‹የጨው ተራራ ሲናድ ፣ ሞኝ ይስቃል ብልህ ግን ያለቅሳል›

ፀጋየ ገ/መድኅን

‹ኑቢያም ፣ ጥንታዊ ጥቁር ግብፅም፣ የዛሬይቱ ጅቡቲም፣ ጥንታዊቱ ሳቢያም፣ ልክ እንደ ኢትዮጵያ የዘር ግንድ ምንጫችን፣ የነሱም መነሻቸው የኩሽ ነገድ ነው፡፡ በኋላ ግን ሁላችንም ከሞላ ጎደል ከሴም ነገድ ጋር ተቀይጠናል፡፡ ቋንቋዎቻችንም፣ ባህሎቻችንም፣ ሥልጣኔዎቻችንም፣ ተወራራሾች ሆነዋል፡፡ አንዲት ምሳሌ ልጥቀስ ክርስቶስ በሰበከበት በአራማይክ ወይም አረማዊኛ ቋንቋ ውስጥ ብዙ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግሦች ይገኙበታል፡፡ ይኸ ሊሆን የቻለው በታሪክ ሂደት ነው እንጂ፤ በሥነ ብዕር ረጅም መተሳሰር ነው እንጂ እንዳው በአቦ ሰጡኝ አጋጣሚ አይደለም፡፡

የዓባይና የአትባራ ወንዞች ለየብቻቸው ከጣና ሐይቅ ወጥተው፣ በጥንታዊት ኑቢያ አትባራ (አድባራ) ከተማ እንደገና በሚገናኙበት ወረዳ ውስጥ ከነባለቅኔው ተዋናይ ኤኬራ ኔፍራት (ውሂብ ነፍስ) ጀምሮ እስከ ነቢዩ ሄኖክ (የአምላክ ተምሳል) ድረስ፣ በኋላም ከእነ ቅዱስ ያሬድ (የፀሐይ ንጉሥ እጅ)፣ እስከ ሊቁ ቅኔ በጉንጬ ድረስ፣ ከዚያም ከደራሲው ንጉስ ከቅዱስ ላሊ በላ (የፀሐይ ፀሐይ ዙፋን) እስከነ ሊቁ ገብረ ክርስቶስና ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ድረስ፣ ዛሬም ከነቀኝ ጌታ የፍታሔ ንጉሤ እስከነ ክቡር ባለቅኔ ከበደ ሚካኤል ድረስ፣ በተለይ ውድ ሕይወታቸውን ለአገር አንድነት መስዋዕት መክፈል ላይ እስካሉት ነፃ ጋዜጠኞች ድረስ፣ የብዕር ሀረግ የሚመዘዘው ከጥንት ኢትዮጵያዊነት የዘር ግንድ ነው፡፡ ከበደ ሚካኤል ‹እኛ የምንጽፈው በቀለም ሳይሆን በደማችን ነው › ያሉት ይህንኑ የብዕር ደም ሥር የዘር ሀረግ ነው፡፡

አዎን፣ ያልዘሩት አይበቅልም፡፡ የብዕር አባቶቻችን  የጨው ተራሮቻችን ናቸው፡፡ ‹የጨው ተራራ ሲናድ ፣ ሞኝ ይስቃል ብልህ ግን ያለቅሳል› መባሉ፣ አንድ ነገር ተገነጣጥሎ ሲሞት የተሰባበረ አጥንቱን መልሰው የሚገጣጥሙት፣ የጨው ተራሮቻችን፣ የብዕር አባቶቻችንና ወራሾቻቸውና ወጣት የብዕር  ልጆች ስለሆኑ ነው፡፡ ያልዘሩት አይበቅልም ማለታችን ለዚሁ ነው፡፡›

  ጦቢያ ጋዜጣ ጽቅ11፣ ቁ.9 1996

Please follow and like us:
error

Leave a Reply