ የተሳሳተውን በመተቸት፣ ትክክለኛውን አርሞ በማሳየት እንዲያስተካክል፤ በማስረጃ ተደግፎ ይገለጽለታል፤ እሱን ተከትለውም ሌሎች እንዳይሳሳቱ ማስተካካያ ይደረግበታል፤ ይህም ምዕዳን ይባላል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን ያጠፋው ዐውቆና በግድለሽነት ከኾነ መቆጣት ያስፈልጋል፤ በዚህም ስህተቱን እንዲያርምና እንዲያስተካክል ተግሣፅ ያስፈልገዋል፤ ምክንያቱም እንዳይመከር ዐውቆ ነው ያጠፋው፤ ማስተካከያ ምዕዳንም ቢሠጡትም ብዙም አያርመውም፤ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሰውን ‹ራስህን አርም!› ብሎ መገሠፅ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህም የማይመለስና የማይስተካከል ከኾነ በፅርፈትና በዘለፋ ከጉባኤው እንዲለይ ይደረጋል፤ የሠራው መጥፎ መኾኑን ብቻ ሳይኾን ኾን ብሎ መፈጸሙ ትልቅ ልቅነት መኾኑን በፅርፈት መልክ ይነገረዋል፤ ጉባኤውን ከማበላሸትህ በፊት ወደ ጥፋት አባትህ ዲያቢሎስ ጋር ሒድ ይባላል፤ ‹ምከረው ምክረው እንቢ ካለ መከራው ይምከረው› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡› ካሉኝ በኋላ የኹለቱን ሊቃውንት አቀራረብ ልዩነት ከዚህ ጋር አያይዘው አስረዱኝ፡፡

‹አንተ እንዳልከው ኹለቱ ሊቃውንት መልሱን የሰጡበት አቀራረባቸው ይለያያል፤ አለቃ አያሌው ‹እርኩስን እርኩስ ካላሉት የቅድስናን ሥፍራ ይይዛል› የሚል አቋም ይዘውና ካቶሊኮች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር በውግዘት ከተለያዩበት ከ451 ጀምሮ የሚያገናኛቸው ጉዳይ የለም በማለት አቀራረባቸው ፅርፈታዊና ‹አይመለከትህም› በማለት ላይ የቆመ ነው፡፡ ስለዚህ አባ አየለን በማማጣጣልና በመወረፍ ላይ ያዘነበሉ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ክርክራቸውን በመጨረሻው ደረጃ በ‹ዘለፋ› ላይ ማድረጋቸውን ይነግረናል፡፡ ይኹንን አንዱን ብቻ ይዞ መሔድ ስለማይቻል፤ በክርክራው ውስጥ ምዕዳንና ተግሣፅም አሉበት፤ ይህም ያዘጋጀውን ሰው ለመመለስ ሳይኾን አንዳንድ ጥያቄ የሚያስነሱና የሚያሰናክሉ ያሏቸውን ሳይመልሱና ሳያርሙ ቢተዋቸው ሌሎች አንባቢዎች ባለማወቅ ይሣሣቱበታል ብለው ይመስለኛል፡፡ ምሳሌ ልንገርህ አባ አየለ ‹ኢትጵያውያን ክርስቶስ ኹለት ባሕርይ አለው ሲባሉ፤ አራት እግር፣ አራት እጅ አለው የተባሉ ይመስላቸዋል› ላለው ሐሳብ ሲመልሱ ምን አሉ መሰለህ፤ ‹አባ አየለ በዚህ መገረሙ ይገርማል ምክንያቱም አካል የሌለው ባሕርይ እንደሌለ ይታወቃል፤ ይህ ከኾነም አባ አየለ ክርስቶስ ኹለት ባሕርይ አለው ካለ ኹለት አካላት አሉት ማለቱ ነው፤ ኹለት አካላት ካሉትም አራት እግሮች፣ አራት እጆች አሉት ማለት ስለመሰላቸው መገረሙ ይገርማል› አሉት፡፡ አኹን እዚህ ላይ የምታየው ለምን እንደሚባልና የእሱ ትክክለኛ ስህተት ምን እንደኾነ በማብራራት አይደለም የሞገቱት፤ እሱው በሰጠው ላይ ተመሥርጠው ‹የማታውቀውን አትፈትፍት› ማለታቸው ነው፤ ሌሎችም እንዳይሳሳቱ አገላለፁ ስህተት መኾን አሳይተውበታል፡፡ የመልአከ ብርሃን አድማሱ መልስ አሠጣጥ ግን ለዘብ ያለ ነው፤ ወደ ዕዝናትና ተግሣጻት ያዘነበለ ነው፤ ዘለፋ ላይ አልሔዱም፡፡

መልአከ ብርሃን ስገምት ሰውየውን በመዘለፍ የሚገኙው ጥቅም ዐልታያቸውም፡፡ ስለዚህ የእሱን መጽሐፍ ያነበቡ ሰዎች እያመዛዘኑ እንዲረዱላቸው ወደ ማረምና ማስተካከል ነው ያተኮሩት፡፡ ስለዚህ እሱ የጻፈውን መስመር በመስመር እየተከተሉ ‹ይህ ልክ ነው፤ እንዲህ ካልከው ጋር ግን አይስማማም፤ ይህ ስህተት ነው፤ የእኛ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ አታምን፣ አታስተምርም› በማለት እርማትና ማስተካከያ ያቀርባሉ ወይም ‹የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህንን ይህንን በማመኗና በማስተማሯ ስህተት ነው፤ ከእኛ እምነትና አስተምህሮ በዚህ ምክንያት አይስማማም› እያሉ ይሟገታሉ እንጂ ወደ ጽርፈት አያዘነብሉም፡፡ ይህንንም ያደረጉት ከመጽሐፋቸው ርእሰ ‹መድሎተ-አሚን ከሚለው እንደምንረዳው መጽሐፉን የሚያነቡት ሰዎች አመዛዝነው እንዲረዱላቸው በመፈለግ ይመስለኛል፡፡› አሉኝ፡፡

‹በሌላ በኩልም አለቃ አያሌው የመልአከ ብርሃን አድማሱ የቀለም ልጅ ስለነበሩ በደንብ ይተዋወቃሉ፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ መልስ ሳይኾን አለቃ አያሌው ቀድመው መልስ ሰጡ ከዚያም መስተካከልና መተቸት አለበት ያሉትን መልአከ ብርሃን አድማሱ ተጨማሪ አቀረቡ፤ እናም በዚህ መልክ ነው እኔ የማየው› አሉኝ፡፡

እኔም ምስጋናየን አቅርቤ ተለየኋቸው፡፡ ኹለት ነገሮችን ግን ተገነዘብኩ፤ ከሊቃውንት ጋር ጠጋ ማለት ዕውቀትን ከምንጩ መቅዳት መኾኑንና አስተያየት ስንሰጥ ለማንና እንዴት መኾኑን ማጤን እንደሚያስፈልግ ተረዳሁ፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply