በክርስቶስ ትንሣኤ ዙሪያ ያሉ መላምቶች

በካሣሁን ዓለሙ

ሕንጽሃ (ቅኔ)

እንከ ቀራንዮ ኢይበጽሕ እግእነ

እስመ ቀራኒዮ ምድረ ደም ኮነ፡፡

ትርጉም፡-

እንግዲህ ጌታችን ቀራኒዮ አይደርስም

ቀራኒዮ የደም መሬት ሆኗልና፡፡[1]

በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዙሪያ በክርስትና እንደሚታመነው ብቻ ሳይሆን በሌላ በኩልም የሚሰነዘሩ ከክርስትና ውጭ የኾኑ መላምቶችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ የጭቅጭቅ መላምቶች የተነሱትም ከምንፍቅና ፍልስፍና አራማጆች (ለምሳሌ፡-በረትናት ረሰል፣ ኒቼ፣ ሾፐን ሐዎር፣ ሌሎች) እና ከክርስትና ሃይማኖት ተቀዋሚዎች ነው፡፡ ስለዚህ የሚያነሷቸው ምክንያቶች ተፈትሸው ትክክል መኾን አለመሆናቸው መመዘን ይኖርባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓለማም እነዚህን መላምቶች መገምገም ነው፡፡

ዋናው ጥያቄም ‹በክርስቶስ ሞቶ መነሣት ላይ ያለው ትክክለኛው አስተምህሮ የትኛው ነው?› የሚል ነው፡፡ ይህ ጥያቄም ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት በኢየሩሳሌም የተፈጸመው ትክክለኛው ክስተት የትኛው እንደኾነ እንድንመረምር ያደርገናል፡፡ እና በክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ ዙሪያ በኢየሩሣሌም ከተማ የተፈጸመው ትክክለኛው ነገር የትኛው ነው? የክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ወይስ አለመነሣት ወይስ ሌላ?

በመሠረቱ የክርስቶስን ትንሣኤ ከሚቃወሙት ወይም ከማይቀበሉት ጋር ለመከራከር ግልፅ ኾነው በገሃድ የሚታወቁት የአራቱ ወንጌሎች መኖርና የክርስትና ሃይማኖት በዓለማችን ላይ ተመሥርቶ መገኘት ብቻ በቂ ማስረጃ መኾን ይችላሉ፡- ቢያንስ እነዚህ ማስረጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁና ተቀባይነት ያገኙ ናቸውና፡፡ ምናልባት ተጨማሪ ማስረጃ መጥቀስ የሚያስፈልገው በዚያን ጊዜ የነበረውን ተያያዥ ታሪክ ይሆናል፡፡ ለማንኛውም  የሚያነሷቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች ባማራጭነት በመውሰድ በክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ ዙሪያ ያሉ ክርክሮችን እንመርምራቸው፡፡ እነሱም በሚከተለው ሰንጠረዥ የተቀመጡት አምስት አማራጮች ናቸው፡፡ ከእነሱ ውጭ ሌላ መከራከሪያ የሚያቀርብ የለም፡፡

ተ.ቁ. የኢየሱስ ክርስቶስ መላምት
ሞት ትንሣኤ
1 ሞቷል ተነሥቷል፡- ሐዋሪያት ያስተማሩትም እውነት ነው ክርስትና (Christianity)
2 ሞቷል አልተነሣም፡-ሐዋሪያት የተነሣ መስሏቸው ተታለዋል ተታላይነት (Hallucination)
3 ሞቷል አልተነሣም፡- ሐዋሪያት ተረት ፈጥረው አስተምረዋል  ሥነ ተረት(Myth)
4 ሞቷል አልተነሣም፡- ሐዋሪያ የተነሣ አስመስለው አታለዋል ሤራ  (Conspiracy)
5 አልሞተም በደመነፍስ መቆየት (Swoon)

በሰጠንረዡ ከ2-5 ያሉት መላቶች በተ.ቁ.2 እና 4 አማራጮች አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ ከሞት ካልተነሣ ሐዋሪያት ወይ አታለዋል ወይም ተታለዋል የሚል መደምደሚያ መስጠት የግድ ይኾናል፡፡ በዚህም ሐዋሪያት የተነሣ መስሏቸው ተታለዋል ከተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ መነሣቱን ዓይተውና ዐውቀው ነው ያስተማሩት (የመታለላቸው ምክንያት እነሱ አይደሉምና) የሚል መከራከሪያ ይኖረዋል፤ አታለዋል ከተባለም (ሳይሞት ይቅርም፣ ተረትም ይፍጠሩ) እሱ ከሞት አለመነሣቱን ዐውቀው የፈጠራ ታሪክ ፈጥረው አስተምረዋል የሚለው የክርክሩ አቋም ይኾናል፡፡ ሐዋሪያት ከተታለሉም የእነሱን መታለል የተረዱት አካላት በበቂና ባሳማኝ ማስረጃ ሐዋሪያት የተቀበሉትን እውነት ውድቅ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አታላዮቹ ሐዋሪያት ከኾኑም የዓለማችን አስደናቂ የፈጠራ ሰዎች ይሆናሉ፤ ይህንን ኹሉ የዓለም ሕዝብ ለ2000 ዓመታት ማሳመን ችለዋልና፡፡ እነዚህ አማራጭ መደምደሚያዎች ትክክል ካልኾኑ ደግሞ የመጀመሪያው (ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል፤ ሐዋሪያትም ያስተማሩት ያንን ነው፡- እውነት መስካሪዎች ናቸው የሚለው) ትክክል ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ከኾነም የክርስቶስን ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ማረጋገጥ ቻልን ማለት ይሆናል፤ ትንሣኤውም አምላክነቱን ይመሠክራል፡፡  ለማንኛውም አማራጮቹን ለየብቻ እንመልከታቸው፡፡

ሀ. ሥነ-ተረት (Myth)

የክርስቶስን ትንሣኤ የማይቀበሉ አካላት አንድኛ መከራከሪያ አድርገው የሚያቀርቡት ሥነ-ተረትን ነው፡፡ ይህም ‹የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የተረት ፈጠራ ነው› የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ እነዚህም አካላት በሁለት ይከፈላሉ፤ በአንደኛው በኩል የሚገኙት አጠቃላይ የክርስቶስ ታሪክና ፈጸማቸው የተባሉት ተግባራት በተረትነት የተፈጠሩ ናቸው የሚሉ ሲሆኑ፤ ታሪኩን ከሌሎች ከጥንት ከግብፅ፣ ከባቢሎን፣ ከግሪክና ከሮማ ተረታት ጋር በማሳሰል ያቀርባሉ፡፡ በሌላ በኩል የሚገኙት ደግሞ የክርስቶስ ታሪክን ትክክል መሆን ተስማምተው፣ ሥቅለቱንና ትንሣኤውን ግን ከሥነ ተረት ፈጠራ ጋር ያይዙታል፡፡ በዚህ የተነሣም ሐዋሪያትን የክርስቶስን ትንሣኤ በተረትነት ፈጥረው ያስተማሩ አድርገው ይከሷቸዋል፡፡

በእዚህ መላምት መሠረት የክረስቶስ መነሣት የሚባለው ትምህርት ተረታ ተረት ነው እነጂ ምንም እውነት የለበትም፡፡ ሌሎች መላምቶች ኹሉም ምንም መሠረት የላቸውም፤ ክርስትስ  የሚባል ሰው ተሰቅሎ አልተነሳምና፡- ይላሉ፡፡

ይህ መላምት ግን ለልብወለድነት የማይበቃ ግምት ይመስላል እንጂ ማስረጃ ያለውና የታሪክ ተጠየቅን የሚያቀርብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የክርስቶስን ትንሣኤ ተረት መኾኑን ለማሳመን ከኹሉም በፊት የሐዋሪያት ምስክርነትንና የታሪክ አሰረጅነትን ሐሰትነት ማረጋገጥ መቻል አለበት፡፡ እነዚህ ጠንካራ ማስረጃዎች ትክክል አለመሆናቸው ወይም የተሳሳቱ መሆናቸው ከተረጋገጠ እና ታሪኩ ከየት መጣ ለሚለው ጥያቄ መልስ በመስጠት አማራጭ መላምት በመኾን መቅረብ ይችላል፡፡ ያለበለዚያ ግን ለሕዝብ መቅረብ የሌለበት ተራ ግምት ወይም ምኞት ነው የሚኾነው፡፡ የሐዋሪያትን ምስክርነት እንዳው ይሁን ብለን ብንተወው እንኳን የታሪክ ማስረጃዎች  የሚያረጋግጡት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱን ነው፡፡ ለዚህም እንደምሳሌ  ክርስቲያን ያልነበሩት የሦስቱ የሮማ መንግሥት ታሪክ ፀሐፊዎች ምስክርነት ጥሩ ማስረጃ መኾን ይችላል፡፡[2]

 1.  ሊዩሽያን(120-180ዓ/ም) የተባው የታሪክ ፀሐፊ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ተሠቅሎ የሞተ ሶፊስት ፈላስፋ አድርጎ ይጠቅሰዋል፡፡
 2. ጆሰፈስ(37-100ዓ/ም) የተባለው ፀሐፊ ደግሞ ‹ይህ ጊዜ አስደናቂ ጀብዱ የፈጸመው ብልሁ ሰው ኢየሱስ የተገለፀበት ወቅት ነው፡፡ ከመሪዎቻችን መካከል የኾነው ጲላጦስ በቀረበበት ክስ የተነሣ በመስቀል ላይ እንዲሰቀል ሲፈርድበት እሱ ግን ማለቂያ በሌለው ፍቅር አፈቀረው፡፡› በማለት በክርስቶስ መሰቀል የተሰማውን ስሜት ገልዋፅዋል፡፡
 3. ታሲተስ (20-120ዓ/ም) ‹ስሙ ከመጣበት የወጣለት ክርስቶስ የእኛ ሰው በነበረው በጴንጤናዊው ጲላጦስ እጅግ አሰቃቂ የኾነ የሞት ፍረድ ተፈርዶበት ተሰቃየ› ብሎ ፅፏል፡፡

ስለኾነም የክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞት በጊዜው የነበረው የሮማ መንግሥት ታሪክ ምስክርነት፣ የአይሁዳዊያንም በዓለም ላይ ተበትነው በሚያደርጉት የክርስትና እምነት ተቃውሞ ያረጋገጡት ብዙ የእማኝ ምሰክርነት ያለው እውነት ነው፡፡ ይህ ከሆነም ተረታዊያን የሥነ ተረት ተፅዕኖ አስቸግሯቸው ነው በማለት ምግታቸውን እንተወው፡፡

ለ. ክርስቶስ በመስቀል ላይ አልሞተም (The Swoon Theory)

ዕዝል ጉባኤ ቃና

ለበሊዕ ኅብስተ ሮምያ መስቀለ

ቦአ ቃል እንግዳ ዐውደ ቀራኒዮ መርጡለ፡፡

ትርጉም፡-

የሮሚያን እንጀራ መስቀልን ለመብላት

ቃል እንግዳ ወደ ቀራኒዮ አደባባይ ቤት ገባ፡፡[3]

እውን ክርስቶስ በመሥቀል ላይ አልሞተም? ስለመሞቱም ኾነ አለመሞቱ ምን ማስረጃ ይገኛል?

የዚህ ንድፈ ሐሣብ አራማጆች አንድ ጥሩ ጎናቸው የክርስቶስን በመስቀል ላይ መሰቀል ይቀበላሉ፡፡ ስለኾነም የክርክራቸው መነሻ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሕይወት ነበር እንጂ አልሞተም፡- ደክሞት በሰመመን ውሰጥ ነበር፤ ባለመሞቱም ከመቃብር አምልጦ ለሐዋሪያት ተገለፀ፤ እነሱም ከሞት የተነሣ መሰላቸው የሚል ነው፡፡ እና ይህ ትክክል ነው?

ይህ መላምት ትክክል አለመኾኑን ለማሳየት ከዚህ በታች የተጠቀሱትን የመከላከያ ነጥቦች ማቅረብ ይቻላል፡፡

 1. ከኹሉም በፊት መታወቅ የሚኖርበት ስቅላት በጊዜው በነበረው የሮማ መንግሥት ከፍተኛው አሰቃቂና በሕወይት መትረፍ የማይቻልበት ፍርድ ነው፡፡ በዚህ መልክ ተሰቅሎ የተረፈ ሰውም በሮማ ታሪክ አልተመዘገበም፡፡ የክርስቶስም ስቅለት በዚህ መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ በተለየ የሚተርፍበት ዕድል አይኖርም፡፡ ይህንንም ሮማውያን የፍርድ አስፈፃሚዎች የተገበሩት ጠንቅቀው በማወቅ ነው፡፡ ይህ ከኾነም ኢዮሱስ ክርስቶስ ይህን አሰቃቂ ስቅላት አልፎ ሊተርፍ ቻለ ማለት አሳማኝነት የለውም፡፡ ስለዚህ እውነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ነፍሱን ከሥጋው በመለየት መሞቱ ነው፡፡
 2.  ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱን የሕክምና ታሪካዊ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደነበረ መሞቱን ለማረጋገጥም አንድ የሮማ ወታደር  በጦር ጎኑን ወግቶታል፤ በዚህም ውሃና ደም መፍሰሱ ተገልፅዋል፡፡[4] ይህም ኢየሱስ ሳንባውን ብቻ ሳይኾን ልቡንም መወጋቱን ያረጋግጣል፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ልብና ሳንባውን ከተወጋ መትረፍ አይችልም፡፡ ይህንን ማንኛውም የሕክምና ባለሙያ ማረጋገጫ ሊሰጥበት ይችላል፡፡ ለምሳሌም በአሜሪካ የሕክምና ማኅበር መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ የክርስቶስ በጦር መወጋቱ በግልፅ መሞቱን እንደሚያረጋግጥ ገልፅዋል፡፡[5]
 3.  ዮሴፍም የኢየሱስ ክርስቶስን አስከሬን ለመቅበር ጲላጦስን ሲጠይቀው ጲላጦስ መሞቱን ከወታደሮቹ በመጠየቅ አረጋግጦ ነው የሰጠው፡፡ ወታደሮቹም ጉልበቱን ከመስበር የተውት ፍፁም የሞተ መኾኑን አረጋግጠው ነው፡፡ ሳይሞት ቢተውት ከፍተኛ ተጠያቂነትና ቅጣት አለባቸው፡፡ እነዚህ ማስረጃዎችም የኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል መሞት ይመሰክራሉ እነጂ ሳይሞት መቅረት የቻለበት ምክንያት ሊኖር እንደሚችል አይጠቁሙም፡፡
 4. እንዳው እንደ ዕድል ኾኖ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳይሞት ቀርቶ በሕይወት እያለ ተቀበረ ብንል እንኳን ከመቃብር ውስጥ ወጥቶ መሔድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም መቃብሩ በትላልቅ ቋጥኞች ተዘግቷል፤ ይህንን ፈንቅሎ መውጣት አይችልም፡፡ ሌላ ደግሞ ሊያወጣው የሚችል ኃይል የለም፤ ሐዋሪያት አይባል ያልሠለጠኑ ሰዎች በውትድርና የሰለጠኑትን የሮማ ወታደሮች አሸንፈው ከመቃብሩ ውስጥ አውጥተው ወሰዱት ማለት ይሆናል፡- ይህ ደግሞ ለማመን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ደግሞስ ሐዋሪያት ይህንን ካደረጉ የጻፉት ወንጌል ውሸት ነው ማለት ነው? ለምን ይዋሻሉ? የሠሩት ሥራ የጀግና ተግባር አይሆናቸውም እንዴ? እነሱ እንኳን ቢዋሹ የሮማ መንግሥት እንዴት ዝም ይላቸዋል? የአይሁድ ካህናትስ (ፈሪሣዊያን) እንዴት አድርገው የሮማን መንግሥት ዝም ይሉታል? ነው ድርጊቱ  ሣይሠማ ቀርቶ ሊባል? አይ ሐዋሪያት ሣይኾኑ ሮማውያን ወይ ተቃዋሚ የነበሩት አይሁዶች ናቸው የሠረቁት ማለት ደግሞ አይቻልም፤ ምን ጥቅም ለማግኘት? ስለዚህ በሌሎች ተሠርቆ ነው ወይም በሐዋሪያት ከመቃብር ተወስዶ ነው ማለት አይስኬድም፡፡ ከመቃብር በሌሎች ተወስዶ ከኾነም ክርክሩ ሐዋሪያት ዋሽተው አታለውናል በሚል መቅረብ አለበት እንጂ ተሠቅሎ ሳይሞት ቀርቷል የሚል መኾን የለበትም፡፡
 5. መጀመሪያ እንደጠቀስነው ደግሞ ሣይሞት ቀርቶ በራሱ መቃብሩን ፈንቅሎ ወጥቷል ብንልም  መቃብሩን የሚጠብቁ የሠለጠኑ ወታደሮችን አልፎ መሔድ የሚችልበት ዕድል አይኖረውም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በመስቀል ላይ ሲንገላታ ስለዋለ ማምለጥ የሚያስችል አቅም አይኖረውም፡፡ ይባስ ብሎ የግራ ጎኑ (ልቡና ሳንባው) በጦር ተወግቷል፤ ይህንን ተቋቁሞ የሰለጠኑትን ወታደሮች አልፎ የሚሔድበት ዕድልና አቅም አይኖረውም፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ባይሞት እንኳን ሳይሞት ከመቃብር ድንጋይ ፈንቅሎ መውጣት፤ ያንን ፈንቅሎ ቢወጣም ወታደሮች ሳይሰሙት ቀርተው ከእነሱ አልፎ መሔድ፤ ይህንንም የሚያደርግበት አቅም ሊኖረው አይችልም፡፡
 6. ከዚህ ባለፈም ሳይሞት ቀርቶ ከመቃብር ወጥቶ ከወታደሮቹ በማምለጥ መሔድ ቢችል እንኳን በ3ኛው ቀን የብርሃን ክብርን ተጎናፅፎ በክብር ለተከታዮቹ መገለፅ አይችልም ነበር፡፡ እንዴት ኾኖ? በመስቀል የተንጋላታው ሰውነቱ አስፈሪ ገፅታን ይፈጥርበታል እንጂ ግርማና ክብርን አያጎናፅፈውም፡፡ አስፈሪ ገፅታን ለብሶ ለሐዋሪያት ቢገለፅ እንኳን ሳይሞት አምልጦ መጣ ይባል ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህ የማስረጃ ተጠየቆች የሚያረጋግጡልን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ሞቶ፤ ሞትንም ድል አድርጎ መነሣቱን እንጂ ሣይሞት መቅረቱን አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ይህንን የተመዘገበ የታሪክና የወንጌል ማስረጃ ሐዋሪያት በመስማማት ዐውቀው ለማተለያነት የፈጠሩት ነው ከተባለም ክርክሩ ተሰቅሎ ነበር ግን አልሞተም የሚል ሳይኾን ሐዋሪያት ዐውቀው በመዋሸት አታለዋል በሚል ዕይታ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ‹ይህስ ምን ያህል ያስኬዳል?› የሚለውን ደግሞ እየለየን እንመልከት፡፡

ሐ.የሤራ ንድፈ ሐሣብ (The Conspiracy Theory)

በዚህ ንድፈ ሐሣብ መሠረት የክርስቶስ መሞት ብዙም አጨቃጫቂ አይደለም፤ ተሰቅሎ ሞቷል፡፡ ይሁንና ክርስቲያኖች እንደሚያምኑትና እንደሚያስተምሩት ከሞት አልተነሣም፤ ከሞት ተነሥቶ ታየ በማለት ሐዋሪያት በመስማማት የሐሰት ታሪክ ፈጥረው ስለአስተማሩ ነው እንጂ! የክርስቶስ ትንሣኤ ሐሰት ነው፡፡

ኾኖም ይህም ንድፈ ሐሣብ ቢኾን ምንም ማስረጃ፣  የታሪክ እና የሥነ ልቦና ተጠየቅ የለውም፡፡ ምክንያቱም፡-

 1. በመጀመሪያ ደረጃ ሐዋሪያት ይህን ፈጠራ ፈጥረው ለማታለል የሚችሉበት በቂ ምክንያት ወይም በማታለል የሚያገኙት ጥቅም መኖር አለበት፡፡ በታሪክ እንደተመዘገበው ሐዋሪያትን ያጋጠማቸው ግን የክርስቶስን ወንጌል በመስበካቸው መሰቃየት ነው፡፡ ለመኾኑ መታሠራቸው፣ መደብደባቸው፣ መሰደዳቸው፣… ምን ጥቅም ለማግኘት ነው? ሥልጣን? ሀብት? ዝና? በወንጌልና በታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ከኾነ በጊዜው በነበረው ሁኔታ ሥልጣን፣ ሀብትና ዝና ለማግኘት ዋሽተው የክርስቶስን ትንሣኤ ከመመሥከር ይልቅ ከሮማ መንግሥት ጋር ቢያብሩ፤ ከፈሪሳዊያን ጋር ቢተባበሩ የተሻለ ዕድል ይኖራቸው ነበር፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የምድራዊ ጥቅም ለማግኘት ያለመ አይደለምና፡፡ አንድ ሰውም ምንም ጥቅም ለማይገኝበት ነገር ዝም ብሎ አይዋሽም፤ ለውሸቱም ጥብቅና ቆሞም አይሰቃይም፤ በዚያም ሥራን አይሸርብም፡፡ እንዴትስ ኹሉም በመስማማት ማሤር ቻሉ? አንድ ሰው እንኳን ሐሰትነቱን አያጋልጥም? ሐዋሪያትስ አሢረው ያታለሉት ማንን ነው? ተከታዮቻቸውን ወይስ የእነሱ ተባባሪ የማይኾነውን ኅብረተሰብ? መቼም ተከታዮቻቸው የኾኑ ክርስቲያኖች ተታለናል ሲሉ አልተሰሙም፡፡ ሌላውን ኅብረተሰብ ከተባለ ምን ቂም ኖሯቸው ነው ኅብረተሰቡን በሐሰት የሚያታልሉት? ወይም ምን ጥቅም ለማግኘትስ የዓለም ሕዝብ በሤራቸው እየተታለለ እንዲኖር አደረጉ? የሚያስኬድ አይመስልም፡፡
 2. ሐዋሪያት በነበሩበት ጊዜ ሰው ሞቶ ይነሣል የሚል የተለመደ ዕምነት አልነበረም፡፡ ሰውን ዋሽቶ ማታለል የሚቻለው በተለመደና በሚታመን ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ የነበሩት ፈሪሳውያንና ኤሣውያን የሚባሉት አጠቃላይ ትንሣኤ (ምጽአት) በዓለም ፍጻሜ እንደሚኖር ቢያምኑም በተለየ ክስተት ሰው ሞቶ ከተቀበረ በኋላ ይነሣል የሚል ዕምነት አልነበራቸውም፡፡ ሰዱቃዊያን የሚባሉት የአይሁድ ክፍሎች ደግሞ ጭራሹንም ትንሣኤ ሙታን መኖሩን አይቀበሉም ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ሮማውያን ጣኦት በማለክ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ ሐዋሪያትም ቢኾኑ ከዚህ ኅብረተሰብ የተገኙ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሣ ቀድሞ ቢነግራቸውም፤ ልምዱ አልነበራቸውም፤ እምነታቸውም ሙሉ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በማኅበረሰቡ ያልተለመደውንና እነሱም በእምነት ሙሉ ያልኾኑበትን ፈጥረው በመዋሸት ለማሳመን አይሞክሩም፡፡ በዚህ ሁኔታ እያሉስ እንዴት ሤራን ለመጎንጎን ይችላሉ?
 3. ሐዋሪያት የተመረጡት ከተለያየ የድሃ ኅብረተሰብ ስለኾነ በአንድነት አሢረው ማታለል የሚያስች የሕግ ዕውቀትና ስልት አልነበራቸውም፡፡ ብዙ ሰውን በሤራ ተጠቦ ለማታለልም ልምድ፣ የዳበረ ዕውቀት፣ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ልዩ ጥቅም፣ ያንንም ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊ የኾነ ስልት… ያስፈልጋል፡፡ ሐዋሪያት ደግሞ የተሰባሰቡት ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል (ካልተማረው) ነው፡፡ ለምሳሌ ዓሣ አጥማጆች፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎች (በዚያን ጊዜ እንደ ሴተኛ አዳሪነት ይጠላ የነበረ)፣ ገበሬዎች፣ ሐኪሞች… ነበሩ እንጂ እንደ ፈሪሣዊያንና የሮማ መንግሥት ባለሟሎች ለማታለል የሚያስች ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ ሰዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች መቀናጀት ችለውና በዕቅድ ተስማምተው  አታለሉ ማለት የሚያሳምን አይደለም፡፡
 4.   ሐዋሪያት አታለው ቢሆንም የሮማ መንግሥትና ፈሪሳውያን  በቀላሉ አታላይነታቸውን ማጋለጥ ይችሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስን ‹ሬሣ› ከተቀበረበት በማውጣት ሐሰት መኾኑን በአደባባይ ማጋለጥ፤ በዚህም የሐዋሪያትን ትምህርት ማንም እንዳይቀበለው ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ይህንን አድርገዋል የሚል የታሪክ ማስረጃ ደግሞ የለም፡፡
 5. ሁሉም ሐዋሪያት ተባብረው በአንድነት  በሤራው ይጸናሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አንድም ሐዋሪያ የክርስቶስን ትንሣኤ በመመስከር ሥቃይ ከመቀበል ውጭ በሐሰት ኅብረተሰቡን ማታለላቸውን በሥቃይ ውስጥ እያለ እንኳን ተፀፅቶ አልመሰከረም፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሮ ለእውነት ጥብቅና በመቆም ይሞታል እንጂ ለሐሰት ራሱን መስዋዕት እስከ ማድረግ የደረሰ ዋጋ አይከፍልም፡፡
 6. የቤተ ክርስቲያን መመሥረትም የክርስቶስ ትንሣኤን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ክርስትና ማንም ሊክደው የማይችል ዓለማቀፋዊ ሃይማኖት ነው፤ የተመሠረተውም በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ በመከራና በሥቃይ ነው፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን ከኾነም ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረችበት ከበዓለ ሐምሣ ጀምሮ በኢየሩሳሌም የተደላደለ ኹኔታ አልነበረም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የአረማዊያን (የአህዛብ) ጣኦት አምልኮ ልምድ ተጽእኖና የአይሁዳዊያን ተቃውሞ ዙሪያዋን ከቧት ስለነበር ብዙ መጋደል ተደርጎ ነው መመሥረትና መስፋፋት የቻለችው፡፡ በዚህ መከራና ሥቃይ ውስጥ ተመሥርታ ልትስፋፋ የቻለችውም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እውነት ስለኾ ነው፡፡ የክርስቶስ መሰቀልና ከሞት መነሣት ሐሰት ቢኾን ኖሮ ግን በመስቀል ላይ (በመከራ) ቤተ ክርስቲያን ተመሥርታ አሁን ባለችበት ደረጃ መገኘት አትችልም ነበር ፡፡
 7. ከኹሉም በላይ ደግሞ የክርስቶስ ደቂቃነ መዛሙርት የክርስቶስ አስደናቂ መገለጥና ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ለዓለም ለመመሥከር ያደረጉት ተጋድሎ የዚህን መላምት ስህተትነት ቁልጭ አድርጎ ያሣውቀናል፡፡ የክረስቶስ ተከታዮች ከትንሣኤው በፊት ፈሪዎችና ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ቁርጠኝነት የሚያንሳቸው ነበሩ፡፡ ከክርስቶስ ተንሣኤ በኋላ ግን ሞትና መከራ የማይመልሳቸው ሲወገሩ የሚፀልዩ፤ ማንንም የማይፈሩና ለኅሊና የሚሰቀጥጥ ድርጊት ሲፈፀምባቸውም ምንም የማይመሰላቸው ኾነው ነው የተገኙት፡፡ ለምሳሌ ክርስቶስን በአንዲት ሌሊት ሦስት ጊዜ በመካድ ታውቆ የነበረው ቅ.ጴጥሮስ በሮም አደባባይ ላይ ‹እንዴ ጌታዬ ሳይኾን ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ› በማለቱ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ሞቷል፤ ቅ.እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወግሩት ፀሎት ያደርስ ነበረ፤ ቅ.ማርቆስ ለአንበሳ ተሰጥቷል፤ ቅ.ቶማስ ከመከራው ጥናት የተነሳ ቆዳው እንደ ሽንኩርት ተልጦ ጨው ተነስንሶበት ተሰቃይቶ ነው የሞተው፡፡ በአጠቃላይ አይሁዶች ባደረሱት የማሳደድ ሥራ፣ አላዊያን ነገሥታት በፈጸሙት ዘግናኝ ስቃይ ሐዋሪያት ወንጌልን በስቃይ ውስጥ ኾነው የሰበኩት የክርስቶስን ትንሣኤ ዓይተው በማረጋገጣቸው ነው፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ሐሰት ቢኾን ኖሮማ የመጀመሪያዎቹ ነቃፊዎች ሐዋሪያት ይኾኑ ነበር እንጂ ጥቅም ለሌለው ነገር እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ጸንተው መቆየት አይችሉም ነበር፡፡ ስለዚህ ሐዋሪያትና ተከታዮቻቸው በስቃይ ውስጥ ኾነው ሕይወታቸውን መስዋዕት ለማድረግ የቆረጡት በክርስቶስ ትንሣኤ ተማርከውና ትንሣኤ ሙታን መኖሩን በእምነት አረጋግጠው ነው፡፡ በዚህ ላይ ቅ.ጳውሎስ ‹ትንሣኤ ሙታን ከሌለማ ስብከታችን ከንቱ ኾነ› ያለው ልብ ተብሎ መስተዋል ይኖርበታል፡፡
 8. በሌላ በኩልም #‹ሐዋሪያት ክርስቶስ ተነሥቷል በማለት በሐሰት አታለዋል› የሚሉ የዚህ ንድፈ ሐሣብ ተከራካሪዎች ክርክራቸውን  የሚደግፍ ምን ማስረጃ ይዘው ነው የተነሱት?$ የሚል ጥያቄን ብንጠይቅ ማስረጃ እንዳላቸው የሚገልፅ መልስ ማግኘት አንችልም፡፡ ምክንያቱም የዚህ ንድፈ ሐሣብን ትክክልነት ለማረጋገጥ ተመዝግበው የሚገኙትን የወንጌልና የታሪክ ማስረጃዎች ውድቅ የሚያደርግ ተደብቆ የተገኘ የሐዋሪያት የማታለያ የስምምነት ሰነድ ወይም ቢያንስ በሐዋሪያት የማታለል ስምምነት ላይ የነበረና ኹኔታውን የተከታተለ የዓይን እማኝ ምስክርነት ጽፎ ያስቀመጠው ማስረጃ መገኘት ነበረበት፤ ያለበለዚያ የ‹ቢኾንስ› ግምት ነው የሚኾነው፡፡ የተባለው ማስረጃ ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ የማታለል ንድፈ ሐሣብ ማስረጃም ምክንያታዊ ተጠየቅም የሌለው ግመታ ብቻ ነው ብለን ውድቅ ለማድረግ እንገደዳለን፡፡
 9. የሐዋሪያት ማታለል ትክክል ከሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ሁሉ ጥያቄ እንደሚነሣባቸውም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ምክንያቱ የሐዋሪያት የትንሣኤ ምስክርነት በተግባራዊ ድርጊት የተደገፈና በታሪክ ክስተት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያለው ነው፡፡ ይህ ሐሰት ነው ከተባለ ታዲያ ምን ዓይነት የታሪክ ማስረጃ ነው እውነት ኾኖ ተቀባይነት የሚያገኘው? የመጀመሪያ ደረጃ ማስረጃ (ምስክርነት) ተቀባይነት ከሌለው እንዴት ኾኖ ነው በተጻፉ ታሪኮች ላይ መስማማት የሚቻለው? …

መ. የመታለል ንድፈ ሐሣብ

በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት የተታለሉት ሐዋሪያት ናቸው፤ ይህም ሊሆን የቻለው በምትሃት ነው፡፡ ሆኖም አስተሳሰቡ ምንም ዓይነት የማስረጃ ተጠየቅ የለውም፡፡ እንዴት እንደማያስኬድ ለመገምገምም የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፡፡

 1. ራሳቸው ሐዋሪያት የመጀመሪያ ደረጃ (የዓይን) ምስክሮች ናቸው፡፡ ከእነሱ መካከል ግን አንድም በምትሓት ተታለልኩ በማለት የመሰከረ የለም፡፡ እና ሌሎች ከየት አምጥተው ነው የሐዋሪያትን  መታለል የሚናገሩት?
 2. እንዳው ይሁን እንኳን ብንል በዚያን ጊዜ የነበረው ነበራዊ ኹኔታ መላምቱን እንዳንቀበል ያደረገናል፡፡ ለምሳሌ በምትሃት መታለል በግል ነው እንጂ በኅበረት በአንድ ላይ መከሰት አይችልም፤ የተለያዩ ሰዎች በተለያየ ቦታ በማየት ቢታለሉ እንኳን ማስመሰል ይቻል ነበር፤ በአንድ ሥፍራ ግን ብዙ ሰዎች በአንድነት ምትሐት ዓይተው ተታለሉ ለማለት አይቻልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ 500 ሰዎች በተሰበሰቡበት ተገልፆ ታይቷል፡፡ እና ይህ ኹሉ ሕዝብ እንዴት በአንድነት በምትሐት ሊታለል ይችላል? ይህ በእውነት የሰዎችን ሥነ ልቦናዊ ተፈጥሮም ያስተዋለ ግምታ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምትሐት በፍርሐትና ቀድሞ ሊኾን ይችላል ብሎ በመገመት የሚፈጠር የሥነ ልቦና ችግር ነው፡፡ 500 ሰዎች እኩል የፍርሐት ግምትና ሥነ ልቦናዊ ኹኔታ ኖሯቸው በምትሐት ተታለሉ ማለት ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡
 3. ምትሐት ሊፈጠር የሚችለው ለተወሰነ ደቂቃ ቢበዛ ለሰዓታት ነው ክርስቶስ ግን ለ40 ቀናት እያስተማራቸው አብሯቸው እስከ ዕርገቱ ቆይቷል፡፡ ይህ በኾነበት እንዴት በምትሃት መላምት እንመን?
 4. ምትሐት የሚፈጠረው በሚታወቅ ነገር እንደ ህልም ነው የክርስቶስ ተነስቶ መታየት ግን በእውን ሰውነት፤ አብሯቸው እስከ መብላትና እያስተማራቸው እስከመቆየት ድረስ ነው፡፡ (1) በምትሐት የሚታይ ሰው አይመገብም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከትንሣኤው በኋላ ከሐዋሪያት ጋር አብሮ ቁጭ ብሎ ተመግቧል፡፡ (2)  ምትሐት የሆነ ሰው አስተምሮ ሰዎችን ሊያሳምን አይችልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለ40 ቀናት ሐዋሪያት ሲያሰተምራቸው ቆይቷል፡፡ (3) ምትሐት የሆነ ነገርን በእጅ በመዳሠሥ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ቶማስ ግን የክርስቶስን አካል እውንነት በእጁ ዳስሶ ማረጋገጥ ችሏል፡፡
 5. የክርስቶስ ትንሣኤ ምትሐት ከኾነ መቃብሩ ባዶ ሆኖ መገኘት አይችልም ነበር፤ ‹ሬሣ›ው በመቃብሩ ውሰጥ ይገኝ ነበር እንጂ! በመቃብሩ ላይ የተከደነው ቋጥኝም አይፈነቀልም ነበር፡፡ ስለዚህ በዚያን ጊዜ የተፈጠሩትን ክስተቶች ከትንሣኤ ውጭ ሊገልጻቸው የሚችል መላምት የለም፡፡
 6. ሐዋሪያት እንኳን እውነት መስሏቸው ቢታለሉ አይሁዳውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ‹ሬሣ› በማምጣት አለመነሣቱን ያሣዩ ነበር እንጂ በመታለላቸው ሌሎችን ሰዎችም ሲያታልሉ ዐይተው ዝም አይሉም ነበር፡፡

ስለዚህ ይህ መከራከሪያም ተቀባይነት ሊኖር የሚችል አይደለም፡፡

ሠ. ተንሥአ እምውታን ወዐረገ በክብር

በአጠቃላይ ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው አማራጭ መላምቶች እንደማያስኬዱ ከተረዳን ያለው ትክክለኛ አማራጭ በክርስትና የሚታመነው እውነት ነው ማለት እንችላለን፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የታየ ልዩ ክስተትም እንደተናገረው ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱና ማረጉ ነው፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያን ተመሥርታለች፤ የክርስትና ሃይማኖትም እንደዚሁ ተመሥርቶ ተስፋፍቷል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተጻፉ የነቢያት፣ የሐዋሪያት፣ የአበው፣ የሊቃውንትና የታሪክ መጻሕፍት ማስረጃዎችና ምስክርነቶች ሞልተዋል፡፡ ስለዚህ እነሱን መመልከት ይገባናል እንጂ በዘመኑ የ‹ፋሽን› መንፈስ መበረዝ የለብንም፡፡

በትንሣኤ ዙሪያ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምታስተምረው ትምህርት ምን እንደሚመስል ለመረዳት ካስፈለገም  ትንሣኤ ዘክርስቶስ  የሚለውን የቀሲስ ደጀኔ ሽፈራውን መጣጥፍ መመልከት መልካም ነው፡፡

ተያያዥ ጽሑፎች፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው

እግዚአብሔር ለምን ሰው ኾኖ መገለጥ አስፈለገው?


[1] የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ 1፣ ገፅ- 352

[2] . In Great Books of the Western World, ed. By Robert Maynard Hutchins, Vol. 15, The Annals and The Histories by Cornelius Tacitus (Chicago: William Benton, 1952).

[3] የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ 2 ገፅ 26

[4] ዮሐ.19፡-34

 1. [5] William D. Edwards, M.D., et al., “On the Physical Death of Jesus Christ,” Journal of the American Medical Association 255:11, March 21, 1986.
Please follow and like us:
error

4 COMMENTS

Leave a Reply