ፍልስፍና-ቅኔ (ጥበበ-ቅኔ) ፪

(በከሣሁን ዓለሙ)

መጀመሪያ ይህንን link ማንበብ ጠቃሚ ነው፡፡

ቅኔ ለምን ከኹሉም በላይ የሚታይ ዕዉቀት ኾነ? ነዉ ሊቃውንቱ ከዚያም ባለፈ እንደእነ ከበደ ሚካኤልና መንግሥቱ ለማ ዓይነት ምሁራን ቅኔን የሚያገኑት ሌሎችን ዕዉቀቶች ካለመረዳት ይኾን? እንደ እኔ ግንዛቤ ሌሎቹን ካለመረዳት አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም የቅኔ ድንቅነትን ስለተገነዘቡ ይመስለኛል፤ ዋና ጉዳያችን ግን የእነሱ ልቅና ሳይኾን የቅኔ ዕውቀት ምጥቀት፣ ስፉህነትና መሠረታዊነት መመርመር ነው፡፡

ከኹሉም በፊት ከዚህ በፊት እንደጠቀስነው በሀገራችን ሊቃዉንት ቅኔ የተለየና የተከበረ ዕዉቀት መኾኑን እናዉቃለን፤ ይህ ከኾነ ‹ቅኔ እንዴት የተለየና የተከበረ ዕዉቀት ሊኾን ቻለ? የቅኔ ልዩ ፍልስፍና ምንድን ነዉ?› በሚል ጥያቄ ተነሥተን እንመርምር፡፡ ‹ቅኔ ሆይ! ፍልስፍናዬ ምንድን ነዉ ትላለህ? ነዉ ለፍልስፍናም ወላጁ እኔ ነኝ ባይ ነህ?›

በእነዚህ ጥያቄዎች በመመሥረት የቅኔን ዕሳቤና ምጥቀት ከተለምዷዊ ዕይታ መጠቅ አድርገን ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ከመጀመሪያዉ ጥያቄ በመነሣት እየፈተሸን እንሂድ፡፡ የሀገራችንን የግዕዝ ቅኔ ፍልስፍና ማርዬ ይግዛዉ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡

ቅኔ ራሱ ሙሉ በሙሉ ምርምር እና ፍልስፍና ነዉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የዘርፉ ባለሙያዎች ከአብዛኛዉ ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ወጣ ባለ መንገድ ማሰብና የሚፈልጉትን መልእክት በምሥጢር በመሰወር ሌላዉ ሰዉ በሚያዉቀዉ ቋንቋ የሚነገረዉን ነገር እንዳይገባዉ አድርጎ ምሥጢር ማስተላለፍ የሚያስችል ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡

የሚነገርበትን (የግዕዝ) ቋንቋ በሚያዉቁ ሰዎች መካከል እንኳ አንድ ሰዉ የሚፈልገዉ ሰዉ ብቻ እንዲገባዉ አድርጎ ለመናገር ማስቻሉ ቅኔን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ጋር በአስተሳሰብ ወጣ ያሉ ፍጹም በተለመደዉ መንገድ ለማሰብ የሚያስቸግሩ ሐሳቦች ላይ በመፈላሰፍ  የቅኔን ያህል የፍልስፍና እና የምርምር ስልት ያለ አይመስልም፡፡[1]

በዚህ ሐተታ ማርዬ ፍልስፍናዉን አድንቆ ጠቁሞናል፤ የበለጠ ሊታይም ይገባል፡፡ መጋቤ ምሥጢር ወልደሩፋኤልም የቅኔን ጥልቅና ምጡቅ ዕዉቀት መኾን ሲገልጹ ‹ቅኔ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜና ምሥጢር መፈተሻ፣ የአእምሮ ማደሻ፣ የዕዉቀት ማጎልመሻ፣ የምርምር ዋሻ ነዉ፡፡›[2]ይላሉ፡፡ በጥቅል የተቀመጠ ግሩም ገለፃ ነዉ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሱ እዮብም የኢትዮጵያን ቅኔ የሚያውቅ ይመስላልና ልብ ብላችሁ ተመልከቱልኝ፤ እንዲህ ብሏል፡-

…ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው?

የማስተዋልስ ሥፍራ ወዴት ነው?

ሰው መንገዷን አያውቅም

በሕያዋን ምድር አትገኝም፡፡…

ስለ ዛጎልና ስለ አልማዝ አይነገርም፣

የጥበብ ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ ይበልጣል፡፡

የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፣

በጥሩ ወርቅ አትገመትም፣

ከሕያዋን ኹሉ ዓይን ተሠውራለች፣

ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች፡፡

(ኢዮብ፡ 28፣ 12-21)

እንደ እኔ እምነት ‹የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን› ሊባል የሚገባው ትልቁ ጥበቧ ቅኔዋ ነው፤ ታዲያ! እዮብ በዚህ ንግግሩ የጥበብን ምንነት ለመግለፅ የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን የኾነዉ የቅኔ ጥበብም አልበቃ ያለዉ አይመስላችሁም? ስለኾነም ቢያንስ ማነጻጸሪያ የኾነዉን የቅኔን ቶጳዝዮን አስደናቂነት መረዳት ግን የጥበብን ምንነት ለመረዳት አቅራቢያዉ ይኾናል፡፡ ስለዚህ ይህንን ልዩ የኾነ ፍልስፍና እንደአቅም መመርመራችንን እንቀጥል፡፡

ከመሠረታዊ ትርጓሜዉ ስንነሣ ‹ቅኔ አእምሮን ለምሥጢር ማስገዛት› የሚል ይዘት እንዳለዉ ተመልክተናል፡፡ ይህ ከኾነም አእምሮ ምሥጢር የሚባል ተቆጣጣሪ አለዉ ማለት ነዉ? አንድ ፈላስፋ ግን ‹ከአእምሮ የሚበልጥ ምንም ነገር የለም፤ ነገሥታት በሕዝብ ላይ ይፈርዳሉ፤ ዐዋቂዎች ደግሞ በነገሥታቱ ላይ›[3] ብሎ ነበር፤ እንዲሁም ‹አእምሮም የነፍስ መኖሪያ ቦታ  ናት፤ ነፍስም የማስተዋል ኃይል ናት፡፡ ሰው ሁሉ ክብር ሥጋዊንና ክብር መንፈሳዊውን የሚያገኘው በአእምሮና በጥበብ ነው›[4] ያለ ፈላስፋም አለ፡፡ ቅኔ ግን አእምሮን መቆጣጠሪያ ምሥጢር ካለዉ የዐዋቂዎቹ ዕዉቀት መለኪያዉ ቅኔ ሊኾን ነዉ፡- ቅኔ አእምሮን በልጦ ወይስ ለአእምሮ ታዞ? አእምሮ እንዴት ነዉ ግዛቱን በምሥጢር የሚያስጠብቀዉ? (ጉድ በል ባለአእምሮ!)

የሰዉ ልጅ አእምሮ ሰፊና ምሥጢራዊ ግዛት ነዉ፤ በዚህም አእምሮዉ ተቆጣጥሮ ግዛቱን መምራት የሚችለዉ የዚህ ምሥጢር መፍቻ ሥርዓት ሲኖረዉ ነዉ፤ ይህ ሲኾንም የመግዛት ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ይችላል፡፡ በዚህም ቢኾን አእምሮዉ ሊያዉቃቸዉና ሊመረምራቸዉ የሚተጋባቸዉ ነገሮች (ሐሳቦችም) እየተመሰቃቀሉ፣ እየተደበላለቁና አፈትልከዉ እያመለጡ አንገዛም በማለት ስለሚያስቸግሩት የአስተሳሰብ ጦርነት (ትግል) ይፈጠራል፡፡ እጓለ ገ/ዮሐንስ የትምህርት ዓላማዉ የሰዉ ልጅ ሕሊናን (አእምሮ) በሕግ-ሥርዓት መመራት ማስቻል መኾኑን በመግለጽ ‹ሕሊና አኮፋዳ አይደለም፡፡ እውነተኛ ጠባዩ ሕግ ሥርዓት ነው፡፡ ለሕሊና ዋናው ጠላቱ ድብልቅልቅና ዝብርቅርቅ ነገር ብቻ ነው፡፡ ዓላማውም ይህንን ለማጥፋት ነው፡፡… የዚህ የተዋበው ዓለም ሠራዒ መጋቢ ሕሊና ነው…፡፡[5] ይላል፡፡ ምክንያቱም ዓለም ለሰዉ ልጅ የሚያስፈልጉት ፍጥረታት (ሐሳቦች) አንገዛልህም በማለት የሚያምጹባት (ያመጹባት) ሥፍራ ነች (እንደ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ አባባል የሰዉ ልጅ ገዥነቱን ለማስጠበቅ፣ ፍጥረታት (ምድር) ደግሞ ተገዥ ላለመኾን በትግል ዉስጥ ይኖራሉ)፡፡ እንዲሁም የሰዉ ልጅ የራሱ የስሜት ሕዋሳትና የተለያዩ ፍላጎቶች ወጥረዉ የሚያስጨንቁት፣ ስብዕናዉ የጦርነት ሜዳ የኾነ ፍጡር ነዉ፡፡ ይሁንና የአእምሮ ግዛት ሰፊ ስለኾነና ኃይልን ስለታደለ የአእምሮዉን ኃይል ተጠቅሞ፣ ስሜቶቹንና ፍላጎቶቹን ወይ ጨቁኖ ወይም አጣጥሞ ግዛቱን ለማስጠበቅ ይጥራል፡፡

‹ከአእምሮ የበለጠ መዝገብ፣ ከእውነት የቀና መልክተኛ የለም› [6]እንዲሉ፤ አእምሮዉ በሐሳብ ግዛት ስፋት፣ ዉስብስብነትና መስተጋብር ሲጨነቅም የቅኔ ምሥጢር ዉል እያስያዘና እያጣጣመ ሐሳቦቹን በማደራጀት ለአእምሮዉ ያስገዛለታል፤ እውነቱን በሥርዓት በመለየት ከሐሳቦቹም የተሻለ ወይም የሚበልጥ ሐሳብ ያለዉ የገዥነትን ሥልጣን ያገኛል፤ ትናንሽ (ንዑሳን) ሐሳቦች በተገዥነታቸዉ ለትላልቁቹ ግብዓት ይኾናሉ፤ ‹የንዑሳን መብት መከበርና የብዙሓን ገዥነት› በሐሳብ ግዛትም ዉስጥ ይሠራልና፡፡ በዚህ መስተጋብርም አእምሮዉ የሐሳብ ግዛቱን ሰላምና መረጋጋት ጠብቆ ለሌሎችም በአርአያነት በመትረፍና በኃላፊነት በመቆጣጠር ይኖራል፤ ስለዚህ ቅኔ ማለትም አእምሮ ይህንን ግዛት የሚቆጣጠርበት ጥበብ ነዉ፡- ቅኔ የአእምሮ ሕገ-መንግሥት፡- አእምሮ የሚገዛበትም የሚገዛበትም ሥርዓት ነዉ፡፡

በእዚህ ላይ አእምሮና የሚታሰቡ ሐሳቦች የተለያዩና የተያያዙ በመኾናቸዉ በማሰቢያዉ አእምሮና በሚታሰበዉ የሐሳብ ዓለም መካከል ገዥና ተገዥ ኹለት ነገሮች ተፈጥረዋል፤ የማሰቢያ ስሜቱ ሕሊናም ትክክለኛነቱን ይመዝናል፡፡ እንደ አንድ ሕገ-መንግሥት የቅኔ ምሥጢር በእዚህ ምንታዌ ላይ እየፈለቀም አእምሮን ለምሥጢር ሕገ መንግሥት ተገዥ በማድረግ ግዛቱን ይቆጣጠራል፤ ይመራል፡፡ በአእምሮና በሐሳቦቹ መካከል ባለዉ የእገዛለሁ-አልገዛም ግብግብም የቅኔ ተግባር ሕሊናን የምሥጢሩ ባለቤት ማድረግ ነዉ (ቅኔ የአእምሮ ወገንተኛ ነዉ፤ የምሥጢሩን መፍቻ ቁልፍ ይሠጠዋልና)፡፡ ይህ ምሥጢርም በድንቀት ጥበብን በመፍጠሩ የቅኔ ፍልስፍና ማጠንጠኛ ነጥብ ኾኗል፡፡ ስለዚህ ቅኔ አእምሮን ተቆጣጥሮ ለጥበብ ምሥጢር በማስገዛት ኃያልና የምሥጢራት መፍቻ አድርጎታል፡፡ አሁን ወደ ዋናው ጥያቄ እንለፍ (ታገሱኝ እባካችሁ! ገና ነን እኮ!)

ከላይ የጠቀስነዉ የቅኔ ሥርዎ-ቃላዊ ፍልስፍና እንደተጠበቀ ኾኖ አእምሮን የሚቆጣጠረውን የቅኔን የዕዉቀት ዳራ ይዘት ሲያስተዉሉት በተፈጥሮ ምሥጢር ተቃኝቶ፣ በኅብርነት፣ በዕምቅነትና በለዛዊነት ዙሪያ የሚሸከረከር ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ፍልስፍና በድንቀት ላይ የተመሠረተች ፍቅረ ጥበብ ናት፤ ቅኔ ደግሞ በተዋህዶ የከበረች የምሥጢር ቤት መኾኑ ይታወቃል፤ ፍጥረታት ኹሉም በተፈጥሯቸዉ በቅኔ የተቃኙ ናቸዉ፡፡ ቅኔነታቸዉም የተሸመነ ኅብርነት፣ ተፍታትቶ የማያልቅ ዕምቅነት፣ ለዛና ዜማዊ ቃና እንደያዘ፣ በስምም ቀለም ተሰንዶና በመዓዛ ሰምሮ ይገኛል፤ በተለይም ኅብረነቱና ዕምቅነቱ ቅኔነትን በግልጽ የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ ይህንን ቅኔነት ለማወቅም የሚጠይቀዉ የፍጥረትን ክሳቴና ተፈጥሮ ማስተዋል ነዉ፤ በዚህ ዙሪያ ለማሳያ የሚኾኑ ዉስን ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

‹የቅኔ ዋነኛ መሠረቱ የሰምና ወርቅ[7] ምሳሌ ነዉ፡፡›[8]ይላሉ አለቃ አፈወርቅ ተክሌ፡፡ የተፈጥሮ የቅኔ አፈጣጠርም በዚህ ላይ ይሸከረከራል፡፡ ፍጥረት ስንል ራሱ ቅኔ ነው፤ ምክንያቱም ‹ፍጥረት› በሚለው ቃል ውስጥ ፈጣሪነትና ተፈጣሪነት ተዋህደው ይገኛሉና፤ ማለትም ‹ፍጥረት› ማለት የተፈጠረ ማለት ነው፤ የተፈጠረ ስንልም በውስጡ የፈጠረው (አድራጊና ተደራጊ ወይም ሠሪና ተሠሪ) መኖሩን መግለጻችን ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ተፈጥሮ ምሥጢር ስንናገር በሰምነት ስለፍጥረታት ብንገልጽም ፈጣሪው በሥውር (በወርቅነት) ይመሠጠራል፤ የአገራችን ባለቅኔዎችም (ፈላስፎች) በቅኔ መነጽራቸው የሚታያቸው ይህ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ሰሙን ስናይ ስለ አጽናፈ ዓለም ህላዌ፣ ሥፋት፣ ውስብስብነት፣ መስተጋብር፣ የሕይወትና የዓለማት የህላዌ መስተጋብር፣ ወዘተ… እንናገራል፤ ይህንን ለማወቅና ምሥጢሩን ለመፍታት እንጥራለን፡፡ ወርቅ የኾነ ምሥጢሩን ለመፍታት ስንሞክር ደግሞ ስለ ፈጣሪ (አምላክ) ፈጣሪነት፣ የፍጥረታት ጠባቂነትና ከፍጥረታት ጋር ስላለው መስተጋብር፣ ከዚያም አልፈን ስለ ህላዌው፣ ስለ መታወቂያዎቹ (በኃይሉ፣ በዕውቀቱ፣ በሞራሉ፣ በስፋቱ፣ በርቅቀቱ፣…)፣ ወዘተ… አእምሯችን እስከቻለው ድረስ እንመረምራለን፡፡ ለምሳሌ ፈላስፋው ዘርአ ያቆብ ይህንን ሲያመሠጥር ‹ፍጡር አለፈጣሪ ሊገኝ እንደማይችል ፈጣሪ አንዳለ ግን እውነት ነውና ይህ የምናየው ኹሉ ፍጡር እንደኾነው የሰው ልቦና ያውቃል፡፡[9] ይላል፤ ከእሱ ጋር ተስማሚ በኾነ ገለጻ ተማሪው ወልደሕይወትም ‹አለፈጣሪ ፍጡር እንዴት መኾን ይቻላል?›[10] በማለት ይጠይቃል፡፡ በአጭሩ ሰንገልጸው ተፈጥሮ አጽናፈ-ዓለምና ፍጥረታቱ ሰም፣ ፈጣሪ (አምላክ) ደግሞ ወርቅ ኾነው በቅኔነት የሚገኙበት ምሥጢራዊ ነገር ወይም ቅኔ ነው፡፡ ይህም ሊቃውንት አንድን ቃል ወይም ስም (መጠሪያ) ሲሰይሙ በቅኔያቸው አመሥጥረው (ሰምና ወርቅን አዋህደው) መኾኑን ያሳየናል፡፡

በዚህ መልክ ድንቅ ምሥጢር የያዠውን ይህንን ቅኔ መመርመር ባንችል (ቅኔው ረቆብን ማመሥጠር ቢያቅተን) እና ‹ሰም ነው› ባልነው የተፈጥሮ ክስተት ላይ ብቻ ብንቸከል እንኳ (ምናልባት ‹ፍጥረት› በሚለው ቃል ውሰጥ የእግዚአብሔር በወርቅነት የሚገኝ መኾኑን መረዳት አቅቶን ወይም ሳንፈልግ ቀርተን) ከዚያ መለስም የጊዜና የሥፍራን ኅብርነት (ቅኔነት) እናገኛለን፡፡ እንደሚታወቀው ፍጥረት ኹሉ ህልዉናዉን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በጊዜ የሚለካ (ዕድሜዉ የሚቆጠር) እና በዉህድነት ሥፍራ ይዞ የሚገኝ መኾኑ (በtime & space መሠራቱ) ቅኔነቱን ይመሰክራል፤ በዚህም ዉህዳዊ ክስተቱ በአካል የሚገለጽ ሲኾን ዕድሜዉ ግን ሥዉሩ የዚያ ነገር መለኪያ ነዉ፤ ስለዚህ ክስተቱን ሰም ጊዜዉን ደግሞ ወርቅ ልንለዉ እንችላለን፤ ይህ ከነጥብ እስከ አጽናፈ-ዓለም ስፋት ያለው ሥፍራ ከቅፅበት እስከ ዘላለም ባለ ጊዜ የሚለካበት የሰምና ወርቅ ተዋህዶ-ምሥጢር ነው፡፡ ሰሙ የወርቁን ቅርፅ አሠርቶ እንደሚጠፋዉ ክስተትም የሥፍራን ቅርጽ፣ ይዘት፣ መልክና መጠን ይዞ ይከሰታል፤ ክስተቱም በሥፍራ፣ በኹኔታና በጊዜ ገደብ እየተመዘገበ ይጠፋል፡፡ ለምሳሌ ከታሪክ ክስተቶች ብንጠቅስ፣ የአድዋ ጦርነት ማሳያ ሊኾነን ይችላል፤ የአድዋ ጦርነት በአንድ ቀን ዉሎ የተከናወነ ክስተት ነዉ፤ በእለቱ የተመዘገበዉ ክስተት ግን ለዘመናት እየታወሰ ይኖራል፤ ይህም ወርቁ የሰሙን ቅርጽ ይዞ እንደሚቀረዉ ክስተቱም የአንዱን ቀን ዉሎ ይዞ ይታወሳል (ይታወቃል)፡፡ በዚህ መልክ የሰዉን ዕድሜም ኾነ የሌሎችን ፍጥረታትን መከሰት ከቆይታ ጊዜያቸዉ ጋር በማገናዘብ መረዳት ተፈጥሯዊ ነዉ፡፡ በዚህም ከሥፍራ ጊዜ ስለሚረቅ ሥፍራ የያዘ ክስተት እንደ ሰም ሊወሰድ ሲችል፤ የክስተቱ ዕድሜ ወይም የጊዜ ቆይታው ግን እንደወርቅ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለዚያም ነዉ ከአምላክ ወዲህ ያለው ፍጥረትም ቅኔ ነዉ የምለው፡፡

ይህም ብቻ ሳይኾን የፍጥረትን ቅኔያዊነትም ክስተቱን ብቻ ለይተን ብንወስድ የክስተቱ (የፍጥረት) ምንነት በእርግጥነት (actuality) እና በዕምቅነት (potentiality) ተዋህዶ እናገኘዋለን፤ በዚህም ፍጥረት ኹሉ በዕምቅ ተፈጥሮ ይለዋወጣል፤ በእርግጥነቱ ግን ፀንቶ ይኖራል፤ በዕምቅነቱ ውስጥ እርግጥነቱን መርምረን እናዉቃለን፤ የሚቀጥለዉን ኹነት በመረዳት ሥዉራዊ ምሥጢሩን እናመሠጥራለን፤ በዚህም ዕምቅነቱ ሰም ሲኾን እርግጥነቱ ደግሞ ወርቅ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም ከፍጥረታት መካከል አንድ አካል ነሥቶ የተከሰተ ነገር ‹ዕምቅ ተፈጥሮ›ና ‹እርግጥ ተፈጥሮ› ይነረዋል፤ ይህም በአካላዊ ተፈጥሮዉ በኋኝነት የሚገኝበት ኹኔታና ወደፊት የሚኾነዉ ናቸዉ፤ የወደፊቱ በዕምቅነት ይገኛል፤ የአሁኑ ደግሞ በአካልነት ተገልጽዋል (ያልተገለጸና የተገለጸ ማለት ነዉ)፤ ስለዚህ አንድ ህልዉ ነገር የእነዚህ ተፈጥሮዎች ዉህድ ነገር መኾኑ ፍጥረት ኹሉ በቅኔነት የሚኖር መኾኑን ይገልጽልናል፡፡ ስለዚህ ከፍጥረታት መካከል በዕምቅነትና በእርግጥነት ዉህደት የማይገኝ ወይም የኀብርነት ተፈጥሮ የሌለው ልሙጥ የተፈጥሮ ክስተትም የለም፡፡

እዚህ ላይ ግን ‹ዕምቅ ተፈጥሮው ሥውር፣ እርግጡ ግን ግልጽ አይደለም ወይ? ይህ ከኾነስ ዕምቅነትን በሰም እርግጥነትን ግን በወርቅነት ለምን እናመሠጥራል?› የሚል ጥያቄ ዐይኑን አፍጦ ሊመጣብን ይችላል፡፡ ኾኖም ገለጻው ወርቃወርቅነት መኾንና የሐሳቡ ክብደት ለመረዳት ከብዶን ነው እንጂ ክስተት ኹሉ ተለዋዋጭና ቋሚነት የሌለው መኾኑን እናዋቃለን፤ ፍጥረት ኹሉም በዚህ መልክ የሚገኝ ከኾነ እርግጥነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባብናል፤ በመኾኑም የክስተትን ምንነት የምንረዳው ቋሚነት ባለው ባሕርዩ ነው፤ ባሕርዩ ደግሞ ከእርግጥ ተፈጥሮው ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይህም ወደሚቀጥለው ምሥጢር የሥነ-ህላዌ ምሥጢር ምርምር ይዞን ይሄዳል፡፡

የትኛዉም ፍጥረት አካልና ባሕርይ ይኖረዋል፤ አካሉ መገለጫዉ ሲኾን ባሕርዩ ደግሞ ያ አካል (በሥዉር) እሱነቱ እንዲታወቅ የሚያደርገው ነዉ፤ ይህም ከቅኔ የሰምና ወርቅ ወይም የኅብርነት ተፈጥሮ (ባሕርይ) ጋር ይመሳሰላል፡- አካል ሰም፣ ባሕርይ ወርቅ በመኾን፤ ባሕርይ አካልን በማስነበብ አርግጥ ኾኖ በቋሚነት ይቆያልና፡፡ ስለዚህ የአካልና የባሕርይ ግንኙነት ድንቅ ምሥጢር የያዘ ቅኔ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ የሰውን ልጅ የነፍስና ሥጋ ተዋህዶንም ስንመረምር  ድንቅ ምሥጢር ያለው ቅኔን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ሕይወትም በሥጋ ሰምነት የተሠራ የነፍስ ምሥጢር ወርቅ ኾኖ ይፈታበታል፤ ሥጋችን ተለዋዋጭና በግዝፈት የሚገኝ ሰም ነውና፤ አገልግሎቱም የነፍስ መኖሪያ መቅረጫ መኾን ነው፡፡ እዚህ ላይስ እጓለ ገ/ዮሐንስን ልጥረው፤ ንገረን እስቲ!፡

ሰው በሁለት ዓለማት መካከል የሚገኝ አማካይ ፍጥረት ነው፡፡ በአካሉ የጉልሁ ዓለም ተካፋይ ነው፡፡ በመንፈሱ የረቀቁ የዘላለማዊ ዓለም ተሳታፊ ነው፡፡… የፍልስፍና መንፈስ እነዚህን ሁለት ነገሮች መርምሮ ስለመላው ዓለምና ስለሰው ሕይወት ትክክለኛና በሕገ-ምክንያት የተመሠረተ አስተያየት ለማቅረብ ይጣጣራል፡፡[11] ብሏል፡፡

ከተለመደው ፍልስፍና አንጻር ብንመለከት ደግሞ የሰው ልጅ የአካልና የሐሳብ ተዋህዷዊ ምሥጢር እንቆቅልሽ ኾኖ ይገኛል፡፡ በመኾኑም በሐሳቡ ርቅቀትን እየመረመረ በሥጋዉ ገዝፎና ተወስኖ የሚገኝ መኾኑ የሰዉን  ተፈጥሮ ቅኔ ያደርጋዋል፡፡ ይህም የሰዉ ልጅ በሐሳብና በአካል ወይም በነፍስና በሥጋ ተዋህዶ የሚገኝ ፍጡር መኾን የዕንቆቅልሻዊ ተፈጥሮዉን ገና አለመፈታትና ጥልቅ ምሥጢርነቱን ይነግረናል፡፡

ከዚህ አንጻር ሲታይ የትኛዉም በህልዉነት የሚገኝ ፍጥረት በቅኔነት የሚገኝ መኾኑን አመሥጥሮ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምናልባት ያላስተዋለ ሰዉ ብዙ ሊጨቃጨቅበት ይችላል እንጂ ይህ መሠረታዊ የተፈጥሮ ቅኔነት ማሳያ ነዉ፡፡ አስተዋይ ሰዉም በድንቀት ተመሥጦ ምሥጥሩን ለመፍታት ይጥርበታል፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸዉ የተፈጥሮ ቅኔነትም ለፍልስፍናም የምሥጢረ-ፍጥረት (Metaphysics) እና የምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) ጥናቶች ማጠንጠኛ መሠረቶች መኾናቸዉን ልብ ማለት ጠቃሚ ነዉ፡፡ የቅኔ ፍልስፍናነትም በዚህ በጠቀስነው የሰምና ወርቅ እሳቤ ላይ ስለተመሠረተ ኅብርነት ዋናው የማጠንጠኛ ምህዋሩ ነው፤ ኅብርነቱ ደግሞ በተፈጥሮ ላይ ብቻ ሳይኾን በቋንቋ ዉክልናም ይገኛል፤ ይህም የተፈጥሮ የኅብርነት ምሥጢር በቋንቋ እንዴት እንደሚገለጽ መመርመርን ይጋብዛል፡፡

ከላይ በተለያየ ማሳያ እንደተመለከትነው ቅኔ በተፈጥሮዉ ኅብር ስለኾነ፤ በኅብረ-ትርጓሜ የተቃኘ ነዉ (ይህ ዋና ነጥብ ነዉ)፡፡ ይህም ኅብራዊነት ከተፈጥሮ ሥሪት ጋር የተናበበ፣ በሥዉርነትና በግልፅነት ተዋህዶ የተቀመመ፣ ሥጋዊነትንና መንፈሳዊነትን አዋህዶ የያዘ፣ አማን ከጥላ፣ ትንቢት ከአሁን፣ እዉን ከምሳሌ፣… የለየ፣… ነዉ፡፡ ይህ በቋንቋም አጠቃቀም ሰምና ወርቅን አጣምሮና አስተሳስሮ በመያዝ ሰሙን ተጠቅሞ ወርቁን አንጥሮ በማሠራት የሚያሳዉቅ፣ በዚህም ሥዉርነትን ለመግለጽ አስቸጋሪ የኾነዉን በግልጽና በገሐዳዊ ነገር ሠርቶ የሚያስረዳ ነዉ፡- ቅኔ፡፡

‹የኅብር አገር ጎጆ መግቢያና መዉጫዉ፣

ሊቃዉንት የሠሩት ኹለት በር አለዉ፤

ምንም ኹለት ቢኾን ሦስት አራትም፣

ጠባብ ስለኾነ ደንቁር አይገባም፡፡›[12] ይሉታል ዓለማየሁ ሞገስ፡፡

የቅኔ ኅብርነትም ዕምቅነትንና ለዛን ይሰጠዋል፤ የተመጠነና የተመረጠ ቃላትን፣ አግባባዊ ምሳሌንና ሰዋሰዋዊ ሥርዓትን በመጠቀም እንደ ወርቅ የነጠረና የፈረጠመ ሐሳብን እንዲገኝ ያደርጋል፡፡ ‹የንግግር ለዛዉ ማሳጠር ነዉ› እንደሚባለዉም ሐሳብ ‹እንደ ወርቅ ተንከብሎ፣ እንደሸማ ተጠቅልሎ› ይቀርብበታል፡፡ ለምሳሌ የሚከተለዉን የጉባኤ ቃና ቅኔ የተቀኘ ሊቅ ምን ያህል መጥቆና መጥኖ እንደተቀኘና በአምላክ ድንቅ ሥራ ሲደነቅ እንደኖረ መገመት አይከብድም፡፡

‹በምንት ቆመት ማርያም እኅተ ሙሴ ወዮሣ፣

ሰማይ ወምድር እስመ ተሰዉሩ በከርሣ፡፡›

ትርጉም፡-

የሙሴና የዮሳ እኅት ማርያም በምን ላይ ቆማለች፣

ሰማይና መሬትን በሆዷ ዉስጥ ከሰወረች፡፡

የቅኔውን ምሥጢር ከማየታችን በፊት ከዚህ ቅኔ ጋር የሚመሳሳል አንድ የብሉይ (የቆየ) የጀርመኖች አባባልም አለ፤ እሱን እንይ፤ እንዲህ ይላል፤ ‹ቅዱስ ክርስቶፈር ክርስቶስን ተሸክሟል፣ ክርስቶስ ደግሞ ዓለምን ተሸክሞ ይገኛል፤ ግን ክርስቶፈር ምን ላይ ቆሞ ነዉ ይህ የኾነዉ?›፤ አገላለጹ ስለ መንሥኤያዉነት መነሻ ጥያቄ ያነሣል፤ ‹እግዚአብሔር አጽናፈ-ዓለሙን (Universe) ፈጥሮ የሚያስተዳድር ከኾነ እሱ ምን ላይ ኾኖ ነዉ ይህንን ያደረገዉና የሚያርገዉ?› የሚል ጉምቱ ጥያቄ ይዟል፡፡ በሌላ አገላለጽ ብናየዉ ‹ጫማችን እኛን ይሸከመናል ወይስ የጫማችን ተሸካሚዎች ራሳችን ነን?› የሚል ጥያቄም አብሮት ይሔዳል፡፡ ‹ከጫማ ተሸካሚነት ሠዉረን› አንል ያለጫማ እሾህና ጠጠሩን እንዴት ልንችለዉ ነዉ? በመሸከሙ ከተስማማንም በጫማ ተሸካሚነታችን እንዴት ሞኝ አንባልም?

የግዕዙ ቅኔም ከጀርመኑ አባባል ጋር የሚመሳሰል ከሰሙ እስከ ወርቁ የተራቀቀ ፍልስፍናን ይዟል፡፡ ከላይ የጠቀስነው ባለቅኔም በሰምነት ‹አስቡት እስቲ ሰማይና ምድር በአንዲት ሴት ሆድ ዉስጥ የተቀመጡ ቢሆኑ ሴትዮዋ በምን ላይ ትቆማለች? እንዴትስ ወደ ሰማይ ቀና ልትል ትችላለች?› ብሎ በመጠየቅ ሰማይና መሬት በምን ላይ ቆመዉ ሊገኙ እንደቻሉ እያሰበ በአምላክ ሥራ ይደነቃል፡፡ እና! አዮናዊያንና አቴናዊያን የግሪክ ፈላስፎችስ ከዚህ የበለጠ ምን ጥልቅ የፍልስፍና ጥያቄ ጠየቁ? እንዳዉም እጥር ምጥን በማለት ይህ ፍልስፍና አይበልጥም? እናፍታታዉ ከተባለ እኮ ስንት መጻሕፍት ያጽፋል፡፡ ኾኖም ምንም እንኳን መጥኖና አጥልቆ ቢገልጸዉም ለኢትዮጵያዉያኑ ሊቃዉንት ይህ ሥጋዉና ፊት ለፊት የሚታየዉ አካል እንጂ ስዉሩ ምሥጢር አይደለም፡፡

በኢትዮጵያዉያን ነፍስ የሌለዉ ሥጋ የሞተ ነዉ (ሬሣ በሉት)፤ ስለዚህ የለበሰዉን ሥጋ (ሰሙን) ብቻ ሳይኾን ነፍሱ መኖሯንም መረዳት ይገባል፤ የሚመሠጠረው የነፍስ ፋንታ የኾነው ነውና (ሥጋማ ገዝፎ እያየነው አይደል!)፤ ማለት ከቅኔዉም ዉስጥ የ‹ጨዋ ሰዉ› ያልኾነዉን ምሥጢሩን መቃኘት፣ ዋናዉን የቅኔዉን ፍልስፍና መንፈስ መመርመር ግድ ይላል፡- ወርቁን ማለቴ ነው፡፡ ምሥጢሩም ‹ሰማይና መሬትን ፈጥሮ የሚያኖርና የሚያስተዳድር አምላክ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በማኅፀኗ በማደር ሰዉ ኾኖ መወለዱን ማድነቅ ነዉ›፡- ይህ ጥልቁ የኢትዮጵያዉያ ሊቃዉንት የዕዉቀት ጣሪያና የምርምር ማዕከል ነዉ፡- የክብረ-ተዋህዶ ማጠንጠኛ፡፡ ‹ባንድ በኩል እግዚአብሔርን ሰማይና መሬት አይወስኑትም እያልን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሰውን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ በጠባብና በአጨር ቁመት ተወስኖ እንደማንኛውም ሰው ተፀንሶ ተወልዷል› የሚባልበት የምሥጢረ-ተዋህዶ ጥበብ እንዴት የሚረቅ ነው? ይህ አስደናቂ ምሥጢር የተመሠጠረባት ድንግል ማርያምስ እንዴት ቻለችው? ጉድ እኮ ነው! የትስ ላይ ቆማስ ወስነችው እንበል?… እያለ የሚያደንቅ ይመስላል፡- ባለቅኔው፡፡ ይህም ባለቅኔዉ የቅኔውን ጥልቀት በመመሰጥ ሰማያት አድርሶ በአምላክ ሰዉ ኾኖ መገለጥ ተደንቆ በመመጠንና አይረሴ በማድረግ ማቅረቡን እንረዳለን፡፡ ቅኔዉ እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ አባ ሕርያቆስ፣ እነ ቅዱስ ያሬድና ሌሎች ሊቃዉንት አምላክ ከእመቤታችን ሰዉ የመኾኑን ምሥጢር ያደነቁበትን ምስጋና መጥኖና ሰብስቦ የገለጸ ነዉ፡፡ በዚህ መልክ ቅኔ ጥልቅ ስሜትንና ዕሳቤን አዉጥቶ በመመጠን መግለጫ ነው፤ ድንቅነቱ ከፍ የሚለውም በኀብርነት ከመገለጹም በተጨማሪ በዕምቅነት አጥሮና ተመጥኖ ሲለሚገልጽም ነው፡- ምጥን ያለ ግን ጥልቀቱ ብዙ የሚያመራምር በመኾን፡፡ ከድንጋይ ዓይነቶች የሚከብደው ወርቅ ነው፤ ከወርቅም ደግሞ ዕንቁ ይከብዳል መሰለኝ (እርገጠኛ አይደለሁም)፤ ለዚያም ይመስላል ዋጋቸው ውድ የኾነው፤ ቅኔም እንደዚሁ ነው፡፡

እንደ ሌላ ምሳሌ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን የጉባኤ ቃና ቅኔ (ብዙ ሰው በወሬ ወሬም ቢኾን ስለሚያውቀው) ጨምረን እንመልከተው፡-

ባሕቲቶ ነቢረ እግዚአብሔር ፈርሀ፣

እምኢሀልዎ ንዋም እስመ ዓለም አንቅሀ፡፡

ትሩጉም፡

እግዚአብሔር ብቻውን መቀመጥን ፈራ፣

ካለመኖር እንቅልፍ ዓለምን ቀስቅሷታልና፡[13]

ይህንን ቅኔ ማብራራት በአንድ በኩል ‹ያላሰደጉትን ውሻ መቆንጠጥ› ወይም ያልዋሉበትን ጉዳይ ማስረዳት ይኾናል፤ በሌላ በኩል ለተረዳው ሰው ደግሞ አስጨናቂ ዕሳቤዎችን በማብሰልሰል ለመጨነቅ ይገደዳል፡፡ እንዳው ዝም ብለን እንደፈር፤ የቅኔው የሰምነት ሐሳብ በግልጽ ማሳያ ነው የተጠቀመው፡- ማለትም አንድ ሰው በሌሊት ዓለም የምትባል ሴት ዕንቅልፍ ይዟት በተኛችበት ብቻውን ቁጭ ብሎ ጅቡን፣ ሌባውን፣ አጠቃላይ የጨለማው አደጋ ጣዮች እያሰበ ብቻውን መኾኑ ስላስፈራው ዓለምን ከተኛችበት እንቅልፍ መቀስቀሱን ይነግረናል፤ ይህም ዮፍታሔ ንጉሤ ‹ዓይኔን ሰው ራበው ዓይኔን ሰው ራበው፣ የሰው ያለህ የሰው የሰው ያለህ የሰው› እንዳሉት ብቸኝነት በፍርሃት የተነሣ ‹ሰው ሰው› እንደሚያሰኝ፣ ያለ ሰው ኹሉ ነገር ከንቱ መኾኑን፣ ብቸኝነት ለፍርሃት እንደሚዳርግ፣ ስለኾነም የሰው መድኃኒቱ ሰው ስለኾነ ያለሰው ሕይወት ትርጉም እንደማይኖራት ያስረዳናል፡፡ ለእግዚአብሔር ደግሞ ትልቁ የአጽናፈ-ዓለም ፍጥረት ሰው መኾኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡

የቅኔው ዋናው ጉዳይ (ወርቁ) ግን የአንድ ሰው በሌሊት በብቸኝነት በፍርሃት መጨነቅ ሳይኾን ‹እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ምን ይሠራ ነበር?› በሚል ጥያቄ ‹እግዚአብሔር በባሕርዩ ምስጉን ስለኾነ ዓለም ሳይፈጠር በፊት በአንድነት በሦስትነት ራሱን በራሱ እያመሰገነ ይኖር ነበር፤ ከዚያም ጥበቡን ለመግለጽና ምስጋናውን ለፍጥረቱ ለማካፈል ዐሰበ፤ ዐስቦም አልቀረ ዓለምን ፈጠረ፤ በተለይ ሰውና መልአክትን የምስጋናው ተካፋይ አደረጋቸው› የሚለውን የቤ/ክ አስተምህሮ ነው በምሥጢር የገለጸው:- ቅኔው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አለቃ ዘነብም ‹ኢየሱስ ክርስቶስ ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን ውረሱ ይላል፤ ዓለም ሳይፈጠር ምን ኖሮታል? ጥበቡ አይታወቅ[14] በማለት የአድናቆት ጥያቄ አቅርበዋል፤ የዚህን ቅኔ ሐሳብ በእግዚአብሔር ልጅ ሰው መኾን ጋር አያይዘውም ‹እግዚአብሔር ፈሪ ነው፤ እኛ ብንበድለው ልጁን ልኮ ቀስ ብለህ ተዛምደህ ና ብሎ በልጁ ታረቀን፤ አሁን ምን ያደርጉኝ ብሎ ነው? ለካስ በየቤቱ ፍራት አይታጣም፤ እኛ ስለበደልነው የምንክሰውን እሱ እራሱ ካሠን›[15] በማለት ገልጸውት ይገኛል፡፡ ቅኔውም ኾነ ገለጻው የነቀፉ በማስመሰል የእግዚአብሔርን ጥበቡ መጥነውና አምቀው ማድነቂያ ነው የኾነው፡፡

ከፍልስፍና አንጻር ስንቃኘው የጠቀስነው ቅኔ የስንት ፈላስፎችን አእምሮ ያነኾለለውን ‹አጽናፈ-ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ለምን መጣ?› የሚል ጥያቄን ነው ምጥን አድርጎ የገለጸው፡፡ ዕምቅነቱን ሲያስተውሉትም ‹እግዚአብሔር አጽናፈ-ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር? ምን እየሠራ? ለምንስ አጽናፈ-ዓለም መፍጠር አስፈለገው?› የሚሉትን ጥያቄዎች አምቆ ብዙ መላመቶችን እንድሰጥ ይጋብዘናል፤ ከዚያም ባለፈ ‹እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በፊት ከነበረ ብቻውን መኖሩ ምን ትርጉም ነበረው፤ እንኳን ምንም ሌላ ነገር በሌለበት አንድ ሰው ብቻውን ሲኾን እንኳን መኖሩ ትርጉም አይኖረውም› በሚል ክርክር አጽናፈ-ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሊኖር ስለሚችለው የእግዚአብሔር ማንነት፣ ስለ አጽናፈ-ዓለም አፈጣጠርና የመፈጠር ምክንያት እያነሣን እንድንመራመር ይጋብዘናል፡፡ ይህም ቅኔው ምን ያህል ዕምቅና ጥልቅ ፍልስፍናን እንደያዘ ይመሰክራል፡፡

ቅኔ ዕምቅ ብቻ ሳይኾን በለዛ የተዋበም ነው፤ ለዛውም በዜማ ይገለጻል የማኅሌታይ ያሬድ ዜማ ቅኔን በጣዕመ ዜማ እንዲከሸን አስችሏል፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ‹ቅኔ የያሬድን መዝሙር መስሎ የሚሔድ በዜማ የሚዘመር መኾኑ ታውቋል፡፡[16] ካሉ በኋላ ቅኔ ያሬዳዊ ዜማን አስማምቶ መደረስ እንዳለበት ምክንያቱን እያመሠጠሩ አብራርተዋል፡፡ በለዛዊነት ጥበብ የተቀባ በመኾኑም ቃላትንና ዓረፍተ ነገርን እንደፈለጉ አድርጎ የመጠቀም ችሎታንና የኅብራዊ ፍች ምንነትን ገንዘብ ማድረግ ስለሚያስችል ቅኔ የጨዋታንና የንግግር ለዛን ዉብና ጣፋጭ አድርጎ ያዳብራል፡፡ ስለዚህ ቅኔ የለዛና ቁምነገር ቤት ስለኾነ ሐሳብን እንደፈለገ ጨምቆ በመመጠን፣ በመቀመምና በመኳሸት የማቅረቢያ ስልት ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ በለዛዊነቱም ዉስጥ ሕግን አክብሮ፣ ጸያፍን ተጠንቅቆ፣ የቅኔን ስልትና መንገድ ጠብቆ መግለጽ እንጂ እንደፈለጉ መደንጎር ምጣኔዉንና ኅብራዊ መርሁን አጥፍቶ ያበላሸዋል፤ ስለኾነም ቅኔ ሥርዓትም አለዉ፡፡ ቤት የተሠራለትም ኹሉም ቤቱን ዐውቆ ገብቶ እንዲያርፍበትና ውጭ በማደር የጅብ ድንቁርና መጫዎቸ እንዳይኾን ነው፡፡

እነዚህ የጠቀስናቸው ‹ተፈጥሯዊነት›፣ ‹ኅብርነት›፣ ‹እምቅነት› እና ‹ለዛዊነት› የቅኔ ፍልስፍና ማጠንጠኛ ነጥቦች ናቸዉ፤ እነሱም ከዚህ በላይ እንደጠቀስነዉ ከተፈጥሮና ሥርዓቷ ጋር የተገናዘቡ መኾናቸዉን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ኅብርነትና ዕምቅነት የሌለዉ ፍጥረት የለም፤ በለዛዊነቱም ዉስጥ ምጣኔ፣ ዜማና ዉበት ያሸበሩቅበታል፤ ስለኾነም ቅኔ በኅብርነት ዜማ ጠብቆ፣ በምጣኔ ታምቆና በለዛ ተዉቦ ይገለጻል፤ እጓለ ‹ለቅዱስ ያሬድ ይህ ዓለም በመላ እንደ አንድ ትልቅ ማኅሌት›[17] መኾኑን የገለጸው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ እንዲሁም መቼም ቢኾን አካል ነስቶ በግዝፈት የተከሰተ መልክ፣ ቀለም፣ ቅርጽ፣ ይዘት፣ ከሌላ ጋር የሚፈጥረው የዜማ መስተጋብር ይኖረዋል፤ ፍጥረታት ደግሞ በመስተጋብር የሚገኙ በመኾናቸው ዜማቸው እንደማኅሌት የሚስማማና የሚመሥጥ ድንቅ ነገር ነው፤ የተፈጥሮ ዜማ ለእኛ ከመስማማቱ የተነሣ የሌለ እስኪመስለን ተመሥጠንበታል፤ ለዚያም ነው ሊቃውንት ቅኔን ላቅ ያለ የምስጋና ዜማ ማቅረቢያ የሚያድርጉት (ካስተዋልነው ግን የቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይነት ብቻ ብዙ ይነግረናል)፡፡

የኢትዮጵያ ቅኔ ይህንን መሠረታዊ መስተጋብር ባገናዘበ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ነዉ፡- እንደኔ አረዳድ፡፡ በጥቅሉ ካስተዋልነዉም ተፈጥሮ የተሠራችዉና የከበረችዉ በቅኔነት እንጂ በልሙጥነት ስላልኾነ (ተፈጥሮን በልሙጥነት ካልተረዳሁ ብሎ የሚታገልም መሃይም እንጂ ሊቅ ሊባል አይገባዉም፡- ባይ ነኝ፤ ያልኾነችውን እንዴት ሊረዳት ይችላል?)፤ ምሥጢሯም የተጻፈዉና የሚነበበዉ በቅኔነት ነዉ (በቅኔ ባትሠራማ ኖሮ ምሥጢር አይኖራትም ነበር፤ ዜማዋም አይመስጠንም አይደንቀንም ነበር)፡፡ ይህ ጥበብ ነው በሊቃውንቱ በቋንቋ አማካይነት ሥርዓት ይዞ የተገለጸው (ቋንቋ ራሱ የተፈጠረው በልሳን ወይም በድምፅ መኾኑን ልብ ይሏል)፡፡ ይሁንና የተመለከትነውን የተፈጥሮ ቅኔነት አሁን ከሚገኘዉ የሊቃዉንት የቅኔ ልማድ ጋር አገናዝቦና አዋህዶ ምሥጢሩን ለማፍታትና ያንንም በትክክል ለማስረዳት ብዙ የመሟገቻ ምርምሮችን ማድረግ ይጠይቃል (እንዳው እየነሸጠኝ እንጂ እዚያ ውሰጥ በመግባት አልዛቁንም፤ ዐዋቂ ይመስልም አልፈተፍትም፤ በዚህ ባቀረብኩት እንኳ ‹የልጅ ሙግት ጠዋት ወደ ሰማይ፣ ማታ መሬት መሬት ሊያይ› ብለው እንደሚፎትቱኝ ይገባኛል)፡፡ ‹ሕልም ተፈርቶ› እንቅልፍ ማጣት መኾንም የለበትም፡፡

የተፈጥሮ ቅኔነት የገባቸው ከጥንት ጀምሮም የተፈጥሮ መስተጋብርን በማስተዋል መመርመር የሰዉ ልጆች ሲተገብሩት የኖሩት እንጂ ዐዲስና ድንገቴ ጥናት አይደለም፤ ከጥንት ጀምሮም የሰዉ ልጅ የተፈጥሮን ቅኔነት ለመፍታት ቀጥታ ዓይኑን በመቸከልም ይኹን የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም አጉልቶ ሲመረምር ኖሯልና (በተለይም ደፋር አትበሉኝና እነ አፍላጦን ምርምሩን ሳያጣምሙት በፊት)፤ የቅኔ ተግባርም ልክ እንደ ሳይንስ ዕዉቀት የተፈጥሮን ምሥጢር መግለጽ ይመስለኛል፡፡ ይህም ማለት የሰዉ ልጅ ፍጥረትን ሲመረምር ለማወቅ ይጥር የነበረዉ ቅኔያዊነቷን ስለነበረ የተመራማሪነት ተፈጥሮዉም የተቆራኘዉ ከቅኔ ጋር ነበር፤ ነዉም፤ የቅኔ ጥንታዊ የምርምር መሠረትም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ግልፅ ለማድግ የተፈጥሮን ኹኔታና እንዴት የሰዉ ልጅ የጥናት ዝንባሌ የተፈጥሮን ሥሪትና ሥርዓታዊ ተመጋጋቢነት በማስተዋል ላይ ተመሥርቶ እንደመጣና በቋንቋውም ያንን ለመግለጽ እንደጣረ ማየት ይጠቅማል፡፡

ከዚህ በፊት እንደገለጽነው ተፈጥሮ በኅብርነት ከብራ በዕምቅነት የምትገኝና በለዛዊ ዜማ የሠመረች ነች፤ ስለዚህ የሊቃውንት ምርምራቸዉ ኹሉ የሚኾነው ቅኔነቷን መፍታትና ምሥጢሯን መግለጥ፤ በለዛ በመመሰጥ መደነቅና መደሰት ነበር፡፡ ስለኾነም የሰዉ ልጅ ምርምርን የጀመረዉ የተፈጥሮን ቅኔነት በማወቅና ምሥጢሯን በመፍታት ነዉ ማለታችን አግባባዊነት ያለዉ ገለጻ ነዉ፡፡ ይህም ቅኔ የሰዉ ልጅ ጥንታዊና ተፈጥሯዊ የዕዉቀት መክፈቻና መዝገብ መኾኑን ያስገነዝበናል፤ ይህ ስለኾነም ይመስላል አበዉ ‹ቅኔን ይቀኙታል እንጂ መዝግበዉ አያጠኑትም› የሚል አቋም የነበራቸዉ፡- ተፈጥሮን አስተዉለዉ ይረዱታል እንጂ በመዝገብ ገልብጠዉ አይዙትም ወይም አያስቀምጡትም ማለታቸዉ መሰለኝ፡- የሚመዘገበዉ የዚያ (የተፈጥሮ) ነጸብራቅ ነዉና፡፡ ‹አእምሮ እስካለ ድረስ ቅኔ አይጠፋም› የሚሉትም ከዚህ የተፈጥሮ መስተጋብር ግንዛቤ መራቅ ስለማይቻል ነዉ፤ ‹ቅኔነትን የታደለ፣ በቅኔነት የተሠራ አእምሮን ይዞ እንዴት ቅኔን ማወቅ ያቅተዋል?› የሚል ዕሳቤ ያላቸዉ ይመስላል፡- ሊቃውንቱ፡፡ ስለዚህ የሰዉ ልጅ በኖረበት ጊዜ፣ ሥፍራና ኹኔታ ኹሉ ተፈጥሮ በመኖሩ የተፈጥሮን ምሥጢር መጥኖ የሚያሳዉቀዉ ቅኔም ከአእምሮዉ ሊጠፋ አይችልም፡፡

ይህንን ግንዛቤ መሠረት የሚያደርገዉ የግዕዝ ቅኔ ፍልስፍናም ከጥንታዊ መሠረቱ ጋር የተገናዘበ ስለኾነ የጥንት የፍልስፍና አስተምህሮን አካቶ የሚገኝ የምርምር ማዕከል ነዉ፡፡ ስለኾነም ቅኔያዊ ፍልስፍናዉ ከሰምና ወርቅ የግጥም ጨዋታ ያልፋል፡፡

የሰዉ ልጅ የተፈጥሮን ምንነት በቋንቋነት አጉልቶና በፊደላት ቀርጾ ለማወቅ ሲጥርም የተፈጥሮን ቅኔያዊ ተፈጥሮ መተዉ ስላልኾነለትም የቋንቋ ቅኔን ፈለሰፈ፤ ይህም በኅብራዊ ቋንቋ ስዉሩን እየገለጹ፣ ዉስብስቡን እየፈቱ መግለጽ ነዉ፤ ኅብራዊ ተፈጥሮውም ነገሮችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳያይ ከምሥጢራዊነትና ከገሐዳዊነት ጋር አገናዝቦ በመፍታት የቃላትን ኃይልና አግባባዊ አጠቃቀም እያበጠረ የሚያስረዳና ምንነታቸዉን እስከ አጠቃቀማቸዉ የሚያሳዉቅ አደረገው፡፡ ይህ ደግሞ የፍጥረታትን ምደባዊ ክፍፍል መሠረት አድርጎ ከተሠራዉ የግዕዝ ቋንቋ (ሰዋሰዉ) ጋር አግባባዊ ስምምነት አለዉ፡፡ የቋንቋ ሰዋሰዋዊ ሥርዓት ከተፈጥሮ መስተጋብር ጋር ተናቦና ቀጥታ ተገልብጦ የተሠራ ስለኾነም የተፈጥሮን ቅኔ በቋንቋው ለማመሥጠር አቅም አግኝቷል፡- በተለይም የግዕዝ ቅኔ፡፡

ይህን ተፈጥሯዊ የቋንቋ ሥርዓት መሠረት ያደረገ የቅኔ ጥበብም ልክ የተፈጥሮን ምሥጢር ዉድ ማዕድናት (ዕንቁ፣ ወርቅ፣ ነዳጅ…) ፈልጎና በጥልቀት ቆፍሮ እንደማዉጣት ጥልቅና ዉስብስብ የጥበብ እሳቤዎችን ለይቶ ለማወቅም ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ማለትም ልክ ነዳጅና ወርቅ ከመቀመቅ ቆፍሮ እንደማዉጣት የጥበብ ምሥጢርም በስንት ምርምርና ቁፋሮ ነዉ ከጥልቅ ሐሳብ ዉስጥ ተሸልቅቆና ተጣርቶ የሚወጣዉ፤ የቅኔ ሊቅም የጥበብ ቅኔን ምሥጢር የሚያገኛት ከተቀበረችበት አዘቅት/ጥልቀት ስንትና ስንት ‹ሰም የኾኑ› ሐሳቦችን ቆፍሮና ለፍቶ ነዉ፡፡ ስለኾነም የቅኔ ሊቅ በገሐዳዊነት የተገለጸዉን በማየት ብቻ በቀጥታ ዕይታ ተሸብቦ (አፍጦ) አይቀመጥም፣ ሲፍታታና ሲገላለጥ በዉስጡ ምን ይኖረዋል፤ ምን ምሥጢርን ዐምቆ ይዞ ይኾን (አልማዝ ነዉ ወርቅ ወይስ ነዳጅ ከመቀመቁ ጉድጓድ ዉስጥ ተቆፍሮ የሚወጣዉ)፣ ትንቢት የነበረዉ ከአሁኑ ጋር፣ የአሁኑ ኹኔታም ወደፊት ከሚመጣዉ ጋር በእንዴት ዓይነት ግንኙነት ይገለጻል፣ በምሳሌ የሚገለጸዉ ነገር ምን ያህል ከእዉን ነገር ጋር የተናበበ ነዉ፤ የሥጋዊና የመንፈሳዊ ትርጓሚያት ግንኙነት ምን ይመስላል፤… የመሳሰሉትን ነጥቦች በማገናዘም አንድ ሐሳብ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲታይ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ቅኔ ስዉር መግለጫ፣ ዉስብስብ መፍቻ፣ ጥልቅ ሐሳብን ማዉጫ፣ የጥልቅ ሐሳቦች ማማረጫ፣ የተሻለዉን ሐሳብ ማረጋገጫ፣… ነዉ፡፡ ለዚህም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የመጻሕፍት ትርጓሜ ስልቶችን፣ የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክሮች፣ የፈለጢና ምሳሌያዊ ንግግሮች እና  ሌሎች የቅኔ ትሩፋት የኾኑ ጥበባትን ልብ ይሏል፡፡

ከቅኔ ዕዉቀት ጥልቀት የተነሣ ጠቢባኑ የፍጥረታት የወላዊነትና የብትናዊነት ተፈጥሮና መስተጋብርን የወከለዉ የሰዋሰዉ ጥበብ (የአግባብ፣ የግሥ ሥርዓት እና የእርባ ቅምር ጥበብ) ባለቤቶች ስለኾኑ ንግግሮችን በተለያየ አንግል የመረዳት፣ የሐሳቦቹን ፍሰት የማወቅ አቅም ይኖራቸዋል፡- የማስተዋያ አንግልንና ሐሳብን የማቀናበር አቅምን ያዳብራልና፡፡ ስለኾነም የቅኔ ጠቢባን ሌላዉ ሰዉ የሚናገረዉን ቃል ወይም ሐሳብ ገና ካጀማመሩ ከተለያየ አተያይ ይረዱታል፡፡ ለዚያ ነው ሊቅነታቸውን ለማስመስከር በቅኔ ነጠቃና ዘረፋ የሚወዳደሩት፡፡ ለምሳሌም አንድ ጊዜ አለቃ ከሣ ጉዱና አለቃ ዶሪ እኔ እበልጥ! እኔ እበልጥ! በማለት በቅኔ መዛራፍ ሲወዳደሩ በመጨረሻም አለቃ ዶሪ ‹ማዕበል ቅኔከ ለእመ ገፍዓኒ፣ ወተንተንኩ ለወዲቅ እግዚአብሔር አንሥአኒ› (ማዕበል የኾነ ቅኔህ ገፍትሮ ሊጥለኝ ሲል እግዚአብሔር ታደገኝ) ሲለው አለቃ ካሣም በተራው ‹ዶሪ ዶሪ፣ የቅኔ ፈጣሪ›[18] ብሎ ችሎታውን መስክሮለታል ይባላል፡፡ በመዘራረፍ ውድድር ብቻ ሳይኾን አንድ ነገርንም በፍጥነት ገልብጠው በማየት በቀላሉ ችግሩን ወይም ምሥጢሩን የሚረደት፣ ምሥጢሩ የረቀቀባቸውን ለመፍታት በተመስጦ መንኮራኩር ተሳፍረው ሰማየ-ሰማያት፣ አጽናፈ-አጽናፋትን፣ ዕምቀ-እመቃትን፣ የሚበሩት ልዩ ችሎታን ገንዘብ ስሚያደርጉ ነው፡፡

ለቅኔ ግልበጣ[19] (ከጀርባው ገልብጦ ማየት መቻል) ማሳያ የሚኾን ከእንስቷ ባለቅኔ ከእማሆይ ገላነሽን ታሪክ እንጥቀስ፡፡ አንድ ጊዜ የቅኔ ተማሪዎች ትግራይ ዉስጥ ከሚገኝ ሳምሮን ከተባለ ሥፍራ ተነሥተዉ እሳቸዉጋ ቅኔ ለመማር ይመጣሉ፡፡ እማሆይም ተማሪዎቹን ከየት እንደመጡ ሲጠይቋቸዉ አንዱ ተማሪ ትንሽ የቆጠራትን የግዕዝ ቅኔ ለማስተዋወቅ ብሎ ‹መጻእነ እም ሳምሮን› ይላቸዋል፤ እሳቸዉም ‹እኛም አለን ተኳኩለን› አሉት ይባላል፤ እዚህ ላይ ተማሪዉ ለማለት የፈለገዉ ‹ሣምሮን ከሚባል ሥፍራ መጣን› ነበር፤ የቅኔዋ ሊቅ ግን እሱ ባልጠረጠረበት መንገድ ገልብጠዉ የብልግና ቃል ‹እምስ አምሮን መጣን› ያለ አስመስለዉ ተረጎሙበት፡፡ ስለኾነም ቅኔ ቃላት ወይም ሐሳቦችን ባልተጠበቁና በተለያየ አንግል ለመረዳት ያስችላል፡፡ ይህንንም ማርዬ ‹ለዚያ ነዉ ባለቅኔ ሌላ ሰዉ ሊናገረዉ የፈለገዉን ገና ከንግግሩ አጀማመር መረዳት የሚችለዉ፡፡ አንድ ሰዉ ከእነርሱ ጋር በሚያደርገዉ ዉይይት እንኳ ገና ትንሽ እንደተናገረ ስለሰዉየዉ ኹኔታ (የዕዉቀት ደረጃ፣ ፍላጎት፣ ሐሳብ) አጠቃላይ ግንዛቤ ለመያዝ ብዙ ጊዜ አይወስዱም፡፡›[20] በማለት አስቀምጦታል፡፡ ለዚያም ሳይኾን አይቀርም ሊቃዉንቱ ቅኔን የአንድምታ ትርጓሜ ዕዉቀት መሠረት የሚያደርጉት፡- ኅብራዊ ቃላቱን በተለያየ አገላለፅ እንዲረዱት ይረዳቸዋልና፡፡  መገቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤልም ‹የቅኔ ትምህርት ከፍተኛ ትምህርት በመኾኑ የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ራሳቸው የአንድምታን ትርጓሜ በሚተረጉሙበት ወይም መጻሕፍትን በሚያኼዱበት ጊዜ በአስረጅነት ይጠቅሱታል፡፡›[21] በማለት ገልጸውታል፡

ቅኔ የሊቃዉንቱ መሠረተ-ዕዉቀት፣ መመርመሪያ ስልትና የዕዉቀታቸዉ ደረጃ ማስመስከሪያ ጥበብ ስለኾነም የፍልስፍናቸዉ መሠረት ነዉ፡፡ ለዚያም ነዉ ቅኔን ‹የምሥጢራት መክፈቻና መቆጣጠሪያ ብርሃን፣ የዕዉቀቶች ሊቀመንበር፣…› በማለት የሚጠሩት፡፡ ለዚያም ነዉ ሊቃዉንቱ ‹ያለ ቴሌስኮፕ ከዋክብትን፣ ያለ ማይክሮስኮፕ ጥቃቅን ነገሮችን በማየት ማጥናት እንደማይቻለዉ ያለ ግዕዝ ቅኔ ዕዉቀትም የመጻሕፍት ምሥጢራትን በአግባቡ አስማምቶ በመረዳት መተርጎም አይቻልም፤ በጨለማ ያለ ባትሪ መጓዝ ነዉ› የሚሉት፡፡ ስለኾነም ነዉ አብዛኞቹ የመጻሕፍት ሊቃዉንት ለማስተማር የግዕዝ ቅኔ መማርን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚመለከቱት፡፡ አሁንም መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤልን እንጥራና ያሉትን እንስማ፤ እንድህ ይላሉ ‹ቅኔ በሀገራችን በኢትዮጵያ ወይም በቤተ ክርስቲያናችን ራሱን የቻለ ትምህርት ቤት ያለዉ ከፍተኛ የትምህርት ዓይነት ነዉ፡፡ የቅኔ ትምህርት ደቀመዛሙርትን ተመራማሪዎች፣ ደራሲዎችና የምሥጢር ሰዎች ወይም ፈላስፎች የሚያደርግ ከሣቴ ብረሃን በመሆኑ በቤተክርስቲያን ከፍተኛ ክብርና ቦታ የተሠጠዉ ነዉ፡፡›[22]

እዚህ ላይ ‹ለምን ሊቃዉንቱ መጻሕፍትን ለመመርመር ቅኔ ማወቅን በቅድመ-ኹኔታነት ወሰዱት?› ብሎ መጠየቅ አግባብ ይኾናል፡፡ ‹ቅኔ እንደ ሌሎች ሀገሮች ግጥም ከኾነ ለመጻሕፍት መመርመሪያነት በምን መልኩ ሊረዳቸዉ ይችላል?›

ይህ ጥያቄም ‹ቅኔ መቼ ግጥም ብቻ ኾነና ምንነቱ ከግጥሙ በሻገር ነዉ› የሚል መልስን ይጠራልናል (ከግጥሙ ባሻገር ያለዉን የቅኔ ምንነት ማስተዋልና መረዳት ካልቻልን ግን የቅኔ ምንነት ከግጥም ጋር ተደባልቆብናል ማለት ነዉ)፡፡ ለዚያ ሳይኾን አይቀርም ቅኔን እንዳንድ ዋና የትምህርት ዘርፍ እና ሌሎች እንደ የመጻሕፍት ትርጓሜያት ዓይነት ትምህርቶችን ለመማርም እንደ ቅድመ-መሥፈርት የሚወሰደዉ፡፡ የመጽሐፍ ትርጓሜ ትምህርት የሚቀናቸዉ ቀድመዉ የቅኔ ዕዉቀትን የተረዱት ሊቃዉንት ናቸዉ፤ ቀድመዉ ዕዉቀታቸዉን በቅኔ ያዳበሩ አብዛኞቹ ሊቃዉንትም የመጻሕፍት ምሥጢራትን ሰርስረዉ ለመረዳትና ለማሳየት የዕይታቸዉን አድማስና የአስተዉሎታቸዉን ምጥቀትና ጥልቀት በቅኔ ዕዉቀታቸዉ መቆጣጠር ስለሚችሉ የአንድምታ ትርጓሜዉን ለማስማማት ያስችላቸዋል፡፡

ቅኔ ለመጻሕፍት አንድምታ ትምህርት የሚሠጠዉ ጥቅም በዋናነት ተመራማሪዉ ትርጓሜዎቹን በተለያየ አንግል የማየትና የመተርጎም ችሎታን እና የማነጻጸር ጥበብን (አቅምን) ገንዘብ እንዲያደርግ ማስቻል ነዉ፡፡ ይህም ጥበብ ለሚተረጎመዉ ሐሳብ የተለያዩ የዕይታና የትርጉም ምርጫዎችን በማቅረብ፣ እነሱንም በማፍረስና በማወዳደር የተሻለዉን ወይም ትክክለኛዉን ትርጓሜ እንዲረዳዉ ያደርጋል፤ ታሪኩንም እንዲመረምር በምሥጢር ይዞት ይሔዳል፡፡ በዚህ መልክ ከተለያየ አንግል በማነጻጸርና በማማረጥ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ዕዉቀትም በቀላሉ አይናድም፤ እንዳዉም ምሥጢሩ በዉስጥ እየተብላላ የበለጠዉና አይረሴው ምሥጢር ተፍታትቶ ይገለጻል፡፡ መጋቤ ምሥጢር እንዲህ ይላሉ፡-

‹ቅኔን ከእነ አግባቡ በጥልቀትና በስፋት የተማረ ሰዉ ትርጓሜ መጻሕፍት አያግደዉም፤ ወደ መጻሕፍ መምህራን ዘንድ ሳይሄድ መጻሕፍትን ራሱ ሊተረጉማቸዉና ሊያመሠጥራቸዉ ይችላል፤ ወደ ትርጓሜ መጻሕፍት ቤት ቢገባም ጊዜ አይፈጅበትም፤ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ትርጓሜ መጻሕፍትን አጠናቅቆ ሊወጣ ይችላል፡፡›[23]

ይህም የሥነ-አመክንዮ ዕዉቀት የፍልስፍና መመርመሪያ እንደኾነዉ የቅኔ ዕዉቀትም የጥበብ መመርመሪያ ስልት መኾኑን ይጠቁመናል፡፡ ነገር ግን ቅኔ እና ሥነ-አመክንዮ በስልትነታቸውና በቋንቋ መጠንቀቅ ቢመሳሰሉም በተፈጥሯቸው ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ ‹ሥነ-አመክንዮ ዐጥንቶቹ የቆሙት በተጠየቃዊነት ክርክር ሲኾን ክርክሩም በአግባባዊ የቋንቋ ሥሪት የተገነባ ነዉ፡፡ ከግዕዝ ቅኔ ጋር ቋንቋን በጥንቃቄ በመጠቀማቸው ቢመሳሰሉም በኅበርነት (ቅኔ) እና በልሙጥነት (ሥነ-አመክንዮ) ተፈጥሯቸው ተቃዋማሚ ናቸው፡፡ ባይኾን የኢትዮጵያውያን ጥበብ የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር ከሥነ-አመክንዮ ጋር ይመሳሰላል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የተጠየቅ ጥበብ ደግሞ በተዘዋዋሪነት ቢኾንም የሚፈልቀው ከቅኔ ጥበብ ነው፤ በቅኔ ዉስጥ ተጠየቃዊ ጥበብ (ምክንያታዊነት) የሚገኘዉ በስዉር ስለኾነ የሚገለጸዉም በተጠየቅ-ልጠየቅ ክርክርና ዉይይት ወቅት[24] ወይም ሐሳቦችን ጨምቆና በትኖ በማስቀመጥ ኹኔታ ነዉ፡፡ ስለኾነም በቅኔ ዉስጥ የተጠየቅ ጥበብ ቢኖርም ከሥነ-አመክንዮ አመክንዮ ሕግጋትና መርሆዎች ጋር አይስማማም፤ ምክንያቱም ኅብራዊነት ለቅኔ መሠረቱ ሲኾን ለሥነ-አመክንዮ ግን እንደጠላቱ ስለሚቆጥረው መርሁ ኅብራዊነትን ማስወገድ ነው፡፡  ስለኾነም የሥነ-አመክንዮ ዕውቀት ተፈጥሮን በልሙጥነት ቅኝት ነው የሚረዳዉ፡- ልሙጥነት ደግሞ የፍጥረትን ቅኔነት አሟልቶ መግለጽ አይችልም፡- አንድ ዓይና ነው (አንድ ብርቁ!)፤ ወርቅ ሐሳብን ዐያይም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ቅኔ ግን ከተፈጥሮ ኅብርነት ጋር የተገናዘበ ስለኾነ ለጥልቅና ለምጡቅ ጥበባት መጠበቢያ መኾን ይችላል (ቢያንስ ኹለት ዓይና፣ ከዚያም ካለፈ አራት ዓይና ይኾናልና)፡፡ ለዚያም ሳይኾን አይቀርም የኢትዮጵያ ሊቃዉንት ከሥነ-አመክንዮ ዕውቀት ጋር ተመሳሳይ የኾነውን ‹የተጠየቅ-ልጠየቅ› የክርክር ጥበብ እንደ ቅኔ የተለየና ዋና ትምህርት በመማርና በማስተማር የአንድምታ ትርጓሜና የሌሎች መንፈሳዊ ጥበባት መመርመሪያ መሣሪያ (ስልት) በማድረግ ያልተጠቀሙበት[25]፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ማርዬ ‹ቅኔ ኹሉ ግጥም ይኾናል፤ ግጥም ኹሉ ግን ቅኔ አይኾንም› ይላል፤ ነገር ግን የመደበኛውን የግዕዝ ቅኔ ብቻ ማለቱ ካልኾነ በስተቀር ቅኔ በግጥም ብቻ አይገለጽም፤ በዝርዉነትም ሰምሮና ተዉቦ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ዓለማየሁ ሞገስ ይህንን ሲገልጹ፡

‹ቅኔም የሚባለው በንግግር ስልት ነው እንጂ፤ ቤት በመታሽ ግጥም በገጠምሽ አይደለም፡፡ በቅኔ ዜማ ተሳክቶ ስልቱን ያልያዘ ግጥም እንጂ ቅኔ እንደማይባል ተራ ንግግርም ኅብርና ምርምር፣ አንጻርና ሰም ለበስን የመሰለ ይዞ ሲገኝ ቅኔ ነው› ይላሉ[26]፡፡

ምሳሌ ቢያስፈልግ ‹ወዳጄ ልቤ› የሚለዉን የብላቴን ጌታ ኅሩይ መጽሐፍን፣ በዘሪሁን አስፋዉ ተሰብስቦ ‹ልብወለድ አዋጅ› በሚል በታተመዉ መጽሐፍ ላይ የሚገኙ ጽሑፎችን፣ የአለቃ ዘነብን ‹መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ እና ሌሎች መጽሐፎችን ማየት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሊቃዉንትም ንግግራቸዉ ኹሉ ከቅኔ ጋር ከመቆራኘቱ የተነሣ ጨዋታቸዉ ኹሉ የታመቀ፣ ምሥጢር ያቀፈ፣ በለዛዊ ተዉህቦ የተኳሸና አይረሴ ነዉ፡፡ ለዚህም እንደ እነ አለቃ ገ/ሐና ዓይነቶቹ ጥሩ ምስክር ይኾናሉ፡፡ እንደ እነ አለቃ ተክሌ፣ አለቃ የማነ ብርሃን፣ መሪጌታ ክፍለ ዮሐንስ፣ መሪጌታ ውቤ ገረጨጭ እና እማሆይ ገላነሽ ዓይነት ሊቃዉንትም ምሳሌዉን በማጎልበት ተጠራርተዉ ይመጣሉ፤ የቀልድ፣ የጨዋታቸው ፍልስፍና ቅኔ ነዉና፡፡

እዚህም ላይ አንድ ተጨማሪ ነጥብ እናንሣ፤ ምናልባት ለቅኔ ልዩ ክብደት በመስጠታችን የተነሣ በአእምሯችን ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፤ ‹ቅኔ ፍልስፍና ነዉ ወይስ ፍልስፍና ራሱ በቅኔ ዉስጥ የሚገኝ ፅንሠ-ሐሳብ ነዉ እያልን ነዉ?› የሚል ጥያቄ በአእምሯችን ብቅ ጥልቅ ይልኾናል፤ የዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቅኔ በፍልስፍና ዉስጥ የሚገኝ ከኾነ ‹የቅኔ ፍልስፍና› በሚል ቅርንጫፍ እያወራን ነው ያለነው ማለት ይኾናል፤ በተቃራኒዉ ግን ‹ፍልስፍና የቅኔ አካል› ከኾነ ግን ቅኔ ከፍልስፍናም በላይ የኾነ ዕዉቀት ሊኾን ነዉ፡፡ የኹለተኛዉ ሐሳብ አሁን ያለዉን ገዥ የዓለም ነባራዊ ዕዉቀት ኹሉ የሚገለብጥ ነዉ (ጉረኛ! ምኑ ተይዞ አላችሁ፤ በሉኛ!)፤ ምክንያቱም በዘመናችን የሚገኙት የዕዉቀት ክፍሎች ኹሉ የፍልስፍና ዝርዝር ብልቶች (ምንነቶች) እና ከእሱም እየተቀዱ የተስፋፉና በሳይንስ አማካይነት ወደ ተግባራዊነት የሚቀየሩ ዕዉቀቶች እንጂ ሌላ ነገር የለባቸዉም[27]፡፡ ይህ ምንነታቸዉ ከቅኔ ጋር ከተጋባና ቅኔ የፍልስፍና ሊቀመንበር ኾኖ በእሱ ይትባህል ከመራቸዉ ያለዉ ምንነታቸዉ ተንዶና ተቀይሮ ዐዲስ ይትባህልን ለመላበስ ይገደዳሉ (በአንድ ዐይን ከማጮለቅ ያለፈ ስልት ያዳብራሉ)፡፡ ስለዚህ የተነሣዉ ጥያቄ ጥልቅ አስተዉሎትንና የዕዉቀቶችን የመስተጋብር ሁኔታ መረዳትን ይፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ባይኾን አንባቢ ከግሉ የዕውቀት ተዘክሯዊ ክምችት እና እስካሁን ከተመለከትናቸው ዕይታዎች ተነሥቶ  የራሱን ፍርድ እንዲሠጥ መተው ሳይሻል አይቀርም (ልብ ያለው ጎበዝ እስቲ ይችን ነጥብ ያብስልና መላ ይፈልግላት፤ ‹ክፍተቱን አስተውሎ ይሙላ› ማለቴ ነው)፡፡ በተጨማሪም የቅኔና ፍልስፍና የግንኙኑት መስተጋብር እና ‹የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ› ፍልሚያ ለመረዳትም በምዕራባዊያን ቅኔ ከፍልስፍና የተለየበትን ታሪካዊ ምክንያት ማየት ትዝብታችንን ያዳብርልና ምክንያቱንም ይገልጽልናል፤ እንቃኘው፡፡

 

[1] ቅኔያዊ የዕውቀት ፈጠራ፣ ገጽ 79

[2] የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልደት ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም. ገጽ 139

[3] አንጋረ ፈላስፋ፣ ገጽ 8

[4] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 10

[5] እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 11

[6] አንጋረ ፈላስፋ፣ ገጽ 48

[7] እዚህ ላይ የሰምና የወርቅ ግንኙነትን ማወቅ፣ ሰምና ወርቅ ለቅኔ ትርጉም ለምን እንደዋና መሠረት እንደሚወሰድ ለመረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰምና ወርቅ የሚለው ምሳሌ የተወሰደው ከወርቅ ሠሪ ነው፤ ወርቅ የሚሠራ ጠቢብ የሚፈልገውን የወርቅ ቅርጽ  የሚቀርጸው መጀመሪያ በሰም ላይ ነው፤ ቀርጹንም በሰም ላይ አስተካክሎ ከሠራ በኋላ ወርቁን አቅልጦ በዚያ በተሠረው የሰም ቅርጽ ላይ ያፈሰዋል፤ ያ የቀለጠ ወርቅም ሲበርድ የፈሰሰበትን የሰም ቅርጽ በትክክል ይዞ ይቀራል፤ ከዚያም ሰሙን በማስወገድ ወርቁ የተፈለገውን የጌጥ አገልግሎት ይሠጣል፡፡ በዚህ መልክ ሐሳብም ፊት ለፊት የምንመለከተው ብቻ ሳይኾን በዚያ ውስጥ ተሸፍኖ የተሠራ ወርቅ የኾነ ሐሳብም አለው፤ ይህንን ሠርቶ የሚያሳየው ደግሞ ጠቢብ የኾነ የወርቅ ሠሪ ባለሙያ ነው፤ ሌላው በወርቅ ማጌጡን እንጂ ወርቅ እንዴት እንደሚሠራ ላያውቅ ይችላል፡፡ ስለኾነም ነው ሰምና ወርቅ ለቅኔ ዋና ትርጉም የሚኾነው፤ ምክንያቱም ምንም ዓይነት መንገድ ይከተል ኅብርነት ያለው ትርጉምን ይይዛልና፡፡

(ይቆየን! ያቆየን!)

[8] የግእዝ ቅኔያት የሥነ-ጥበብ ቅርስ ንባቡ ከእነትርጓሜው፣ 1980፣ ገጽ-24

[9] ኢትዮጵያዊውያን ፍሎሶፊዎች፣ ሐተታ ዘርአ ያቆብ፣ ገጽ 24

[10] ዝኒ ከማሁ፣ ሐተታ ወልደሕይወት፣ ገጽ 48

[11] የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 12

[12] ዓለማየሁ ሞገስ፣ መልክዐ-ኢትዮጵያ፣ ገጽ (1)

[13] መጽሐፈ ቅኔ፣ ገጽ 34፤ የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ፣ ገጽ 31

[14] መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ፣ ገጽ 19

[15] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 22

[16] መጽሐፈ ቅኔ፣ ገጽ 30

[17] እጓለ ገጽ 60

[18] ጥንታዊት የኢትዮጵያ ትምህርት፣ ገጽ 280

[19]  ቅኔ ግልበጣ የመምህሩን ቅኔ ወሰዶ በሌላ ቅኔ በመቀየር ገልብጦ ማቅረብ ነው፤ እኔ እዚህ የጠቀስኩት ግን ቅኔን በተለየና ባልተጠበቀ አተያይ አዙሮ ማየትን ነው፡፡

[20] ቅኔያዊ የዕውቀት ፈጠራ፣ ገጽ 63

[21] የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልደት ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም. ገጽ 141

[22] የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልደት ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም.፣ ገጽ 135

[23] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 139

[24] የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር ማጣረስን መጠበቂያና እውነትን ማንጠሪያ ‹የማር ማገጃ› ሥዓት ስላለው ትኩረቱ የክርክር ፍሰትን መጠበቅ ላይ ስለኾነ ከሥነ-አመክንዮ ክርክር የመንደርደሪያና መደምደሚያ  መስተጋብር ጋር ይመሳሰላል፡፡

[25] የተጠየቅ-ልጠየቅ እሰጥ አገባ ክርክር በበአብዛኛው ከሥነ-አመክንዮ ጋር መሳሰላሉን ልብ ይሏል፤ እሱን ግን በሙግት ጊዜ ካልኾነ በስተቀር ትኩረት አድርገው ወይም እንደ ዋና ጠቃሚ ዕውቀት አድርገው አያጠኑትም፡፡ በሌላ በኩል በሀገራችን የሕግ ትምህርት ቢኖርም ፍትሐ-ነገሥትን የመሰሉ መጽሐፎችን በማጥናት ላይ ይመሠረታል እንጂ ከተጠየቅ ልጠየቅ የክርክር ጥበብ ጋር የተገናኘ አልነበረም፡፡

[26] መልክዐ ኢትዮጵያ፣ ገጽ 9

[27] ምንም እንኳን በዚህ ዘመን የሳይንስ ጩኸት ከፍልስፍና በላይ ጎልቶ ቢሰማም፤ የሳይንስ ትምህርቶችን ጩኸት የጨመረዉ ከተግባራዊነትና ከጥቅመኝነት ጋር ስለተቆራኘ እና የቴክኖሎጂ ምርቶችን ስላስገኘ ነዉ፤ እንጂ ሳይንስ ፍልስፍና ላይ ሳይመሠረት ቀርቶ አይደለም፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply