ፍልስፍና= ፍቅረ-ጥበብ= የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ቅኔ

-በካሣሁን ዓለሙ-
ታላቁ ሊቅ ሶቅራጥስ በአንክሮ መጠበብ (ፍልስፍና) እንደምትጀመር ተናግሯል አሉ፡፡ ግን ምን ስለሆነች ነው ጥበብ የምታስደምመን? ምን ስለሆነች ነው በፍቅር የምታሳብደው? ‹በቅድሚያ ማወቅ መተዋወቅ› ብሏል ዘፋኙ! ስለዚህ እንተዋወቃት፤ እኛም ብንሆን ታዲያ ‹ተይ! ማነሽ! ተይ! ማነሽ!› ብለን ልንጠይቃት፣ ልናውቃት ይገባል!፡፡
‹ወይ ጥብብ! ወይ ጥበብ!… አንቺን ያፈቀረ፣
ተብረክርኮ ቀረ!› አለ አድናቂዋ!
እንደኔ ግንዛቤ ጥበብን እንደተሸበበች በቅሎ በአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከት ሙሉ አይመስለኝም፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን የአንድምታ ትርጓሜ በተለያየ አቅጣጫና ደረጃ ገጽታዋ ሊታይና ሊነገር ይገባዋል፡- በቻል አራት ዓይና መኾንን ትፈልጋለች፡፡ ለእኔ በጥቅል የተረዳሁት የመሰለኝ የጥበብ ምንነት ልግለጽ፤ ለእኔ ጥበብ በተዋህዶ የምትሠልስ ናት፤ ማለት የጥበብ ትርጉም ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ (ቅኔ)› ነው፤ አንድም በኢትዮጵያውኛ እንግለጻት ካልን ‹ጥበብ ማለት ቅኔ ናት› (ግጥም አላልኩም)፤ ካሠራር ብልሃት አንጻር ካየናትም ‹ጥበብ ማለት ፊደል ናት›፤ አንድም በመንፈሳዊ ዕይታ ከተመለከትናት ጥበብ እግዚአብሔርን (ሥላሴ) ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥርነት ፈክራ ታመሠጥራለች›፡፡ እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ከሆነ ‹ጥበብ ሰባት አዕማዳት ያሏት ቤት› ነች፡፡ ስለዚህ ጥበብን በተለያየ ዕይታና አተረጓገም መቃኘት ይገባል፤ ግን መሠረታዊ ትርጓሜዋን መልቀቅ የለባትም፤ ያንኑ ማምጠቅ ወይም መወሰን ወይም የትኩረት አቅጣጫዋ መወሰን ወይም የአስተውሎት ልዩነት ነው ልዩነቱን የሚፈጥረው፤ አንድም የትርጓሜው ልዩነት የሚፈጠረው ከምትታይበት የአንግል መለያየት የተነሣ ይሆናል፤ ለማንኛው እነዚህን አንድማታዊ ትርጓሜዎች እንቃኛቸው፡- ቅኔነቷን እየፈታን፤ የላይ ቤትና የታች ቤት ምሥጢራዊ ትርጓሜዋን እየለየን እንያት፡፡
በመሠረትነት ጥበብ የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ ሥሪት ናት፡፡ ጥበብን ልዩ ተወዳጅ ያደረጋትም እነዚህን ነገሮች አወህዳ የያዘች መሆኗ ነው፡፡ ከእነሱም እውነት መሠረት፣ ዕውቀት ግድግዳና ጣሪያ፣ መልካምነት ደግሞ ልስንና ክዳን በመሆን የተዋበችውን የጥበብ ቤት ሠርተዋታል፡፡ ይህች ቤት ናት እንግዲህ ስንቶችን በፍቅር እያከነፈች ስባ ካስገባች በኋላ ነፍሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጧት የምታደርገው፤ ከመሠረት አሠራሯና ንድፏ እስከ አመራረግ፣ አለሣሰን፣ አከዳደንና አቀባብ ውበቷ እየተደነቁ በፍቅር ከንፈው የቀሩላት፣ መኖሪያ እሥር ቤታቸው ያደረጓት ለዚያ ነው፡- እንዴት ብለው ይልቀቋት ትንሽ የምትመስል የዓለምን ምንነት ማወቂያና መገምገሚያ መነጽር ያላት አስደናቂ ቤት ሆና!፡፡ ከእነዚህ ከሦስት አስፈላጊ ነገሮች አንዷ ከተለየች ሦስቱም አይነሩም፤ አንዱ ያለ ሌላው ህልውና የላቸውም ምክንያቱም ጥበብን ወይም የጥበብ ቤትን ማስገኘት የቻሉት በመያያዝ ስለሆነ አይነጣጠሉም፡፡ ይህም ማለት እውነት ያለ ዕውቀት መታወቅ አትችልም፤ እውነትነት የሌለው ዕውቀትም ትርጉም የለውም፤ ያለ ዕውቀትና ያለ እውነት መልካምነት አይገለፅም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሦስት የጥበብ መሠሪያዎች በአንድነትና በሡልስነት ተዋህደው ጥበብን ያከበሩ ናቸው፡፡
ጥበብ ደግሞ የምትሠራው በብልሃት ነው፤ የብልሆችም መዋያና ማደሪያም ትሆናለች፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሯዊ ባህርዩ ብልሃትን የታደለ ፍጡር ስለሆነ ኹሉም ሰው ጠቢብ (ፈላስፋ) ነው ይባላል፡፡ አነጋገሩ እውነታነት አለው፤ አበውም ‹አእምሮ እስካለ ድረስ ቅኔ ሊጠፋ አይችልም› የሚሉት ለዚያ ነው፤ ግን ጥንቃቄንም ይጠይቃል ምክንያቱም ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ ክብሩ፡- ከአንዱ ኮከብ ክብር የአንዱ ኮከብ ክብር ይበልጣል› እንዳለው ቅ.ጳውሎስ፤ አንድ ጣት ከሌላው ጣት ሲነጻጸር እንደሚበላለጠው፤ የጠቢባኑም ደረጃና ብልሃት ተነጻጽሮ የተሻለው ጥበብ የበለጠ ሳቢነትንና ተደናቂነት ያገኛል፡፡ እንዲሁም የጥበብ ቤት የምትሠራው በዘመን ሂደት በጠቢባኑ ቅብብሎሽና ትብብር፣ ወይም መናበብ ነው፡- የጥበብ ቤት የስንት አብሰልስሎት ሥራ ናት፤ ስንትና ስንት የአእምሮ ማገዶ ፈጅታለች፡፡ ስለዚህ በሚገኙበት የዘመን ማዕዘንና ዕይታ ድንጋዩን፣ ዕንጨቱን፣ ሣሩን፣ ማገሩን፣ ጭቃውን፣ ቀለሙንና የመሳሰሉት በማቀበልና በማስተካከል ባደረጉት አስተዋፅኦ፣ መተራረምና ማስተካከል ነው ጥበብ በቤትነት የተሠራችው፡- በተላይ ደግሞ በተመረጡ ባለሙያዎች፡፡ ስለዚህ አሁን የምትገኘው ጥበብ ጠቢባን ለብዙ ዘመናት ለእውነት፣ ዕውቀትና መልካምነት ግንባታ የአእምሮ ጉልበታቸውን የጨረሱባት ናት፡፡ በሌላ አባባል የጠቢባነ-ጠቢባኑ እየተከራከሩ፣ እየተመካከሩና እየተራረሙ የእውነት ዓለትን አጥብቀው (አንጠርው) በመመሥረት፣ በዕውቀት መሣሪያነት አስልተውና አስተካክለው በመሥራት በመልካምነት እሴት አስውበውና አክብረው እኛ አለንበት ዘመን ጋር አድርሰዋታል፡፡ ለዚያም ነው
‹የሚጥሩ ሰዎች ለዕውቀት የታጠቁ፣
በጣም ክቡር ናቸው እንደ አልመዝ እንደ ዕንቁ፡፡›የተባለላቸው፡፡
አንድም ‹ጥበብ ማለት የተዋህዶ ቅኔ ነች› ባልነው ትመሠጠራለች፡፡ ተዋህዶና ቅኔ የኢትዮጵያ ሊቃውንትን ለዘመናት ያስጠበቡ፣ ገና ዓለም በሥጋዊ ዓይኑ በአግባቡ ያላያቸው ድንቅ ጥበባት ናቸው፤ የሚለያዩት በስማቸው እንጂ በምሥጢር በአንድነት ይገናዘባሉ፡፡ ለዚያም ነው ጥበብ የተዋህዶ ቅኔ የተባለችው፤ ዕንቆቅልሻዊ ተፈጥሮ አላት፡፡ አንድም ጥበብ ማለት አእምሯችን መጥቆ ውስብስቡን፣ የማይታየውንና ረቂቃዊን ዓለም በሚታየው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸርና በማዋሃድ እየለየ የሚፈታባት የኹለት ኑባሬያት ተዋህዶ የሆነች ቅኔ ወይም የሰምና የወርቅ ምሥጢራዊ የተራቆ ትርጉምን ያቀፈች ድንቅ ነገር ነች፡፡፡ በዚህም አዕምሯችን የማይታየውንና መልስ ያልተገኘለትን ስውርና ውስብስብ ክስተት መልስ ባለውና ግልፅ ሆኖ በሚታወቀው እያነጻጸረና የሚታወቀውን ተጠቅሞ ውስብስቡን እየፈታ፤ ያልተገለጠውን ደግሞ ‹ምንድን? ለምን? እንዴት?› በሚሉ ጥያቄዎች እያበጠረ ሥውሩን ገልጾ የሚለይባት ማጉሊያ መሣሪያው ናት፡- ጥበብ፡፡
በዚህ የተነሣ የዓለማችንን ጠቢባን በተዋህዶዋ ዕንቆቅልሽ፣ በቅኔዋ የምሥጢር አፈታት በኹለት ቡድን ተለያይተው እንዲደባደቡ አድርጋቸዋለች፡- ሐሳባዊያንና ቁሳዊያን በሚል፡፡ ምሥጢርና ጥልቅ በኾነው በወርቃዊ ሐሳቧ፣ ግልፅ በኾነው በሰማዊ ግዝፈቷ (ቁሷ) ዕንቆቅልሽ ኾናባቸው ሲራኮቱባት ይኖራሉ፡፡ ይሁንና እነሱ ተለያይተው በቡድንና በውገና ሲሟገቱ ቢኖሩም እሷ በተዋህዷዊ ቅኔዋ እየሣቀችባቸው የየትኛቸውን ክስ ሳትጠየፍ፣ የየትኛቸውንም ፉከራ ሳታጸድቅ በተዋህዶዊ ተቀኝቶዋ አለች፤ እንዳለች፡፡ በዚህ ተዋህዷዊ ቅኔዋም ዓለምን ተቆጣጥራ፣ ያለም ጠቢባን ዕንቆቅልሽ ሆና፣ ፍቅረኛቸውም እንደሆነች አለች፤ እንዳለች፡፡ ታዲያ የጥበብ የዕንቆቅልሿ ማጠንጠኛ ይህ ተዋህዷዊ ጠባይ ወይም ቅኔያዊ የምሥጢር ሥፍራ አይደለም ወይ? በእውነቱ ምሥጢሯ ቢገባቸው ኖሮማ ሐሳባዊያን የሚያይቱን፣ የራሳቸውንም ቁስነት (አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ መሆናቸውን፤ ባለቅኔውም ‹ለሠሪው ለመስጠት አፈሩን ይዣለሁ፣ ገል አፈር መኾኑን ተረድቸዋለሁ› ያለውን) ባልካዱ፤ ቁሳዊያንም ግድግዳ ላይ አፍጠው ባልቀሩ ነበር፤ ችግሩ ‹ቅኔ አያውቁማ! የቅኔ ፓውዛ የላቸውማ!› እንዳሉት ነው ታላቁ የቅኔ ሊቅ ንቡረዕድ ክፍለ ዮሐንስ፣ ምሥጢር ከግልጽ ወይም ወርቅ ከሰም ጋር ያለውን ግንኙነት አላስተወሉማ!፡፡ የተዋህዶ ቅኔ ማለትም ጥበብ በዚህ ዕንቆቅልሽ ያላትን ምሥጢር መመርመር ነው፤ ተዋህዷዊነቷን፣ ቅኔያዊነቷን ተረድቶ መጠበብ ነው፡፡
ጥበብ የተዋህዶ ቅኔ መኾኗ ብቻ ሳይኾን በሰባት አዕማዳት የቆመችም ቤት ናት፡፡ ይህንን በሚመለከት ጠቢቡ ሰለሞን ‹ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ሰባት አዕማዳትንም አቆመች› (ምሳሌ 9፣1) ይላል፡፡ ጠቢቡ በእውነትም ታላቅ ጠቢብ ነበር ማለት ይቻላል፤ አባባሉንም ዝም ብሎ አልተናገረም፤ የሚያስገርም ምሥጢርን አምቆና አዋህዶ ገልጾበታል እንጂ!፡፡ ስለሆነም ይህንን ነጥብ መመርመር የጥበብን ተፈጥሯዊ መስተጋብር ለመረዳት ይጠቅማል፤ የጥበብን ቤት ምንነትንና የሰባት አዕማዳቷን ምሥጢር ተንትኖ አንድምታውን ለመረዳት መሞከርም አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ሰለሞን ጥበብን ለምን በቤት መመሰል፣ በሰባት አዕማዳት መቆሟን መግለጽ አስፈለገው? አዕማዳቱስ ምን ምንድን ናቸው? እንመልከታቸው፡፡
ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ (በተለይም ሰለሞን በተናገረበት የዕብራውያን ልማድ፡- በመሠረቱ ንጉሥ ሰለሞን ራሱ ከእኛ የተወሰደውን መሠረት አድርጎ የተናገረው ይመስላል፡- ግን ደግሞ የእኛና የእነሱ ከማለት ይልቅ ጥበባዊ ምሥጢሯን መመርመር ይሻላል) ሰባት ቁጥር የፍጽምና፣ የምሉዕነትና የመደምደሚያነት ምልክት ነው፡፡ ይህም ዝም ተብሎ ሳይሆን የተፈጥሮ አሠራርንና የጊዜ ዑደትን በማስተዋል፤ ሌሎችንም የመንፈሳዊ ትርጓሜያት በማመሥጠር የተነገረ የጥበብ ፍች ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሰማያት ሰባት ናቸው ፤ ፍጥረታት የተፈጠሩባቸው ቀናትም በሰባት ዕለታት ነው ተከፍለው የጊዜ ዑደትን የሚያከናውኑት፤ የመጨረሻው ፍጡር ሰውም ቢሆን ፍጽምናን ያገኘ ድንቅ ፍጥረት የሆነው ሰባት ባሕርያትን ስላሟላ ነው፡፡ ስለዚህ ጠቢቡ ሰለሞን የጥበብ ቤት ያለው አጠቃላይ የፍጥረታት መኖሪያ የሆነውን አጽናፈ-ዓለምና በዚያም የሚገኙትን ፍጥረታተ-ዓለም ነው፤ ይህም በሰባት ሰማያት ተደልድሏል፤ ‹ሰማይ› ማለት ራሱ ሰባት በውሃ የተከፈለ ሥፍራ (ሰ-ማይ) ማለት ነውና፤ አንድም ፍጥረታት በሙሉ በሰባቱ ሰማያት ተሠራጭተው በሰባቱ ዕለታት ውስጥ ተፈጥረው ተፈጽመዋልና፤ የጊዜያት ቀመርም የተመሠረተው በዚህ ነው፡፡ በሌላ በኩል የፍጥረታት ሁሉ ምሥጢር የተጻፈበት አስደናቂው ፍጡር ሰው ነው፤ የሰው ልጅ የተሟላ የጥበብ ቤት፣ የዓለምና የፍጥረታት ዕንቆቅልሽ መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ ይህንንም በሰባት ባሕሪያቱ አምቆና አትሞ ይዟል፤ የሰው ልጅ ድንቅ ተፈጥሮን ወይም የጥበብ ቤትነት ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሰባት ባሕርያት የተባሉትም ክቡድነት (መሬትነት)፣ እርጥብነት (ውሃነት)፣ ሞቃትነት (እሳትነት)፣ ተንቀሳቃሽነት (ነፋስነት)፣ ለባዊነት (አመንጭነት)፣ ነባቢነት (ተናጋሪነት) እና ሕያውነት (በሕይወት መኖር) ናቸው፡፡ የትኛውም ፍጡር አፈጣጠርም ከእነዚህ ባሕርያት ሊወጣ አይችልም፤ ስለኾነም የዓለማት የፍጥረታት ምሥጢር ኹሉም በሰው ልጅ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሰለሞንም ከሰማይ በታች ምንም ዐዲስ ነገር የለም ሲል ምን ያህል የተፈጥሮን ምሥጢር ጠልቆ መረዳቱን ያሳያል፡፡ ይህችን የ‹ሰለሞንን የጥበብ ቤት› አበው ተመራምረውባታል፤ በቅኔያቸውና በትርጓሜያቸው አመሥጥረዋታል፤ ስለዚህ ምሥጢሯ ብዙና ድንቅ ነው፡፡
አበው ይህችን የተፈጥሮ አሠራርና ምሥጢር የያዘችውን ጥበበ በፊደል ገልጸዋታል፤ በፊደል ገበታቸው አማካይነት ለሰው ልጆች (የጥበብ ምግብነት) ሠርተው አቅርበዋታል፤ የፊደል ጥበብ ምሰሶዎቿም ሰባቱ ሆህያት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት የፊደል ሆሄያትም የዓለምን የጥበብ መዝገብ መዝግበው ይዘዋል፤ ማለትም አበው ፊደልን ሲሠሩ የታሪካቸው መዝገብ፣ የፍልስፍናቸው አመሥጥሮ፣ የፍጥረታት ሥዕላዊ ወካይ ምልክት፣ የሃይማኖታቸው ምሥጢር መተርጎሚያ፣ የታሪካቸው መዝገብ፣ ወዘተ… ማስተማሪያና ማስተላለፊያ መሣሪያ አድርገው ነው፡፡ ለዚያም ነው፡-
‹ሊቆች በአንጎላቸው ዕውቀት ያረገዙ፣
ጥበብን ፊደልን (ትምህርትን) ወልደዋል በብዙ፡፡› የተባለላቸው፡፡
እያንዳንዱ የፊደል ሆሄም ከፍጥረታት ምንነት፣ ከጊዜያት ዑደት፣ ከሰው ልጅ ባሕርያት፣ ከሌሎች መንፈሳዊ ትርጉሜያት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የፊደል ፍልስፍና ማጠንጠኛም በእውነተኛ የተፈጥሮ ክስተት ላይ የተመሠረተ፣ በዕውቀትና በብልሃት የተሠራ የመልካምነት ውህደትና የጥበብ ቋት ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለም ከዚህ ከፊደል ጥበብ የበለጠ አስደናቂና የብልህና ጥበበኛ ሰው ሥራ የለም፤ ስለዚህ ጥበብ ማለትስ ፊደል ናት፡፡ ለዚያም አበውም የፊደልን አስደናቂነት ሲገልጹ ‹ፊደል ማለት ነቅዓ ጥበብ ማለት ነው፤ ምክንያቱም የጥበብ ኹሉ ምንጭ መገኛ ፊደል ናትና› ያሉት፡፡ ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በታመቀ ግጥማቸው ፊደልን ሲተረጉሙ፡
‹የፊደል ዘይቤ፣ባጭር ቃል ሲፈታ፣
የቋንቋ ድብኝት፣ የቃል ኹሉ ጎታ፤
የመጻሕፍት ምንጭ፣ የምሥጢራት ነቅ፣
ቢቀዳ ቢቀዳ፣ ውሃው የማያልቅ፡፡› ብለው ነው የገለፁት፡፡
ይህንን ስንረዳም እውነትም የሰብዕ ጥበብ ጥልቀትና የፊደል አሠራርስ ምሥጢሩ ይደንቀናል እንላለን፡፡ እዚህ ላይም ለራሳችን ‹ወይ ጠቢቡ ሰለሞን የኢትዮጵያውያንን አስደናቂ የጥበብ አዕማዳት ዐይቶና አስተውሎ በመደነቅ ‹ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶዎችን አቆመች› በማለት ተናግሯል ወይም የኢትዮጵያ ሊቃውንት የሰለሞን ንግግር ምሥጢሩ በአግባቡ ገብቷቸው ተመራምረውበታል፤ ከዚያም አልፈው በባህላቸውና በፊደላቸው ለኅበረተሰቡ ሠርተው እንዲገለገልበት አድርገዋል› ልንል እንችላለን፡፡ በየትኛውም ቢሆን የሊቃውንቱ ጠቢባንነትና ርቅቀት አስደናቂ ነው፡፡
የዚች የጥበብ ጉዳይ በጣም ጥልቅ ነው፤ ከላይ የሚታይ ፍች ብቻ ሳይሆን ምሥጢራዊና መንፈሳዊ ትርጓሜም አላት፡- ‹ጥበብ ቅኔ ናት› የተባለውም ለዚያ ነው፡፡ ስለኾነም ከሥጋዊ ዕውቀትም አልፎ መንፈሳዊ መስተሐልይን (ስልሳሌን) ገንዘብ ማድግ ትፈልጋለች፤ ከእንብላ እንጠጣ፣ እንሽና፣ እንዘሙት፣ እንዝናና… ከሚባሉት የዘለለት ዕውቀትና ስሜት በላይ አልፋና መጥቃ፣ ረቃና ተሰውራ የምትገኝ ስለኾነች፤ ምሥጢሯን ለመፍታት ጠቢባኑ የሚተጉባት፣ ፍጽምናዋን ለማወቅ ሌት ተቀን ሲመረመሯት የሚኖሩባት ናት፡- ጥበብ፡፡ ምክንያቱም ዓለማችን የሚታይ የሚዳሰስ ጥበብ ብቻ አይደለም ያለት፤ ብዙ አስደናቂና ሥውር ጥበባትንም አምቃ ይዛለች፤ የሃይማኖትና የመንፈሳዊ ጥበባትም ባለቤት ነች፡- የሚያስተውልላት እየጠፋ ነው እንጂ!
ይህንን በሚመለከት አፍላጦን (ፕሌቶ) የተባለው ፈላስፋ ‹በዚህኛው ዓለም የሚገኝ ፍጥረት ኹሉ የእውነተኛው ዓለም ነፀብራቅ ነው› የሚል ክርክር አቅርቦ ነበር፡፡ ይህንን የእኛ አባቶች ደግሞ ‹በሰማይ የተሠራ በምድር ተሠራ› ብለው ጨርሰውታል፤ አንድም አንድ ነገር አካሉን ስታየው በረቂቅነት ብሕርዩም በአእምሮህ ይጻፋል እንጂ በግዝፈት ብቻ ልታውቀው ወይም ልትረዳው አትችልም፡፡ በመሠረቱ ዝርዝር የኾነ ፍጥረት ኹሉ የወል መለያያ ይኖረዋል፤ በዝርዝሩ ነገር በሚንፀባረቀው ክስተት የወሉ ማንነት (ባሕርይ) ይታወቃል፤ ይህም አንድ ነገር የወል ማንነትና የግል ማንነት በአንድነት ይኖሩታል፤ ሁለቱም የማይነጣጠሉ ግን አንድ የኾኑ ናቸው፤ ዝርዝሩ በአካል የወሉ ደግሞ በባሕርይ ይገለጻሉ፡፡ ‹ባሕርይና አካል ሳይለያዩ የተለያዩ ናቸው› እንዲሉ አበው፤ ወልነትና ዝርዝርነትም የተያያዙ ግን የማይለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ፍጥረት ኹሉ ዝርዝር ቢኾንም በወልነት ወደ አንድነት ይሰበሰባል፤ በዝርዝርነቱም ይበተናል፡፡ ‹የጊዜያት ኹሉ ድምር ዘላለማዊነት ነው› እንዲል መርማሪ፤ የፍጥረት ኹሉ መቋጫውና መደምደሚያው፤ በእግዚአብሔር ተገኝቶ በእሱ ሥርዓት ውስጥ ኖሮ ህልውናን በጊዜ ገደብ መቋጨት ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ ከዚህ በላይ አልፋ የዘላለማዊነትን ክብር የተጎናጸፈች ናት፤ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ገንዘብ በማድረግ ትመጥቃለች እንጂ በፍጥረታት ቅንብር ብቻ የምትወሰን አይደለችም፡፡
‹ጥበብ የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ ናት› እንዳልነውም ‹አንድም ሦስትም የሆነው የእግዚአብሔር የምሥጢር ቤት ናት›፡- ምሥጢረ-ሥላሴ ይሏታል አበው ከእግዚአብሔር ህላዌ ጋር በማገናዘብ፡፡ ለእዚያም ነው ‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው› የተባለው (ምሳ.1፣7)፡፡ ምክንያቱም ጥበብ የበቀለችበት ሥር መሠረቷ እግዚአብሔር ነውና፡፡ ኅሩይ ወ/ሥላሴም፡-
‹የጠቢባን አባት አንተ መሰልከኝ፣
መልካም ዓይነት ጥበብ እንድትሠራልኝ፡፡› ብለዋል (ወዳጀ ልቤ፣ ገጽ-70)
አንዱ ፈላስፋም ‹የዕውቀት ሥር መሠረቷ ሃይማኖት፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ ለሰው ሁሉ ባሕርየ-መልካም መሆንና ከወንድም ከጓደኛም ጋር መፋቀር ነው፡፡› ብሏል (አንጋረ-ፈላስፋ፣ ገጽ-34)፡፡ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ የሆነው ወልደ-ሕይወት ደግሞ
‹ፀሐይ የብርሃን መሠረት እንደ ሆነ እንዲሁ እግዚአብሔርም የጥበብ መሠረት ነው፡፡ መንፈስ የሕይወት ምንጭ እንደ ሆነ እንዲሁ እግዚአብሔርም የእውነት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ … መመርመር ወደ ጥበብ የምንገባበት በር ነው፡፡ ዕውቀትም ይህን በር ከፍተን ወደ አዳራሹ ምሥጢር ገብተን ከጥበቡ መዝገብ የምንካፈልበት እግዚአብሔር የሰጠን ቁልፍ ነው፡፡ ((የኢትዮጵያ ፍሎሶፊዎች፡ ሐተታ ዘርአ-ያዕቁብ ወወልደ-ሕይወት፣ ገጽ፣46-47) በማለት ነው ጥበብ እግዚአብሔርን መሠረት እንደምታደርግ የገለጸው፡፡
ይህ ከኾነም ጥበብ የሥላሴ ምሠጢር መኾኗ እሙን ነው፤ ለዚያ ነው አበውም ‹ጥበበ ሥላሴ› የሚል ስም የሚያወጡት፡፡ ለክርስትና ሃይማኖት ምሥጢረ ሥላሴ የምሥጢራት ኹሉ መሠረት ነው፤ የጥበብም ሥላሴነት (የእውነት፣የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ መኾን) የአስተሳሰብ ኹሉ መሠረት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጥበብ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ (ቅኔ) ናት› ብለናል፤ መንፈሳዊ ትርጓሜዋ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ‹እግዚአብሔር› የሚለው ቃልም አንድም ሦስትም የሆነውን የአምላክ ስም በተዋህዶነት የሚገልፅ ነው፡፡ ማለትም እግዚአብሔር ማለት ‹እግዚእ=ጌታ፣ አብ=አባት፣ ሔር=ቸር› በማለት ተዘርዝሮ ይፈታል፤ ይህም ‹አብ ወልድ መንፈስ-ቅዱስ› ማለት ነው፡፡ በዚህም አብ በመሠረትነት (በእውነትነት)፣ ወልድ በሠሪነት (በዕውቀትነት)፣ መንፈስ-ቅዱስ ደግሞ ሕይወት በመሥጠት (በመልካምነት) የሚገለጹ ናቸው፡፡ የጥበብ ተዋህዶነትም እዚህ ላይ ትመሠጠራለች፤ እውነት ያለ ዕውቀት አትገለጽም፤ ያለ መልካምነትም እውነትነቷ አይቆምም፤ ያለ እውነትም ዕውቀት አትኖርም፤ ያለ መልካም እሴትም ዕውቀት ትርጉም አይኖራትም፡፡ ስለዚህ ጥበብ አንድም ሦስትም ናት፤ ሥላሴ ማለት ናት፡፡ ይህም ምሥጢሯን ጥልቅ ያደርገዋል፡፡
ለነገሩ የጥበብን ጥልቅነትና እግዚአብሔርነት አለቃ ዘነብ ኢትዮጵያዊ መጥነውና ተጠበው ገልጸውታል፤ እንዲህ በማለት፡
‹እግዚአብሔር አብ ጣት ነው፣ እግዚአብሔር ወልድ ብዕር ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ቀለም ነው፤ ሰማይና ምድር ወረቀት ናቸው፤ ፊደሉም ፍጥረት ነው፤ እግዚአብሔር አብም በቃሉ ሰማይንና መሬትን ፈጠረ፤ ያለባቸውን ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ፤ በመንፈሱም አጠናቸው… የዚህን ዓለም ሥሩን አገኛለሁ ብዬ ቆፈርሁት፤ ጽኑም ድንጋይ ሆነብኝ ድጅኖ አሳቤም ሁሉ አለቀ፤ እንዲያው ባየው ባስተውለው ሥሩ እግዚአብሔር ነው፡፡›(መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ፣ ገጽ 14-15)፡፡
ለእኔ ድንቅ ገለጻ! የጥበብ ምሥጢር ያስተዋለ አነጋገር ማለት ይህ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹ጥበብን ለምን ትፈልጓታላችሁ? ከገበያ አትገዛ? ከምድር አትበቅል? ከኪሩቤል ጀርባ ካለው ከሕይወት ምንጭ በሃይማኖት ብርጭቆ ቅዱ፡፡› ብለዋል አለቃ ዘነብ!(ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ-8)፡፡ ለዚህ ነው አበው በምናኔና በብህትውና ጥበብን እያውጠነጠኑና በእሷ ተደንቀው እየተመሠጡ ቤት ንብረታቸውን ትተው የሚጠፉት፡፡ ‹ፍልስፍና ማለት ጥበብን ማፍቀር ነው› ማለትስ ይኸ አይደለም ወይ?
በተለይ ከክርስትና ሃይማኖት አንጻር ስናጮልቅ ጥበብ ክርስቶስን ትወክላለች፡፡ ‹እንዴት ሆኖ?› ማለት መልካም ጥያቄ ይኾናል፡፡ በኹለት መልኩ ማየት ይቻላል፤ አንድም ከጥበብ ቅኔነት አንጻር፤ ሌላም ከጥበብ ፍጽምናን ናፋቂነት አኳያ!
‹ጥበብ ቅኔ ናት› ብለናል፤ ቅኔ ደግሞ በተዋህዶ የከበረ ምሥጢርን ያቀፈች ጥበብ ነች፡፡ ይህ ዓለም ደግሞ በኹለት ነገሮች ተዋህዶ የሚኖር ክስተት ነው፤ ለምሳሌ በሐሳብና በአዕምሮ፣ በወልና በዝርዝር፣ በባሕይና በአካል፣ በመንፈሳዊ ነገርና በዓለማዊ ክስተት፣ ወዘተ፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ተዋህደው በአንድነት የሚገኙ መሆናቸው ድንቀትን ይፈጥራሉ፡፡ ለምሳሌ የሐሳብና የአዕምሮ ግንኙነት በፍልስፍናው ዓለም ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ፣ የፍልስፍና አሳቢዎች የተባሉትን በጎራ አስለይቶ የሚያጠዛጥዝ ነጥብ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በአሁኑ ጊዜ የፍልስፍና ምህራኑን ይዘታዊ-አካባቢየዊ (Continental) እና ቅርጻዊ-ፊደላዊያን (Analytical) በሚሉ ጎራዎች አከፋፍሎ የሚያዋጋቸው የዚህ የሐሳብና የአዕምሮ ዕንቆቅልሽ የፈጠረው ቡድናዊነት ነው፡- ምንም እንኳን አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ቢሆንም (መንታዊ ምሥጢሩ ሲተው ቅኔነቱ ይደበዝዛል፤ በዚህ የተነሣም ድንቀቱ ይጠፋል፤ ፍልስፍናም የት/ቤት ሠልጣኞች የጥቅስ ማውጫ ለመኾን ትገደዳለች)፡፡ ያም አለ ያ ምሥጢሩ ያለው የሚታወቀውና ቁስ የሆነው አዕምሮ እና የማይታይ፣ የማይዳሰስና መንፈሳዊ የሆነው ሐሳብ በተዋህዶ ከብረው ሰው የሚለውን ፍጡር ያስገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ሰው በአንድ በኩል የምጥቁ፣ የረቂቁና ያይወሰኔው ሐሳብ፤ በሌላ በኩልም የግዙፉ፣ የውስኑና የተቀያያሪው የፍጥረታት ምሥጢር ማዕከል ነውና (የነፍስና ተዋህዶም በምሥጢር ከዚህ ጋር ተያያዥ ነው)፡፡ ይህ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ረቂቅ፣ ምጡቅ፣ ስፉህና ምሉዕ የኾነው መለኮት፤ ግዙፍ፣ ውስን፣ ተዳሳሽና የሚታይ የኾነውን ሰው በተዋህዶ ገንዘብ አድርጎ የተገለጸ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፤ የጥበብ ቅኔነትም እዚህ ላይ ነው፤ በተዋህዶ መክበር (መገኘት)፡፡ ‹ጥበብሰ ክርስቶስ ውእቱ፡- ጥበብ ማለት ክርስቶስ ነው› እንዳሉ አበው፤ ቅዱስ ጳውሎስም ‹የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው› (1ኛ ቆሮንቶስ 1፣ 24) ብሎ ጨርሶታል፡፡ የበለጠ ሲያብራራም
‹በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን… ዓለም ገዦች ጥበብን አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር› ብሎ ነው የገለፀው፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 2፣ 6-8)
በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ ናት› ብለናል፡፡ እነዚህን መሠረታተ-አሚን (Principles) በምሉዕነት ወይም በፍጽምና አማልቶ የተገኘ ደግሞ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ‹እውነትና ሕይወት እኔ ነኝ› ብሏል፤ በዕውቀቱም ዓለም ሳይፈጠር የነበረውን ሁኔታ ሳይቀር ተናግሯል፤ ‹ቃል ነበር› እና ‹ኹሉ በእሱ ኾነ› የሚሉ ገለጻዎችም የሚገልጹት ዕውቀታዊ ጥበቡን ነው፤ በመልካምነትም ቢሆን ‹የላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት፤ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የበዛባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት፡፡› በማለት ነው ሐዋሪያው ያዕቆብ የገለጸው (ያዕቆብ፤ 3፣ 17)፡፡ የጥበብ የተዋህዶነት ምሥጢር ጥልቅ ነው የሚባለው ዝም ተብሎ ሳይኾን በምትሠጠው የፍካሬ ትርጉም ጥልቀትና አስደናቂነት የተነሣ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ጥበብ ብቻ ሳይኾን ፍቅርም ነው፤ ‹ክርስቶስ ፍቅር እንደኾነ ኹሉ እርስ በራሳችሁ ተፋቀሩ› እንዲል ሐዋርያው ጳውሎስ፡፡ ስለዚህ ፍቅር ከጥበብ ጋር ያለውን መስተጋብር ለመረዳት ‹ፍቅር ምንድን ነው?› የሚል ጥያቄ እናንሣ፤ በዚህም ‹ፍቅር የኹለት አካላት (ሰዎች) መሳሳብ ወይም ለአንድነት መፈላለግ ነው› የሚል መልስ ማግኘት እንችላለን፤ በተዋህዶ አንዱ የሌላው ለመሆን ወይም የሌላውን የራሱ ለማድረግ የሚሳሳቡበት ማግኔት ነው፡- ፍቅር፤ ስለዚህ ፍቅርን ‹ማግኔተ-ተዋህዶ› በማለት መተርጎም ይቻላል፤ በማግኔጢሳዊ ኃይሉም የተዋህዶ ቅኔ ይመሠጠርበታል ፍቅር (ለምሳሌ ሴትና ወንድ በመሳሳብ ተፈላልገው በሚፈጽሙት ሩካቤ ልጅ የሚባል ምሥጢርን ያስገኛሉ)፡፡ ይህ ከሆነም ፍቅር፣ ተዋህዶና ቅኔ የምሥጢር ተያያዥነና አንድነት አላቸው፡፡ ማለትም የፍቅር ግቡ ተዋህዶነት ነው፤ ተዋህዶነት ደግሞ ጥልቅ ምሥጢር ያለበት አንድነት ነው፤ የተዋህዷዊ አንድነት ምሥጢሩም ቅኔን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ለፍቅር ማግኔጢስ ኃያልነት ወይም የተዋህዶነት ምሥጢር ጥልቀት የቅኔነት ጠባዩ መሠረት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ‹ፍቅርሰ ኃያል ውእቱ፡- ፍቅር ኃያል ነው› እንዲል ሐዋሪያው ጳውሎስ!
የፍቅርን ኃያልነት ለማየትም የወንድና የሴት ምሥጢራዊ የመሳሳብ ኃይል ምስክር ይሆነናል፡፡ ምክንያቱም የጾታዊ ፍቅር እንኳን እንዴት አቅልን እንደሚያስት፣ አካልንና ስሜትን እንደሚሰቅጥ የደረሰበት ያውቀዋልና፡፡ ለምሳሌ አንዷን ኮረዳ ያፈቀረ ሸጋዋ፡-
‹የፍቅሯን አረቄ ብቀምሰው ሰክሬ፣
መራመድ አቃተኝ ታሠረ እጅና እግሬ፡፡› ብሏል፤ አትፍረዱበት፡፡ በኃያል ማግኔት የተያዘ ብረት ወደየት ሊያመልጥ ይችላል? ወይ ብረትነቱን ካልተወና ማግኔትነቱ ካልጠፋ መሳሳቡ ያለ ነው፡፡ እናም ኩብሉም በአበሻ አረቄ እንደሰከረና ራሱን እንደሳተ ሰው መራመድም ኾነ መንቀሳቀስ ቢቸግረው አይደንቅም፤ ይልቁንም በዚህ ማግኔጢሳዊ ኃይል በመወጠሩ ሊታዘንለት ወይም ሊቀናበት ይገባል እንጂ!
እንዲሁም በአንዱ ጉብል ፍቅር ተቸግራ የተጨነቀች ኮረዳም ሐሜታዉ ቢያስቸግራት፡-
‹አበደች ይሉኛል፣ ከነፈች ይላሉ፣
እንደኔ በፍቅር ነደው ያልከሰሉ፡፡› ብላቸዋለች፤ ዐያችሁልኝ የፍቅርን ኃያል እሳትነት! ከማብሰል አልፎ ሲያሳርር!!!
አዎ! ፍቅር ኃያል ማግኔት ነው፤ ኃያልነቱም አምላክን ስቦ ሰው እስከ መሆን አድርሶታል፤ ለዚያም ነው አበው ‹ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እም መንበሩ ወአብጽሖ እስከለሞት› ያሉት፤ ‹አምላክ የሰው ዘርን ማፍቀሩ ከመንበሩ ጎትቶ ሰውነትን ገንዘብ አድርጎ እስከሞትም እንዳደረሰው› ሲገልጹ፤ ፍቅር የትዛዛቱ ሁሉ ማሠሪያስ አይደል? ቅዱስ ጳውሎስስ ‹እምነት፣ ተስፋና ፍቅር› ለዘላለም ፀንተው የሚኖሩ የዓለሙ መሠረት መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ ‹ከኹሉም ፍቅር ይበልጣል› ብሎ አይደል የደመደመው? ‹ክርስቶስ ውእቱ› ነውና!
ስለዚህ ፍቅር ይህ ከኾነ፤ የጥበብ ትርጓሜ ምጥቀቱ ከኹሉም ነገር ከበለጠ፤ ስንቱ ሊቅ በጥበብ ፍቅር ተነድፎ ቢቀውስ፤ በጥበብ ፍቅር ሰክሮ ቢነባረር፤ በጥበብ ፍቅር ታሥሮ ቢጃጃል፣ ቢቄል፤…. ምን ይደንቃል? የፍቅር ጠባይ አይደለም ወይ? የጥበብንስ ማግኔጢስ እንዴት ተቋቁመውት መቆም ይችላሉ? ሰዎች በእሷ ራሳቸውን ቢጥሉ እሷን እሷን የሚያሳስበውን፣ ቀልብ የሚያስት መስተፋቅሯን አስነክታቸው አይደለም ወይ? እኛ የጥበብ ጾመኞች ስለሆንን ብቻ እነሱን መኮንን አለብን እንዴ? ብህትውና ማለትም እኮ በጥበብ ፍቅር ተነድፎ፣ ከእሷ ጋር ተጋብቶ ተገዥዋ ኾኖ ለመኖር ከኅብረተሰቡ መለየት ማለት ነው፡- ከገባን፡፡ በብህትውና እሷን እያደነቁ በፍቅሯ ውስጥ መኖር እኮ ነው ጠቢባንነቱ! ሞኞ! ምናኔ ከማሰብ መታቀብ መሰለህ እንዴ? ዓለምን የሚንቁት ካለም የበለጠ ነገር በማግኘታቸው አይመስልህም? አፍላጦን ራሱ ‹ጥበብን ስትሰበስብ ገንዘብንስ ለምን አልሰበሰብክም? ቢሉት ጥበብ ፈጽማ የከበረች ትኾን ዘንድ ብዬ ነው› ብሎ መልሷል፡፡ (አንጋረ-ፈላስፋ፣ ገጽ-13)
ሐሳባችን እንጠቅልለው እስቲ ከዚህ በላይ ጥበብ ማለት ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ ናት› ብለናል፤ ፍቅር ደግሞ ‹ማግኔተ-ተዋህዶ› በሚል ተስማምተናል፡፡ በዚህ መሠረት ፍቅር የኹለት ነገሮች የተዋህዶነት ማግኔት ከሆነ፤ ጥበብም ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ› ከሆነች፤ ‹ተዋህዶ› የሁለቱ የፍቅርና የጥበብ የጋራ ባሕርያቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነም ‹ፍቅረ-ጥበብ› ወይም ፍልስፍና ስንል ‹ማግኔጢሳዊ የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ› ማለታችን ይሆናል፡፡ እንዲሁም ‹ፍቅር፣ ተዋህዶና ቅኔ በምሥጢር አንድ ናቸው፤ በአሀዳዊነት ይገናዘባሉ› ብለናል፤ ምክንያቱም ሦስቱም የውህደትን ምሥጢርና ጥብዓት የሚሰብኩ ናቸው፤፤ ማለትም የፍቅር ግብ ተዋህዶነትን እውን ማድረግ ነው፤ ተዋህዶ ደግሞ የኹለት (የብዙ) ነገረች አንድ የመኾን ምሥጢር ነው፤ ይህም ምሥጢራዊ አንድነት ቅኔ ይኾናል፤ ቅኔ የምሥጢር ጉርጓድ የኾነ የድንቀት ቋት ነውና፡፡ በዚህ መሠረት ፍልስፍና ስንል ጠለቅ ካደረግነው ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ቅኔ› ማለታችን ይሆናል፤ ስለዚህ ፍልስፍና ‹ጥበበ-ቅኔ› ናት፡፡
በሌላ አገላለጽ ፍልስፍና ማለት እየተደነቁ ጥልቋን እውነት መፈለግ አይደል? የፍልስፍና መሠረቱ አስደናቂነትና የተደበቀን መፈለግ ከኾነ ቅኔ ኾነ ማለት ነው፡፡ የኹለቱ ግብም እውነትን መግለጥ ነው፤ በመካከላቸው ልዩነት ያለው በአፈላለግ ስልታቸው ነው፤ ቅኔ በኅብር ዘዴ ይጠቀማል፤ በተለምዶ የምናውቀው ፍልስፍና ደግሞ ነጠላ የአመክንዮ ስልትን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ማለት የዘመናችን ፍልስፍና እንደመኪና በቀጥታ አስፋልት ነው ሚጓዘው፤ ሞተሩን ይዞ መንገድ ሳይለቁ መብረር ነው፤ የሚያስፈልገውም የትራፊኩን ሕግጋት (የሥነ-አመክንዮ ሕጎች) አውቆ በመጠበቅ መጓዝ ነው፡፡ ቅኔ ደግሞ ሲጓዝ እንደሰው በኅሊናው እያሰበ (ኅሊና የምሥጢር ቋት ነው) ነው በአካላቱ የሚንቀሳቀሰው፤ ተዟዙሮ ለማየት ይሞክራል፤ አቋራጭና አስደሳች መንገድ ካገኘ ለመጠቀም ይሞክራል፤ ‹የንግግር ለዛው እጥረቱ› ቢባልም ያለምሥጢር መንገድ አይገፋለትም፤ በአጭሩ መንገድ እየተጋዙ ዙሪያ ገባውን ይቃኛል እንጂ፡፡ ለዚያም ነው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቅኔን ለአንድምታ ትርጓሜያቸው መሠረተ-ግብዓት የሚያደርጉት፤ የቅኔን ጥበብም የፍልስፍና (የጥበባት) ሁሉ ጉልላት ያደረጓት፡፡ ከበደ ሚካኤልም፡-
‹ሰዎች የፈጸሙት የተግባር ሃተታ፣
ክብደቱ ግምቱ ሲሰፈር በጾታ፣
መዓረግ ተሰጥቶትም ሲደለደል ቦታ፣
ቅኔ ተቀመጠች አክሊል ተቀዳጅታ፡፡› ያሉት፤ የጥበብ የቅኔነት ደረጃ ገብቷቸው ነው፡፡
ይህ ከኾነም ፍልስፍናን ከኢትዮጵያውያ ሊቃውንት አንጻር ስንመለከተው ቅኔነትን ገንዘብ ያደረገ መኾን አለበት፤ ቅኔነቱን ከተወ የነጠላ ዕውቀት ይኾናል፤ የነጠላ ዕውቀት ደግሞ ምሥጢር ስለማይኖረውም ምኑን ያስደንቃል? በድንቀት የማያመሠጥርና የሚያስደንቀውን ምሥጢር የማይፈታስ ምን ዓይነት ሊቅ ነው የዐዋቂነት ካባ የሚለብሰው? የጥበብ ቅኔነት ከሥነ-ፍጥረት አኗኗርና አከሳሰትም ጋር የተገናዘበ ነው፤ በተለይ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር፡- ከሰው የበለጠ ቅኔ ምን ሊኖር? አምላክ ራሱን የወከለበት ፍጡር ነው የሰው ልጅ፡- በሹመት፤ ከዚያም በላይ በተዋህዶ ገንዘብ አድርጎታል፡- የአምላክን ባሕርይ፡፡ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የቅኔ ጥበብ ይህንን ኹሉ ያገነዛብ ነው፡፡

Please follow and like us:
error

6 COMMENTS

  1. i could’nt told what u written for us.please keep it up & teach more secretes with regard to filsfina and tibebe.especially world is made from two things example good and bad …etc.

  2. i could’nt told what u written for us.please keep it up & teach more secretes with regard to filsfina and tibebe.especially world is made from two things example good and bad …etc.

Leave a Reply