መሠረታዊ ሎጂክ እና ሕጸጽ

መግቢያ
የሰው ልጅ አእምሮ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አእምሮውም በምክንያት ይመራል፡፡ የምንኖርበት ዓለምም ምክንያት ዓልባ ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ ይህም ምክንያታዊ ዓለም በምክንያታዊ አእምሮ ይታወቃል፡፡ የሰው ልጅ አእምሮም በተፈጥሮው ትክክለኛ ምክንያት ያገኘለትን ነገር ሲያምን ወይም ሲደግፍ ያላገኘለትን ግን ይቃወማል፡፡ ሆኖም አእምሮው ትክክለኛውን ምክንያት ትክክል ካልኾነው ለመለየት የሚቸገርበት ሁኔታ ብዙ ነው፡፡ ‹ለምን?› ቢባል አእምሮው ውስንነት አለበት፤ በስሜታዊነት የመሸፈን ችግር ያጋጥመዋል፤ በተፈጥሮው ያገኘውንና በልምድ ያከማቸውን ዕውቀት የማገናዘብ ችግርም ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህ ከኾነም ሰው ሁሉ ትክክለኛውን ምክንያት በአግባቡ ዐውቆ መጠቀም እንዲችል አእምሮውን በሎጂካዊ (አመክንዮአዊ) ዕውቀት ሊደግፈው ይገባል፡፡ …
አእምሮውን በአመክንዮአዊ ዕውቀት እንዲያበለጽግም ተጠየቃዊነትንና አመክንዮአዊ አመለካከትን የሚያሳዩና የሚያስረዱ በዚህ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍት ያስፈልጉታል፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ዙሪያ በሀገራችን ደረጃ በውጭ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍት ቢኖሩም በሀገራዊ ቋንቋ የተዘጋጁት ግን ቁጥር ውስጥ የሚገቡ አይደሉም፡፡ ስለኾነም በሀገራዊ ቋንቋ ምክንያታዊ አመለካካትንና ተጠየቃዊ ዕይታን የሚያበለፅጉ መጻሕፍት በብዛት ቢጻፉ (ቢተረጎሙ) ጠቀሜታቸው የጎላ ይሆናል፡፡ የዕውቀት ፍሰት በእነሱ ውስጥ እንዲያልፍ ያደርጋሉና፡፡

ማንኛውም ጸሐፊ (ተርጓሚ) አንድ መጽሐፍ ለሕትመት ሲያዘጋጅ (ሲተረጉም) ለራሱም ኾነ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቅም መዝኖ መሆን እንዳለበት እኔም ይህ መጽሐፍ የሚከተሉትን ጠቀሜታዎች ያስገኛል በማለት ተርጉሜ ላቀናብረው ችያለሁ፡፡
1. በአጠቃላይ ጉዳይ አመለካከቱ የሰፋ፣ ከስሜታዊነት የፀዳና ከግላዊ ዕይታ ወሳኝነት የተጠበቀ ዜጋን ለመቅረፅ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብዬ በመገመት፡- በዚህም ‹ሀይ!› ሲሉት ‹ወይኔ!› ወይም ‹ሆ!› ሲሉት ‹ሆ! ሆ!› የሚል ዜጋን ሳይሆን የትኛውንም ነገር በገለልተኝነትና በምክንያታዊነት (በተጠየቅ ዕይታ) እየጠየቀና እያረጋገጠ የሚቃወምና የሚደግፍ ኅብረተሰብን ለመቅረፅና ለመገንባት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል በማለት፡-
2. ለማንኛውም ዜጋ የክርክርና የውይይት ክህሎትንና ስልትን ለማዳበር ይረዳል፡- ነገሮችንም በጥልቀትና በአስተውሎት ለመመርመር ያግዛል የሚል እምነትን በመያዝ፡- በተለይም ለተማሪዎች በትምህርት ቤታቸውና በተለያዩ መድረኮች በሚያደርጓቸው ውይይቶችና ክርክሮች በልጅነታቸው የተጠየቃዊ አቀራረብ ስልትን (የአስተሳሰብ፣ የአነጋገርና የመከራከር ፍሰትን) ለማዳበር ይረዳቸዋል በሚል እምነት፡-
3. የሥነ-አመክንዮ ትምህርትን ምንነትና ይዘት ለማወቅ (ለመረዳት) ዕድሉ ላልገጠማቸው ሰዎችም ይህንን የዕውቀት ዘርፍ በቀላሉ ማግኘትና መረዳት እንዲችሉ ያደርጋል፡- በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ትምህርቱን እየተማሩት በቋንቋ ችግር የተነሳ መሠረታዊ ይዘቱን ቶሎ መረዳት ለሚቸግራቸው በሚረዱት ሀገራዊ ቋንቋና ምሳሌዎች በቀላሉና በአጭር ጊዜያት ውስጥ እንዲገነዘቡት ያግዛቸዋል በሚል ግምት፡-
4. ይህንን የዕውቀት መስክ ተምረውት ላለፉትም መጽሐፉን ቢያነቡት በቀላሉ በማስታወስና ዕውቀታቸውን በማዳበር እንዲጠቀሙበት ያስችላቸዋል ብዬ በመገመት (ፈተና ካለፈ በኋላ ዕውቀቱም ተኖ የሚጠፋ መሆን ስሌለበት) ነው መጽሐፉን ተርጉሜ ያቀረብኩት፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply